"ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር የቱ ነው?" በሚል ርእስ ከማኅበረ ቅዱስ ያሬድ ዘጎንደር ድረ ገጽ ያገኝነውን ጽሁፍ ከአንዳንድ የምስል ወድምፅ ማስረጃዎች ጋር በማዋሃድ አቅርበነዋል መልካም ንባብ።
ጥንታውያን ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በመባል የሚጠሩት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሶርያ፣ አርመንና ሕንድ በእምነታቸው (የተዋሕዶን ትምህርተ ሃይማኖት በመጠበቃቸው) አንድ ቢሆኑም በሥርዓተ መዝሙር (ማለትም በመዝሙር ዜማና አቀራረብ) ግን በመጠኑ ይለያያሉ፡፡ ለምሳሴ ግብፃውያን የዜማ መሣሪያዎቻቸው ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከቅዳሴ በፊትና በኋላ በመዘመራችን፣ ሌሊት ማኀሌት በመቆማችን፤ ሥርዓታችን ተመሳሳይ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መዝሙራትን “ኣርቶዶክሳዊ” ነው የምትለው ትምህርተ ሃይማኖትዋን፣ ሥርዓትዋን፣ ታሪኳንና ትውፊትዋን ሲጠብቅ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በግብፃውያን ሥርዓት ከዜማቸውና ከመዝሙር መሣሪያዎቻቸው ውጭ መዘመር አይፈቀድም፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም አንድ መዝሙር ኦርቶዶክሳዊ ነው፣ የቤተ ክርስቲያን ነው: ሊባል የሚችለው በትምህርተ ሃይማኖትዋ፣ በሥርዓትዋ፣ በትውፊትዋ መሠረት፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓት እና ትውፊት የጠበቀ ሲሆን በጉባዔው ሆነ በግል የምንዘምረው፣ አልያም ደግሞ በካሴት አስቀርፀን የምናሳትመው መዝሙር አዕማደ ምሥጢራትን፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ታሪከ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓትዋን መጠበቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ መዝሙሩ “ድንጋዩን ፈንቅሎ ክርስቶስ ተነሥቷል” የሚል ስንኝ ቢኖረው ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የወጣ ይሆናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል እንጂ መቃብሩን ፈንቅሎ መግነዙን ፈትቶ አልነበረምና፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28 በማለዳ የወጣው የእግዚአብሔር መልአክ በመቃብሩ ደጃፍ ላይ የነበረውን ድንጋይ አንከባልሎ እንደተቀመጠበት ይነግረናል፡፡ በእኩለ ሌሊት ድንጋዩን ያንከባለለው መልአኩ እንጂ ጌታችን የተነሣው በታተመው መቃብር ነወ፡፡
ወይም ደግሞ፡- ‹‹በሥላሴ አርአያ የተፈጠረ ሰው እንደ ዱር አበባ ረግፎ ቀሪ ነው›› የሚል ግጥም ቢኖር የዚህ ግጥም መልእከት ከምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ጋር የሚቃረን ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ፈርሶ በስብሶ፣ እንደ ዱር አበባ ወድቆ የሚቀር ሳይሆን በዳግም ምጽዓት እንደገና ታድሶ የሚነሣ ነው፡፡ ይህ ለእንስሳት ሊቀጸል እንጂ ለሰው ልጁ ሊነገር አይገባውም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ልዑል እግዚአብሔርን፣ ቅዱሳንን፣ ንዋያተ ቅድሳትን፣ ወዘተ የምትጠራበት፤ እምነቷንና ፍቅርዋን የሚገልጹ ቃላት አሏት፡፡ እነዚህ ቃላት ዘመን ወለዶች ሳይሆኑ ከጥንት ጀምሮ ቅዱሳን አበው ልመናቸውን፣ ምልጃቸውን፣ ምሥጋናቸውን ያቀረቡባቸው፣ ልጆቻቸውን ያስተማሩባቸው፣ አንድ ገጽ ጽሑፍ ሊገልጣቸው የማይችላቸውን ምሥጢራት በአንድ ቃል የገለጡባቸው ናቸው፡፡ የምንዘምራቸው መዝሙሮች እነዚህን ዕንቁ የሆኑ ቃላት ማፋለስ የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም መልእክቱን ያዛባዋልና፡፡
ለምሳሌ አንድ መዝሙር “ኢየሱስ ጓዴ ነው” የሚል ቃል ሊጠቀም አይችልም፡፡ ይህንን ቃል የተጠቀመ አባት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የለም፡፡ ቃሉ የጌታችንን ክብር የሚያሳንስ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጌታችንን አምላክ፣ አምላከ አማልክት፣ የጌቶች ጌታ፣ የንጉሦች ንጉሥ፣ መድኃኒተ ዓለም፣ ወዘተ… እያለች ትጠራዋለች እንጂ እንደ ሥራ ባልደረባ “ጓዴ” ብላ አትጠራውም፡፡
በአንዳንድ መዝሙራት ላይ ደግሞ ሕዝቡን የበለጠ ለመሳብ ወይንም አንድን ነገር የበለጠ ለመግለጥ እየተባለ ያልተደረገ እንደተደረገ ሆኖ የሚቀርብበት አጋጣሚም አለ፡፡ ለምሳሌ ጌታችን “ከአጥንቱ አንድም አይሠበርም” (ዘጸ.12÷46) የሚለው ቃል ይፈፀም ዘንድ አጥንቱ አልተሠበረም፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የስቅለት መዝሙራት ላይ “አጥንቱ እስኪሠበር ተገረፈ” የሚል ሐረግ ይገኛል፡፡ ይህ ግን ከቅዱሳት መጽሐፍት ትምህርት የወጣ ነው፡፡ ስለ እመቤታችን ሐዘን በሚዘመሩ መዝሙራትም ላይ “በመስቀሉ ሥር ስትወድቅ ስትነሣ እያለቀሰች ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች” በሚል አኳኋን ይቀርባል፡፡ ነገር ግን እመቤታችን አስቀድሞ ስምዖን፡፡ ‹‹በነፍስሺ ሰይፍ ያልፋል›› (ሉቃ.2÷35) በማለት ነግሮአት ስለነበር መከራውን ታውቃለች፡፡ ሐዘንዋ ተስፋ የመቁረጥ ሳይሆን የእናትነት ፍቅርዋን የሚገልጥ ነው፡፡ ስለዚህ የምንዘምረው መዝሙር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይህንንም ለማወቅ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በእምነታቸው በተመሠከረላቸው አባቶችና መምህራን ማሳረም፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ጠንቅቶ መማር፣ መጻሕፍት ቅዱሳትን ማንበብና በእግዚአብሔር ቤት ዘወትር መኖር ዋና መፍትሔዎቹ ናቸው፡፡ የዘማሪት ማርታን ስርዓት የጠበቀ መዝሙርና የተረጋጋ አዘማመርን ከዚህ በታች ይመልከቱ።
ዜማው ያሬዳዊ ሲሆን:- ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 13ዐዐ ዓመታት ያህል ለልዑል እግዚአብሔር ምሥጋናዋን ታቀርብ የነበረበት ዜማ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ በዚህ ዜማ ተጠቅመው አያሌ ቅዱሳን ምሥጋናቸው በልዑል እግዚአብሔር ፊት ቀርቦላቸዋል፡፡ ክብረ ቅዱሳንንና፣ ርስት መንግስተ ሰማያትን ወርሰዋል፡፡ በየጊዜው የተነሡ የቤተ ክርስቲያናችን አበው (እነ አባ ጊዮርጊስ፣ እነ አባ ዘድንግል) ሰዓታትን፣ ማኀሌተ ጽጌን፣ ሰቆቃወ ድንግልን በዚሁ በያሬድ ዜማ ዘመሩት እንጂ ሌላ ዜማ ለመፍጠር አልፈለጉም፡፡ እግዚአብሔር የዘረጋው መንገድ እያለ ለምን ሌላ መንገድ ይፍጠሩ! አሁንም ሆነ ለወደፊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔር በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የሰጣትን ይህንን ዜማ እንደምትጠቀምበት ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ባወጣው ደንብ ምዕ.5/26/1/ሀ ላይ ደንግጓል፡፡ አጽንቷል፡፡ በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ የምንዘምረው መዝሙር ይህን ዜማ የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም፣ ዜማው እግዚአብሔር ወዶ ፈቅዶ የሰጠን እንጂ ቅዱስ ያሬድ በጥበቡ የተፈላስፎ፣ ተራቅቆ፣ ያመጣው አይደለም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድንጠቀምበት፤አባታችን እግዚአብሔርንም እድናመሰግንበት ጠብቃ ያቆየችን ወስናም የሰጠችን ነውና፡፡ የዜማው ሥርዓት፣ ባሕልና የመሣሪያዎቹ ትርጉም ፍፁም ኦርቶዶክሳዊ መልእክት ያለው ነውና፡፡
አንዳንድ ዘማሪያን የመናፍቃኑን ዜማ ስለሚወዱት በግድ ዜማውን እየጐተቱ በከበሮ በማጀብ ያሬዳዊ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ነገር ግን ያሬዳዊ ዜማ ማለት የተጐተተ ዜማ ማለት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉንም ላለመልቀቅ የሚደረግ ጥረት ካልሆነ በቀር የራሳችን አለን፡፡ የራሳችን እያለንም ወደ ጐረቤት መጓዝ አያስፈልግም፡፡ ክርስቲያን የሆንነው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት ተጠምቀን ነው፡፡ ክርስቲያን ለመሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጣነው ሕግዋን ሥርዓትዋን አክብረን እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን ጸጋና በረከት ለማግኘት እንጂ እምነት፣ ሥርዓትና ሕግ ለዋጮች ለመሆን አይደለም፡፡ ስለዚህም ቀድመን የመጣንበትን ምክንያት አንርሳ፡፡ እኛ የምኖረው እግዚአብሔርን በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መሠረት እያገለገልን እንጂ በቤተ ክርስቲያንና በክርስትና ሽፋን የገዛ ፍላጐታችን እያሟላን መሆን የለበትም፡፡ የራሳችን ዜማ ፈጥረን ከካሴቱ ሽፋን ላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ዜማና ሥርዓት የጠበቀ ስላልነው ብቻ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር መሆን አይችልም፡፡
ለማናቸውም ነገር መነሻና መግቢያ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በርእሰ ነገራችን ባሕረ አድማስ ክልል የብዙ ቃላት መሣፈሪያ የሆነ መርከብ አነጋገር ከመመለሻችን አስቀድሞ ለዚህ ጥልቅና ስፉሕ ለሆነው ርእሳችን መርሕ (ትርጓሜ) ልንሰጠው የተገባ ነው፡፡ እንዲህም ከሆነ መዝሙር ምንድን ነው; የሚለውን መጠይቅ ለርእሰ ነገራችን ሐተታዊ ፍሬ ነገር መነሻ በማድረግ መሠረታዊ ትምህርታችንን እንጀምራለን፡፡ መዝሙር የባሕርይ አምላክ ልዑል እግዚአበሔር በሰማይና በምድር የሚመሰገንበት ዐቢይ የጸሎት ክፍል የሆነ ጣዕመ ዜማ ነው፡፡ እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ መዝሙር መልካም ነውና ለአምላካችን መዝሙር ያማረ ነውና እነዚህን ቃላት (መዝ.146:1፡፡ ዘጸ.15:1-22፡፡ ኢሳ.61-5፡፡ ራእ.15:1፡፡ ራእ.5፤6-14፡፡ መዝ.65:1-5) መመልከት ስለ መዝሙር ያስረዳል፡፡
ከዚህም ጋር መዝሙር ማለት ምን ማለት ነው; ያልን እንደሆነ መዝሙር: ዘመረ: አመሰገነ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም ምስጋና: ልመና ወይም መማጸን :ማራራት: ማስደሰት$ መደሰት፣ ማዜም: ማለት ነው፡፡ ከዚሁም ሌላ እግዚአብሔርን በእጽፍ ድርብ ማመስገን ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የእግዚአብሔር ቃል #ኑ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፡፡ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል፡፡ በምሥጋና ወደፊቱ እንድረስ፡፡ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፡፡ እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና ይለናል፡፡ (መዝ.32:1-5፡፡ መዝ.149:1፡፡ መዝ.150:1-6፡፡ መዝ.80:1-3፡፡ ማቴ.26:30፡፡ ማር.14:26፡፡ የሐዋ.16:25፡፡ ቆሳ.3:16-25፡፡ ራእ.14:1-3፡፡ ማቴ.21:9፡፡ ማር.11:9፡፡ ሉቃ.19:36፡38፡፡) መዝሙር ማዜም ማለት ነው ስንልም ዜማ ማለት ራሱ በቀጥታ ሲፈታ ስልት ያለው ጩኸት (ድምፅ ማሰማት) ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዜማ የምስጋና ብቻ ሳይሆን የሐዘን: የልቅሶ: የቀረርቶ: የሽለላ: የፉከራና የደስታ ሁሉ ስሜት መግለጫ ድምፅ ነው (ኢሳ.6:1-5፡፡ ማቴ.26:30) ፡፡ ከዚህ ላይ ግን ዜማ ባልን ጊዜ የቤተ ክርስቲያናችንን የምስጋና መዝሙር ድምፅ ማለታችን ነው፡፡ ለምን ቢሉ ዜማ ራሱን የቻለ ጥሬ ቃል (ነባር) ቢሆንም ዘመረ: አመሰገነ: አዜመ ካለው ቃል ጋር በጠባይና በግብር ይመሣሠላልና ነው፡፡
የዜማ ምልክቶች:- የያሬድ ዜማ በቂና ጥሩ ጥሩ ምሳሌ ያላቸው ብዙ ምልክቶች ያሉት ቢሆንም ለአብነት ያህል ግን ስምንቱን ዐበይት ምልክቶች እናያለን፡፡ እነዚህም ዜማውን ለሚማር ደቀ መዝሙርና ለሚዘምረው ሁሉ በምልክትነት ሲያገለግሉ ምሳሌያቸውንና ምሥጢራቸው ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለኛ የተቀበለውን መከራ የሚያስታውሱ ናቸው፡፡ እነዚህም የኋላ ሊቃውንት ከጨመ
ቸው ከድርስና ከአንብር በስተቀር ዋና ዋናዎቹ የቅ/ያሬድ ምልክቶች ብቻ ሲዘረዘሩ ይህንን ይመስላሉ፡፡
- ይዘት - በአይሁድ ጭፍሮች ለመያዙ (ማቴ.26$50)፣
- ሂደት - ታሥሮ ለመጐተቱ፣
- ጭረት - ለግርፋቱ ሰንበር፣
- ድፋት - አክሊለ ሶክ (የእሾክ አክሊል) ለመድፋቱ
- ደረት - ሲሰቅሉት በመስቀሉ ላይ አንጋለው ከደረቱ ላይ ቆመው እየረገጡት ለመቸንከሩ፣
- ርክርክ - ለደሙ ነጠብጣብና አወራረድ፣ ለችንካሩ ምልክት፣
- ቁጥር - በጦር ተወግቶ ፈጽሞ መሞቱ ለመታወቁ፣ እንዲሁም
- ቅንዓት ደግሞ በቅንዓተ አይሁድ ለመገደሉ፣ ምልክትና ማስታወሻዎች ሲሆኑ ስምንት መሆናቸውም ስምንቱም ማኀበረ አይሁድ ተባብረውና መክረው በብዙ ስቃይ ጌታን ለመገደላቸው ምሣሌ ነው፡፡
እነዚህ ስምንቱ ማኀበረ አይሁድ ማን ማናቸው ቢሉ፡-
- ጸሐፍት ፈሪሣውያን፣
- ሰዱቃውያን፣
- ረበናት (መምህራነ አይሁድ)፣
- መገብተ ምኩራብ (የምኩራብ ሹማምንት)፣
- መላሕቅተ ሕዝብ (የሕዝብ ሽማግሌዎች)፣
- ሊቃነ ካሕናት፣
- ኃጥአንና
- መጸብሓን (ቀራጮች)ናቸው፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን የማኀበር ጸሎት ሲደርስ በጣዕመ ዜማ ወይም በመዝሙር ማመስገንና መጸለይ የተለመደና የተወደደ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲከናወን ለምሥጋናውና ለጸሎቱ ማጐልመሻ ሆነው የሚቀርቡትን ንዋየ ቅድሳትና የጸሎቱ ቅደም ተከተል ሁሉ በቂ ምክንያትና ምሳሌ ያለው ሆኖ መገኘቱ እኛን የኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በጣም ያኮራናል፡፡ ይህንንም ለመረዳት በጸሎተ ማኀሌት ማለት የምስጋና መዝሙር በሚቆምበት ጊዜ የሚፈጸመውን ከልብ መመልከትና ማገናዘብ ይገባናል፡፡
የመዝሙር ወይም የዜማ ጥቅሙ ምንድነው ?
የመዝሙር ወይም የዜማ ጥቅሙ ምንድነው ?
ሀ. መዝሙር እግዚአብሔርን በተመስጦ ለማመስገን ለመቀደስ
ለ. መዝሙር ወደ እግዚአብሔር ልባዊ ጸሎት ወይም ልመናን በማራራት ለማቅረብ
ሐ. መዝሙር ለመማሪያና ለማስተማሪያ ወይም ልብን ለማነፅና ነፍስን ለማስደሰት (መንፈስን ለማደስ)፣ ለምክር፣ ለተግሣጽና ደግሞም ለመጽናትና ለማጽናናት እጅግ አድርጎ ይጠቅማል፡፡ መዝሙር ወይም ዜማ የተጀመረው በአራቱ ሰማያት ማለት በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በኢዮር፣ በራማና በኤረር ያሉ መላእክት እግዚአብሔር ፈጣሪያቸውን ያለ ዕረፍት ሲያመሰግኑት ነው፡፡ ይህንንም ሲያረጋግጥ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፡፡የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር፡፡ ሱራፌልም በእርሱ ዙሪያ ቆመው ነበር፡፡ እያንዳንዱም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልቷል እያሉ ይጮኹ ይዘምሩ ነበር፡፡ የመድረኩም መሠረት ከጯኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፣ ቤቱንም ጪስ ሞላው።›› ይላል (ኢሳ.6፤1-5፡፡ ራእ.4:11)፡፡ ይህም በኪሩቤልና በሱራፌል ማለት በመላእክት የተጀመረው ጣዕመ ዜማ (መዝሙር) በእነሱ አሰሚነት ለሰው ልጆችም ታድሏል፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሥልጣነ እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ የባርነት አገዛዝ ነፃ ባወጣበት ጊዜ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ በደረቅ ምድር ሲያሻግራቸው ሙሴና ተከታዮቹ በተለይም እኀቱ ማርያምና እርሱ እግዚአብሔርን በከበሮ ድምፅ እየታጀቡ በጣዕመ ዜማ አመስግነዋል፡፡ የመዝሙርም በይፋ መጀመር የታወቀው በዚሁ ጊዜ ነው (ዘጸ.15:22)፡፡ ደግሞም ወንጌላዊው ቅ/ዮሐንስ ባየው ራእይ. (14:1-6) ከምድር የተዋጁት አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ወገኖች ማንም ያልዘመረውንና ሊዘምረውም የማይችል ጣዕመ ዜማ ልዩ የሆነ አዲስ መዝሙርን በመድኃኒታችን ዙፋን ፊት በኪሩቤልና በሱራፌል መካከል እንደዘመሩ ይገልጻል፡፡ የመላእክት ጣዕመ ዝማሬ ለሰው ልጆች የታደለ ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ዘወትር ፈጣሪዋን ታመሰግንበታለች፡፡ ይህም መዝሙራችን እስከ አሁን በዓለም ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡ የተገኘውም በኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ አማካይነት ነው፡፡ እኛም አሁን የምንዘምረው መዝሙር የቅ/ያሬድ ዜማ ነው፡፡ የያሬድ የመጀመሪያ ዜማም አርያም ይባላል፡፡ አርያም ማለትም ልዑል፣ ከፍተኛ ማለት ነው፡፡ ቅ/ያሬድ የዜማ መጀመሪያውን አርያም ብሎ የሰየመው በሰማይ ካሉ መላእክት ሰምቶ መዝሙር ስለጀመረ ነው፡፡ ይህም ‹‹ቀዳሚ ዜማ ተሰምዓ በሰማይ›› እያለ ይሄድ እንደነበረ ሊቃውንት ይተርካሉ፡፡
ይህ ታላቅ ሊቅ በመንፈሳዊ ተመስጦ ሰማየ ሰማያት ተነጥቆ ከመላእክት ያገኘው ዜማ ዓይነቱ ሦስት ነው፡፡ እነዚህም ግእዝ፣ ዕዝል፣ አራራይ ይባላሉ፡፡ እነዚህ ሦስቱ የዜማ ስልቶችም ምሣሌና ትርጉም አላቸው፡፡ ይኸውም ግእዝ ማለት ርቱዕ ነው፡፡ ‹‹አብ ርቱዕ ሎቱ ነአኵቶ›› ማለት ‹‹ክብር ምሥጋና ለእርሱ ይሁን›› ነው፡፡ ዕዝል ጽኑዕ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ጽኑዕ መከራ ተቀብሎ አዳምን እንዳዳነው ለማመልከት ነው፡፡ አራራይ ማለትም ጥዑም ማለት ነው፡፡ ጥዑም ሀብተመንፈስ ቅዱስን እንደተጐናጸፍን ለማስረዳት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ታዲያ ተገነጣጥለው አይቀሩም፡፡ ግእዝ ከተሠኘው ዜማ ዕዝልና አራራይ ይወጣሉ፡፡ ይህም በአሐዱ አብ ዜማ ይታወቃል፡፡ ምሥጢሩ ከአብ እምቅድመ ዓለም ወልድ ለመወለዱ መንፈስ ቅዱስ ለመሥረፁ ምሳሌ ነው፡፡ ከዚህም ጋር የንባቡና የድምፁ ቃና አንድ መሆን የሥላሴን አንድነት ሲያስረዳ የዜማው ሦስት ዓይነት መሆን ደግሞ የሦስትነታቸው ምሳሌ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
kalehiwot yasemaln! ejig betam tekami tsihuf hono new yagegnehut. Egziabher ye agelglot zemenachihun yabzalachihu
ReplyDelete