እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ለከበረ መስቀል በዓሉ ነው። ይህም የጻድቁ ንጉሥ የቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ከተሠወረበት የገለጠችው ነው።
የጎልጎታን ኮረብታ በአስጠረገች ጊዜ የከበረ መስቀልን አገኘችው ታላቅ ኮረብታም የሆነበት ምክንያት እንዲህ ነው። ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቃብሩና ከመስቀሉ የሚገለጡ ሁነው ሙታን ይነሡ ነበርና የጎበጡና በሽተኞች ሁሉ ይፈወሱ ነበር።
ስለዚህም አይሁድ ተቆጡ እንዲህም ሥርዓትን ሠርተው አዘዙ በይሁዳ አገር ሁሉና በኢየሩሳሌም ቤቱን የሚጠርግ ሁሉ ወይም አፈር ወይም ጉድፍ የሚጠርግ በናዝሬቱ ኢየሱስ መቃብር ላይ ይጥል ዘንድ እንዲህም እያደረጉ ዕሌኒ ንግሥት እስከ መጣች ድረስ ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ኖሩ።
እርሷም በመጣች ጊዜ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብርን እስከ አሳዩዋት ድረስ አይሁድን ይዛ አሠቃየቻቸው ያንን ኮረብታም እስከ ጠረጉ ድረስ አስገደደቻቸው የከበረ መስቀሉም ከተቀበረበት ተገልጦ ወጣ።
ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራች በዚች ቀንም አከበሩዋት ለመስቀሉም በዓልን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን አከበሩለት። የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም ከሀገሮቻቸው በመምጣት ክብር ይግባውና ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤውን በዓል እንደሚያከብሩ ለመስቀልም ታላቅ በዓልን የሚያክብሩ ሆኑ።
መስቀሉን ያስወጣችው የእሌኒና የቆስጠንጢኖስ ታሪክ
ይኽ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የአባቱ ስም ቊንስጣ የእናቱ ስም እሌኒ ነው፤ ከሓዲው መክስምያኖስ በሮሜ በአንጾኪያ እና በግብጽ ነግሦ በነበረ ጊዜ አባቱ በራንጥያ ለሚባል ሀገር ንጉሥ ነበር፤ እሌኒ ከርሱ ቆስጠንጢኖስ ከወለደችው በኋላ አባቱ ቊንስጣ እነርሱን ሮሐ (ሶርያ) ላይ ትቷቸው ወደ በራንጥያ ተመለሰ፡፡ ርሷም ልጇን የክርስትና ትምህርትን አስተማረችው፤ ይቅርታንና ርኅራኄን በክርስቲያን ወገኖች ላይ እንዲያደርግ በልቡናው መልካም ዘርን ትዘራበት ነበር፡፡
ከዚያም ቈስጠንጢኖስ አካለ መጠን ሲያደርስ ወደ አባቱ ሰደደችው፤ አባቱም የጥበቡን ብዛት አይቶ በመደሰት ከበታቹ መስፍን አድርጎት በመሾም በመንግሥቱ ሥራ ላይ ኹሉ ሥልጣንን ሰጥቶታል፤ ከኹለት ዓመት በኋላ አባቱ በማረፉ ቈስጠንጢኖስ መንግሥቱን ኹሉ ተረክቦ የቀና ፍርድን የሚፈርድ ኾነ፤ ከርሱ በፊት የነበሩ ነገሥታት የጫኑባቸውን ጽኑ አገዛዝ ከሰዎች ላይ የሚያስወግድ ኾነ፤ በዚኽ ምክንያት ኹሉም ወደደው፤ ዝናውም በብዙ ሀገሮች ላይ ተሰማለት፡፡
በአንጾኪያ ያሉ ክርስቲያኖችም የቈስጠንጢኖስን ፍርድ መጠንቀቁን፣ ድኻ መጠበቁን እየሰሙ ከከሓዲው ከመክስምያኖስ አገዛዝ እንዲያድናቸው የልብሰ ተክህኖውን ቅዳጅ፣ የመስቀሉን ስባሪ ይልኩለት ነበር፤ ርሱም ስለደረሰባቸው መከራ በእጅጉ እያዘነ እንዴት አድርጎ እንደሚያድናቸው ያስብ ነበር፤ ከዕለታት ባንዳቸው በአደባባይ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ከቀኑ በስድስት ሰዓት ጊዜ ሕብሩ እንደከዋክብት የኾነ መስቀል በጸፍጸፈ ሰማይ ላይ ሲታየው፤ በላዩም በዮናኒ ቋንቋ ኒኮስጣጣን የሚል ጽሑፍ ነበረው፤ ትርጓሜውም በዚኽ ጠላትኽን ድል ታደርጋለኽ ማለት ሲኾን፤ ርሱም የመስቀሉ ብርሃን የፀሓይን ብርሃን ሲሸፍነው አይቶ ተደንቋል፡፡
ይኽነንም ያየውን ለሊቃውንቱ በጠየቃቸው ጊዜ አውስግንዮስ የሚባል ሕጽው በዚኽ መስቀል አምሳል ጠላትኽን ድል ታደርጋለኽ ማለት ነው ብሎ ተረጐመለት፤ መልአኩም ሌሊት በራእይ ታይቶት አስረዳው፤ ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ልቡ ጸናና የወርቅ መስቀልም አሠርቶ በነገሠበት ዘውድ ላይ አደረገው፤ መኳንንቱንና ወታደሮቹን ኹሉ መስቀል አሠርተው በጦር መሣሪያቸው ላይ ያደርጉ ዘንድ አዘዛቸውና እንዳላቸው አደረጉ፡፡
ከዚያም በክርስቲያኖች ጠላት በከሓዲው መክስምያኖስ ላይ ዘመተበት፤ ከዚያም መክስምያኖስ ሰምቶ ጦሩን ይዞ መጣበት፤ በመክስምያኖስ ጦር ላይ ዐድረው ድል ያደርጉ የነበሩ አጋንንት በቈስጠንጢኖስ ጦር ላይ ያለውን ትእምርተ መስቀል ባዩ ጊዜ ተለይተውት በኼዱ ጊዜ ድል ተነሣ፤ ርሱም ከጥቂቶች ጋር ራሱን ለማዳን ወደ ሮሜ ለመሻገር በድልድይ ላይ ሲወጡ ድልድዩ ፈርሶ ከሰራዊቱ ጋር ሰጥሟል፡፡
ከዚያም በድል አድራጊነት ንጉሥ ቈስንጢኖስ ወደ ሮሜ በገባ ጊዜ ካህናቱ ሕዝቡ መብራት ይዘው፤ “መስቀል ኀይልን መስቀል ጽንዕነ መስቀል መዋዔ ጸር” እያሉ እየዘመሩ ተቀበሉት፤ ርሱም እናቱ ቅድስት እሌኒ እያስተማረች ያሳደገችው፤ በኋላም ምእመናን ይልኩለት የነበረው፤ በሰሌዳ ሰማይ ላይ የተመለከተው፤ አኹንም በአንጾኪያ ምእመናን ይዘው የተቀበሉትን አይቶ ትክክለኛውን ሃይማኖት በመረዳት ከሀገሩ ሶልጴጥሮስን አምጥቶ ተጠምቋል፡፡
ከዚያም ዐዋጁን ባዋጅ በመመለስ “አብያተ ጣዖታት ይትዐጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ” (አብያተ ጣዖታት ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ) የሚል ታላቅ ትእዛዝን አዘዘ፤ የጌታችንንም መስቀል እንድታወጣ እናቱ እሌኒን ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፨
ልጇ ቆስጠንጢኖስም በመስቀሉ ኀይል የክርስቲያኖች ጠላት የኾነውን መክስምያኖስን ድል ከነሣ በኋላ በሶል ጴጥሮስ ተጠምቆ ክርስቲያን ኾነ፤ ርሷም ልጄ ክርስቲያን ከኾነ ኢየሩሳሌም ኼጄ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት አሠራለኊ፤ የጌታዬ መስቀልን ከተቀበረበት አስወጣለኊ ብላ ስዕለት ተስላ ነበርና ያ በመፈጸሙ ደስ ተሰኝታ፤ ለልጇ ነገረችው፤ ርሱም በደስታ ብዙዎች ሰራዊትን ስንቅ አስይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፤ በደረሰችም ጊዜ ሱባኤን አድርጋ የመስቀሉ ጠላቶችን በጽኑ እስራት አሰረቻቸው፤ በኋላም አሚኖስና ኪራኮስ የሚባሉ በዕድሜ የጠገቡ ሽማግሌዎችን ብትጠይቃቸው ሊነግሯት ፈቃደኛ አልኾኑምና በጽኑ እስራት ብታስጨንቃቸው፤ ታሪኩን ነገሯት፤ ቦታውንም ጠቈሟት፡፡
ከዚያም በጸሎቷ ላይ ቅዱስ መልአክ ተገልጾላት በዕጣን ጢስ አማካይነት እንደምታገኘው ተረድታ፤ መስከረም ፲፮ ደመራን አስደምራ በእሳት እንዲቃጠል አድርጋ እጅግ ብዙ ዕጣንን ብታስጨምር ጢሱ ወደ ሰማያት ወጥቶ መስቀሉ ካለበት ቦታ ላይ ተተክሎ ሰገደ፤ ርሷም ፈጣሪዋ እግዚአብሔርን በፍጹም ደስታ አመስግና ቊፏሮውን ከመስከረም ፲፯ ዠምሮ እስከ መጋቢት ፲ ድረስ እንዲቈፈር አስደርጋለች፤ በቊፋሮው ወቅትም የፈያታዊ ዘየማንና የፈያታዊ ዘጸጋም መስቀል ቢገኙም ዕውር አላበሩም፣ ሕሙማንን አልፈወሱም፡፡
ከዚያም መጋቢት ፲ ጌታችን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት ቅዱስ መስቀሉ ተገኘ፤ በዚኽ ጊዜ ከሕሙማን ላይ ቢያደርጉት ኹሉንም ፈወሳቸው፣ ዕዉራን በሩ፣ ሙታንም ተነሡ፡፡ ከዚኹም ጋር የተወጋበት ጦሩ፣ የተቸነከረባቸው ቅንዋት ኹሉ ተገኝተዋል፤ ርሷም በፈረሷ ልጓም ላይ የመስቀል ምልክትን አስቀርጻበታለች፡፡
ርሷም ጌታችን ተአምራት በሠራባቸው ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናትን በማሠራት፤ በተለይም በጎልጎታ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን መስከረም ፲፯ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተከብሯልና፡፡ ርሷም ለድኾችና ለጦም አዳሪዎች ብዙ መልካም ነገርን በማድረግ ግንቦት ፱ በሰላም ዐርፋለች፡፡
ስብሃት ለእግዚያብሔር
ምንጭ፡-
- ስንክሳር ዘመስከረም 17
- መጋቤ ሐድስ ሮዳስ ታደሰ