Mar 31, 2011

ጾም

ሰው የነፍስና የሥጋ ውህድ ፍጡር ነው፡፡ በመሆኑም የነፍሱን ጥም በቃለ እግዚአብሔር ሲያረካ እንደ ሥጋዊነቱ ደግሞ ሥጋዊ ምግብን ይመገባል ይጠጣል፡፡ በነፍስና በሥጋ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት ነፍስ ኢመዋቲ ሥጋ ደግሞ መዋቲ መሆናቸው ነው፡፡ በሌላ ገለጻ ሥጋ ያለነፍስ ሕይወት የላትም፡፡ ነፍስ ያለሥጋ ብቻዋን ጽድቅን እንደማትፈጽም ሁሉ ያለምግበ ሥጋም ሥጋ ቀዋሚ አይደለችም፡፡ ስለዚህም ነው ጽድቅ የነፍስና የሥጋ ጥምር ድርጊት የሆነ ነው፡፡ 

የሰው ልጅ ሁሌም ቢሆን በፍላጐቱ መካከል ባለ ጦርነት ውስጥ ያለ የጦር ሜዳ ነው፡፡ ፈቃዳችንን ከፍላጐታችን ጋር ለማስታረቅ ሁሌም እንታገላለን፡፡ በአብዝኃኛው ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን የመምረጥ ችግር የምናስወግደው ማእከላዊ የሆነ ውሳኔን በመወሰን ነው፡፡ ጾምም የዚህ ውሳኔ አንዱ አካል ነው፡፡ በመብላትና ፍጹም ባለመብላት መካከል ያለ የሕይወት ውሳኔ ነው፡፡

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር የሚያስፈልጋቸውንም አብሮ ፈጥሯል፡፡ ለአዝእርት፣ ለዕፅዋትና ለአትክልት የሚያስፈልጋቸውን አየር፣ ብርሃንና መሬት ቀደሞ ካዘጋጀ በኋላ ፈጠራቸው፡፡ ሰውንም ከምድር አፈር ሲያበጃጀውና የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ሲልበት ሕያው ነፍስ ያለው ፍጥረት ሆነ፡፡ ይህንን ከማድረጉ በፊት ከምድር አፈር ስለሠራው ፍጹም ሥጋዊ ነው፡፡ ስለዚህም ለሥጋው የሚሆን ምግብን ቀድሞ አዘጋጅቶለታል፡፡ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ሲልበት ፍጹም የሆነ ዕውቀትን ስለሞላበትም ክፉና ደጉን እንዲለይ በሕሊናው ሰሌዳ ላይ የእግዘብሔርን ቃል ጽፎለታለ፡፡ እንግዲህ ሰው ማለት የእነዚህ ሁለት ነገሮች ውህድ፣ ሥጋዊ ብቻ ያይደለ ሰማያዊ፣ ነፍሳዊ ብቻም ሳይሆን ሥጋን የለበሰ ልዩ ፍጠር ነው። የሰው ልጅ በገነት ሲኖር ለመብላት ብቻ የተፈጠር እንዳይመስለው ሕግን ሰጠው፡፡ ይህ የፍቅር ሕግ ባይሰጠው ኖሮ ምናልባትም አዳም የተፈጠረው ከእርሱ ቀድመው የተፈጠሩ ፍጥረታትን ለመመገብ ይመስለው ይሆናል፡፡ የዚህ የፍቅር ሕግ ፍፁምነት የሚረጋገጠው ለሰው ልጅ በሰጠው የመምረጥ መብት ነው፡፡ የመጀመሪያው የጾም ሕግም ይህ ነው፡፡ ከመብል ፍጹም በሆነ ፈቃድ መከልከል የሰው ልጅ የውድቀት መጀመሪያ ወሰን የለሽ ምኞቱ ሲሆን የዚህ ምኞቱ መጨረሻም ለመብላት የተፈጠረ እስኪመስል ለመብል መጐምጀት ነው፡፡

ሥጋ የነፍስ ጠላት ነውን፧
በፍጹም ግኖስቲኮች ፨ጝኖስቲቺስም፨ ሥጋን የነፍስ ጠላትና የኃጢአት ማደሪያ አድርገው ያስተምራሉ፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥጋን የኃጢአት ማደሪያና የነፍስ ጠላት ነው ብላ አታስተምርም፡፡ የምንጾመው ሥጋን ለማድከም እንጅ ሥጋን ለመጉዳት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ቤተክርስቲያናችን ራስን በራስ ሕጽው ፨ጀንደረባ፨ ማድረግ የማትፈቅደው፤ የጾም ዋና ዓላማም ሥጋን ለንፍስ ማስገዛትና መብል የኑሮ ግብ እንዳልሆነ ማሳየት ነው፡፡

ጾምን መቀደስ ማለት።።
በተለያዩ ምክንያቶች ከምግብ ልንከለከል እንችላለን፡፡ ክብደት ለመቀነስ፣ ፓለቲካዊ ዓላማን ለማሳካት፣ የምንበላው ስላጣን፣ መብላት ስለሰለቸን ከምግብ ልንከለከል እንችላለን፡፡ ከላይ የተገለጹት ነጥቦች ዓላማ ግን ነፍስን ለሥጋ ማስገዛት እንዳልሆነ ግለጽ ነው፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ «ጾምን ቀድሱ» ያለን፡፡ የምንጾምበትን ምክንያት በግልጽ ማወቅ ጾማችንን የተቀደሰ ለማድረግ ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ ጾማችንን ልዩ ፨የተቀደሰ፨ የሚያደርገው ዋና ነጥብም ከጾማችን ጐን ለጐን ክርስቲያናዊ እሴቶቻችንን መጠበቅና መፈጸም ስንችል ነው፡፡ ጾማችን በጸሎት፣ በስግደትና በተመስጦ የታጀበ ከሆነ እውነትም ጾምን ቀድሰናል ማለት ነው፡፡

ሥጋችንንም ሆነ ሕሊናችንን ከኃጢአት መቆጠብ ካልቻልን ጾማችንን ከላይ ከገለጽናቸው ነጥቦች መቀደስ፨መለየት፨ አልቻልንም ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የሰውነት ማጐልመሻ እንቅስቃሴ ሠርቶ የሚደክመውና ጾሙን ውሎ የሚደክመው ክርስቲያን ልዩነታቸው ምኑ ላይ ነው፧ ጾም ኃጢአት መሥራት የተለማመዱት የስሜት ሕዋሳቶቻችንን በማድከም ወደ መንፈሳዊ የሕይወት ልምምድ ማምጣት ነው፡፡ የስሜት ሕዋሳቶቻችን ያዩትን፣ የሰሙትን፣ የዳሰሱትንና የቀመሱትን ነገር መልእክት የሚያስተላልፉት ለአዕምሯችን ነው፡፡ ስለዚህም የስሜት ሕዋሳቶቻችን ብቻ ለኃጢአት ዝግ ማድረግ ጾማችንን የተቀደሰ ከሚያደርጉልን ነጥቦች አንዱ ነው፡፡ “ስለምን ጾምን አንተም አልተመለከትከንም፧” የሚለው ኃይለ ቃል መሠረተ መልእክትም ከመብል፣ ከመጠጥ መከልከል ጀርባ ክርስቲያናዊ የሆኑ እሴቶቻችን የምንፈጽምበት ወቅት መሆን እንዳለበት አመላካች ነው፡፡ ሥጋን ከነፍስ ያዋሐደ፣ ሥጋን ለነፍስ ያስገዛ፣ ፍጹም መንፈሳዊነት የሚታይበት የጥርምት ጾም ሲሆን ጾማችንን የተቀደሰ ያደርገዋል፡፡

ጾምን በልምድ ወይስ በልምምድ፧
ለብዙ ጊዜ ከምግብ ተከልክለናል፡፡ ነገር ግን በጾማችን ላይ የጨመርነው አንዳችም መንፈሳዊ ግብአት ስለሌለን ጾማችን በልምድ የቆመ ሆኗል።

ጾምን ከልምድ የአጿጿም ዘዬ ወጥተን በተመስጦ የተሞላ ለማድረግ በትንሽ በትንሹ መንፈሳዊነትን መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ የጾም ግብ ለስንት ሰዓት ያህል ከምግብ ተከልከለናል ሳይሆን ለምን ያህል ጊዜ በተመስጦና በበቂለ ሕዋሳት ተጹሟል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ተመስጦ የሚመጣው እንዲሁ በልምድ አይደለም፡፡ ምን ያህል ሰዓት እንደጾምን ስናስብ፣ ምን ያህሉን የቀኖና አጽዋማት እንደጾምን ስንቆጥር እንደፈሪሳዊው በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ ማለት ስንጀምር በእውነትም ጾማችን በልምድ የተመሠረተ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ የጾምን መንፈሳዊ ኃይል በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተመልክተናል፡፡ ፨ማቴ ፬፥፩፡፩፩፨ ፍፁም የሆነ ጾም የኃጢአት ሥሮችን የሚያደርቅ፤ ከዲያብሎስ ሥራ የሚያርቅ መሣሪያ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡ ጾማችን ከመንፈሳዊ ልምምድ ጋር አቆርኝተን በተመስጦ የምንጾመው መቼ ነው፧ ጾም ፍፁም በሆነ ፈቀደኝነት የሚፈጸም መንፈሳዊ እሴት ነው፡፡ በፍፁም ፈቃድ የሚፈጸም ጾም ልምድን አሽቀንጥሮ ለመጣል አይከብደውም፡፡ ሁሌም በጾማችን ራሳችንን ልንጠይቀው የሚገባን ጥያቄም “እውን በፍፁም ፈቃዴ እየጾምኩ ነውን፧” የሚለው ነው፡፡

የነቢያት ጾም ።። የመጠበቅ ጾም
ጾምን ለተለያዩ መንፈሳዊ ዓላማዎች እንፈጽማለን፡፡ ለመንፈሳዊ ኃይል፣ ለተአምራት፣ የዲያብሎስን ሥራና ተንኮል ለማራቅ፣ የሥጋ ጾርን ለመዋጋት አበው ይጾማሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም መንፈሳዊ ተምኔታቸው እንዲሟላላቸው የሚጾሙ አበውም ይጠቀሳሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን የተጠቀሱ አባቶች አብዛኛው ጾም የመጠበቅ ጾም ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የሚፈልጉትንና እንዲሆንላቸው የሚጠብቁትን ነገር በጾም ይጠይቃሉ፡፡ ነቢያት ፨ምሳሌ ነቢዩ ዳንኤል፣ ሠለስቱ ደቂቅ፣ ነቢዩ ኤርምያስ።።፨ የእስራኤላውያንን ነጻ መውጣት በመጠበቅ ይጾሙ ነበር፡፡ በእስራኤላዊያን ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ይሻር ዘንድም የአስቴርን መልስ ለመጠበቅ ጾመዋል፡፡ ከዚህም በላይ ነቢያት የመሲህ ክርስቶስን መምጣት በተስፋ በመጠበቅ ይጾሙ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጾመ ነቢያት የመጠበቅና የተስፋ ጾም የተባለው፡፡ የብርሃኑን ዘመን በመናፈቅ የክርስቶስን ልደት ለመጠበቅ ለብዙ ጊዜ አምላካቸውን በጾም ጠይቀዋል፡፡ ይህን የነቢያት ጾም መሠረት አድርገን የነበርንበትን የጨለማ ዘመን ለማስታወስና መብል የሌለበትን መጪውን ሕይወታችንን ተስፋ በማድረግ፣ ጌታ ለኛ ያደረገውን የማዳን ሂደት የምናስታወስበት የተመሰጦ ጊዜ ነው፡፡ ጥትናን የተመለከትንበት ጾም ነውና በትሁት ልቡና ጾሙን ጾመን በረከት የምናገኝበት እንዲሆን አምላካችን ይርዳን፡፡
ጾም፦ መከልከል፣ መታገድ፣ መታቀብ ሲሆን ሁሉ እያለ ሁሉ ምሉዕ ሆኖ ሳለ ያንን በመተው በሥጋ ዓለምን ድል ማድረግ ነውና።
ምንጭ፥ በማሞ አየነው። ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ፤ 

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።