Jan 19, 2012

ቃና ዘገሊላ

ምንጭ ፦ በአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት መማማሪያ ገጽ

‹‹ቃና ዘገሊላ›› ምንድነው?
ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡
የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡

በቃና ዘገሊላ ምን ተፈፀመ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ›› ‹‹የጌታ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ (ዮሐ 2÷1) እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሰርጉ ላይ ታድማ ነበር፡፡ እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ሥርዓት ስላልሆነ፤ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ  ከጌታ ጋር በሰርጉ ታድመዋል፡፡ ይህም መምህርን ጠርቶ ደቀ መዛሙርቱን መተው ሥርዓት ስላልሆነ (ተገቢ ስላልሆነ) ነው፡፡ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በሠመረ ባማረ ሁኔታ እየተከናወነ ሳለ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አስተናባሪዎቹ በጭንቀት ባሕር ሰጥመው ምን እንደሚያደርጉ ግራ በገባቸው በጠበባቸው ጊዜ የችግር ጊዜ ደራሽ የኃዘን ጊዜ አፅናኝ የሆነችው የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል እንደተናገረ በፀጋ የተሞላች ናትና (ሉቃ 1÷28)  ማንም ሳይነግራት የልቦናቸውን ጭንቀት አይታ፣ ጎዶሎአቸውን ተመልክታ ወደ ልጃ_ ወደ ወዳጃ_ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹ወይንኬ አልቦሙ›› ‹‹ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል›› አለችው፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለሊቀ ምርፋቅ (ለአሳዳሪው) እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል አንተ ግን መልካሙን እስከ አሁን አቆይተሃል›› አለው፡፡ ወይኑም በሰው እጅ ያይደለ በሠማያዊው አባት የተዘጋጀ ስለነበር ጣፋጭ እና ልብን የሚያስደስት ነበር፡፡
‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?››
ይህንን የጌታችንን ንግግር ብዙዎች በዘመናችን ሲሣሣቱበት ይታያል ፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ይህንን የተናገረው እናቱን ሊያቃልል ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ይህን አረፍተ ነገር መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተናጠል ስንመለከት ‹‹አንቺ ሴት››  ሴት የሚል ቃል የፆታ መጠሪያ ነውና በፆታዋ አክብሮ ሲጠራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን ከአዳም በተፈጠረች ጊዜ አዳም እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› (ዘፍ 2÷23) በመሆኑም ጌታ አንቺ ሴት ማለቱ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ መንሣቱን ለማጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለውን ዐረፍተ ነገር  የንቀት ስለመሰለን ብቻየዳቦ መልክ የያዘ ድንጋይ፤ ዳቦ ነው እንደማይባልየንቀት ንግግር ነው ልንል አይገባም፡፡  ጌታም እንዲህ ሲል ውኃውን ወይን አድርግላቸው ብትይኝ አላደርግም እልሽ ዘንድ ከአንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ  ቦታ ተጽፎ እንደሚገኘው በዕብራውያን ዘንድ የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ ነው፡፡ለአብነት ይሆን ዘንድ ጥቂት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡-
  • የሰራፕታዋ ሴት 1ነገ 17÷18 ላይ እንደምናገኘው ልጇ በሞተባት ጊዜ ኤልያስን በሐዘን በለቅሶ  እንዲህ ብላ ነበር ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?››  ትወልጃለሽ ብለህ የወለድኩት ልጅ ምን በድዬህ ምንስ አስከፍቼህ ሞተብኝ? ስትል ነው እንጂ አባባሏ የንቀት ወይም የማቃለል አይደለም፡፡
  • በጌርጌሴኖን አንድ አጋንንት ያደረበት ሰው ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› አለው፡፡ እውነት ይህ ቃል የንቀት ይመስላልን? የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ብሎ አምላክነቱን እየመሰከረ ሊያቃልለው ይችላልን? ደግሞስ ላለመጥፋት ፍፁም የሚፈልግ ሰው ሊያድነው ሥልጣን ያለውን  ሊንቅ ይችላልን? አይችልም፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው ምን አጠፋሁ ስለምን ልታጠፋኝ ወደድክ በማለት መፍራት መራዱን ነው፡፡ (ሉቃ 8÷28-29)
ስለሆነም ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለው የንቀት አለመሆኑን ከሁለቱ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን፡፡ እመቤታችን እና ጌታ በንግግር አልተቃረኑም ንግግራቸው የፍቅር ነበር፡፡ ንግግራቸው የመግባባት ስለነበር ነው ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ካላት በኋላ ዘወር ብላ አገልጋዮቹን የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ያለችው፡፡
‹‹ጊዜዬ አልደረሰም››
ጌታ ይህን ቃል የተናገረው ስለ ብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ጊዜዬ አልደረሰም ማለቱ፡-
  • እግዚአብሔር ነገሮችን የሚያከናውንበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ በመሆኑም ይህን ተአምር የምፈፅምበት ጊዜዬ አልደረሰም ሲል ነው፡፡
  • ጋኖቹ ውስጥ የቀረ ወይን ስለነበረ ባለው ላይ አበርክቶ እንጂ ውኃውን ወደ ወይን አልለወጠውም እንዳይሉ ወይኑ ከጋኑ ተንጠፍጥፎ እስኪያልቅ ድረስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡
  • ይሁዳ ከሠርግ ቤት ወጣ ብሎ ነበርና ወደ ሠርግ ቤቱ እሰኪመለስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡ ይሁዳ በቃና የገለጠውን ምስጢር ለእኔ ስላላሣየኝ  ተከፍቼበት ከተአምራቱ ቢያጎድለኝ በሞቱ ገባሁበት፤ ሸጥኩት እንዳይል ምክንያት ለማሳጣት እንዲህ አድርጓል፡፡
  • እውነተኛ የሕይወት ወይን የሆነውን ደሜን የምሠጥበት ጊዜ ገና ነው ሲል፡፡
የድንግል ማርያም አማላጅነት በገሊላ ቃና
ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በሠርግ ቤት ሣለ የወይኑን ማለቅ የማይመለከት ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእናቱን የድንግል ማርያምን አማላጅነት ሊገልጥ ስለወይኑ ማለቅ እስክትነግረው ድረስ አንዳች ነገር አላደረገም፡፡ ኋላ ግን የጭንቀት አማላጅ ድንግል ማርያም ስለ ወይኑ አሰበች ልጇ ወዳጇን ለመነች፡፡ እርሱም የእናቱን ልመና ተቀብሎ ተአምራቱን ፈፀመ፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሣይነግሯት በልብ ያለውን  የምታውቅ የምትመረምር እናት ናትና የሠርጉ አስተናባሪዎች ይሄ ጎደለ ሣይሏት የልቦናቸውን ሐዘን ተመልክታ ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ የጎደላቸውን ሞልታለች፡፡ ያስጨነቃቸውንም አርቃለች፡፡ በችግራቸው ደርሳላቸዋለች፡፡ ታዲያ ሳይነግሯት የልቡናን አይታ ከማለደች ስሟን ጠርተው ለሚለምኗትም እንዴት አብልጣ አታማልድ?
ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷን በረከቷን ያሳድርብን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።