Aug 16, 2011

ጾመ ፍልሰታ


ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጉም ስናነሣ ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ /የተገኘ/ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ ከምድር ከመቃብር መለየት፣ ማረግ፤ ወደ ላይ መውጣት የሚለውን ትርጉም ያመለክታል፡፡ በዚህ መሰረት ጾመ ፍልሰታ በአጠቃላይ የእመቤታችን ድንግል ማርያም የሥጋዋን ከመቃብር መለየትና ወደ ገነት ማረጉን የሚያመለክት ሲሆን ቅድስት ቤተክርስቲያን ምዕመናን እንዲጾሙት ከምታዘው አጽዋም አንዱና ለዓመቱ ደግሞ የመጨረሻው ጾም ነው፡፡

ይህ ጾመ ፍልሰታ በሌላ አጠራሩ ጾመ ማርያምም በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ወቅት በብዛት የሚወሳው /የሚነገረው/ቃለ እግዚአብሔር በአብዛኛው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የተያያዘ በመሆኑና የእርስዋ የሥጋዋ ፍልሰት መታሰቢያ በመሆኑ ጾመ ማርያም ተባለ፡፡ነገር ከስሩ ውኃ ከጥሩ እንዲሉ አበው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ይህንን የእመቤታችንን ጾም ለምን እንደምታከብር ለመዘርዘር እንወዳለን፡፡



እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህች የሰው ልጆች መኖሪያ በሆነችዋ ምድር ከእናትና ከአባቷ ማህፀንና አብራክ ተከፍላ ከተወለደችበት ግዜ አንስቶ እስከ መጨረሻዋ የዕረፍት ዘመን በምድር ላይ ስልሳ አራት ዓመታትን ማለትም ከእናት ከአባቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሰባት ወር፣ በቤተመቅደስ 12ዓመት፣ በቤተ ዮሴፍ 34ዓመት ከሦስት ወር፣ ከጌታ እርገት በኋላ ከወንጌላዊው ዮሐንስ ጋር 14ዓመት ኖራለች፡፡ ከዚህ በኋላ እርሷም የአዳም ዘር ናትና ጥር 21ቀን ዐርፋለች፡፡ አበው"ሞትኪሰ ማርያም ይመስል ከብካበ"እንዳሉት የእመቤታችን እረፍት እንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት መላዕክት በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟት፡፡ እንጂ ቅዱስ ያሬድም"ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ"እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለች፡፡ በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች በማለትም ዘምሯል፡፡ የእመቤታችን ሥጋዋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን አስቀድሞ አባቷ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት ሲናገር "ተንስእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ" አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት በማለት ተንብዮዋል፡፡ መዝ. 131፡8

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ጥር 21ሲሆን እረፍቷና ዕርገቷ ብዙ መንፈሳዊ ተአምራትና አስደናቂ ምስጢር የተገለጠበት በመሆኑ ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር የተባለበትም ምክንያት ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ የእመቤታችን እረፍት በሆነበት እለት አይሁድ በአስከሬኗ ጥፋት ለማድረስ ብዙ ጥረዋል፡፡ እነ ታውፋንያም እጁን በመቆረጥ ተአምር ተደርጎበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ንውጽውጽታ ስለነበር ሐዋርያትም በሀዘን ከጌቴሰማኔ ተመለሱ፡፡ በዚህ ሀዘንም እያሉ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ሲመጣ እመቤታችንን መላዕክት ሲያሳርጓት አየ፡፡ ሰገደላት፣ አመሰገናትም እርሷም ባርካው ተለያዩ፡፡

ለሐዋርያው ቶማስም የእመቤታችንን መቀበር ደቀ መዛሙርት አስረዱት፡፡ ቶማስም ሥጋዋን አስከማይ አላምንም አላቸው፡፡ ሥጋዋን ያሣዩት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቶማስ ነገራቸው፡፡ በዚህም ሥጋዋ ሲያርግ ባለማየታቸው አንድ ቀን እንደሚያሳያቸው ጌታችን ተገልጦ ቃል ገባላቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ከሚያስተምርበት ሀገረ እስያ ወደ ሰማይ ተነጥቆ የእመቤታችን ሥጋ ያለበትን ስፍራ አየ፡፡ ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆይተው ነሐሴ በባተ በመጀመሪያው ቀን በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ፡፡ ነሐሴ14ቀን ሁለት ሱባዔ ሲጨርሱ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጣቸው በጥር ወር የእረፍት ጊዜ ተወስኖ በነበረው ቦታ በጌቴሰማኔ ቀበሯት፡፡ ነሐሴ 16ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋህዳ ተነሥታ እመቤታችንን አዩዋት፡፡ እጆችዋንም ዘርግታ ሐዋርያትንም ባረከቻቸው በእልልታ በደስታ ወደ ሰማይ አረገች፡፡ ሐዋርያትም በልባቸው ደስ አላቸው፡፡

እንግዲህ ከላይ ለማስነበብ እንደሞከርነው ጾመ ፍልሰታ እንደወንዝ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነ ታሪክ ሳይሆን ልብን የሚነካ መንፈሳዊ ታሪክ ነው፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት "አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት"ያለው፡፡ አንተ ያለው ጌታችንን ሲሆን የመቅደስህ ታቦት ያለው ጌታ ለዘለዓለም አድሮባት የኖረባትን እናቱ ድንግል ማርያምን ነው፡፡ ጌታ በገዛ ፈቃዱ ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን እንደተነሣ እርሷም በልጅዋ ቸርነት ከሦስት ቀን በኋላ ከሞት ተነሳች፡፡ ስለዚህም ነው ምዕመናን ነሐሴ አንድ ቀን የምትገባዋን ጾመ ማርያም ሱባዔ ለመያዝ ህጻናቱ ተማሪው የክረምት እረፍት በመሆኑ፣ ሰራተኛው የዓመት ፈቃዱን ወስዶ ሌሊት በሰዓታት፣ ቀን በትርጓሜና በቅዳሴ የሚያሳልፈው፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን "የሚባርኩህን እባርካለሁ፣ የሚረግሙህን እረግማለሁ"እንዳለው፡፡ ዘፍ.12፡3የአብርሃም ዘር የሆነች ድንግል ማርያምን የሚያመሰግን ትውልድ ይባረካል፡፡ ለዚህም ነው እመቤታችንም "ትውልድ ሁሉ ብጽእት ይሉኛል" በማለት የተናገረችው፡፡ ይህ የሱባዔ ወቅትም እመቤታችንን እንደ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደስ ይበልሽ ብለን አመስግነን፣ እንደ ቅዱሳን አባቶች ሰአሊነነ ቅድስት በማለት ለምነን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት ልዩ ወቅት ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር


ምንጭ፦ በመምህር ንዋይ ካሳሁን (የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ)

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።