Feb 18, 2012

ጦምን አስመልክቶ የቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ


በጦም ወቅት አንድ ክርስቲያን  በፈቃደኝነት አንድ በጎ ሥራን  ጎን ለጎን ቢፈጽም መልካም ነው፡፡ ወይም ከሰዎች ምስጋናን ወይም አንዳችን ነገር ሽቶ የሚጦም ከሆነ ግን ጦሙ በእግዚአብሔር ዘንድ የማይወደድ ጦም ይሆንበታል፡፡ ማንኛውም በጎ ሥራ ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር የመነጨ  ካልሆነ እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኘው አንችልም፡፡” አንድ ሰው ምንም እንኳ መላ የሕይወት ዘመኑን በትሕርምት ሕይወት መምራት ያለበት ቢሆንም በዚህ በዐቢይ ጦም ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኀጢአቱን  ለካህን ተናዝዞ ለድሆች ምጽዋትን በማድረግ በአግባቡ ሊጦም ይገባዋል፡፡ በእነዚህ አርባ ቀናት ውስጥ ዓመት ሙሉ  የሠራነው ኀጢአታችን ሊወገድልን ይችላልና፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ )

ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ሳይሆን ለሥጋ ጤንነታችን እንዲህ መጠንቀቃችን የሚያስገርም ነው፡፡ እኛ ለራሳችን የተጠነቀቅን መስሎን ደስታን ይፈጥሩልናል የምንላቸውን ምግብም ይሁን መጠጥን አብዝተን እንወስዳለን፡፡ነገር ግን መጨረሻችን ሕማምና ስቃይ ይሆንብናል፡፡ የሥጋን ምቾት የናቁና በጦም በጸሎት እንዲሁም በትሕርምት ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚመሩ ቅዱሳን ግን ሥጋቸውንም ነፍሳቸውም ሕያዋን አድርገው በመልካም ጤንነት ያኖሯቸዋል፡፡ በተድላና በምቾት ይኖር የነበረው ሰውነታችን በሞት ሲያንቀላፋ ከውስጡ ከሚወጣው ክፉ ጠረን የተነሣ ሽቶ በራሱ ላይ እናርከፈክፍበታለን፡፡ ነገር ግን የቅዱሳን ሰውነት በሕይወት ሳሉም ቢሆን በሞት ሥጋቸው መልካምን መዓዛ ያመነጫል፡፡ ይህ እጅግ ድንቅ የሆነ ነገር ነው ፡፡ እኛ ሥጋችንን በመገንባታችን ራሳችንን ስናጠፋ እነርሱ ግን ሥጋቸውን ለነፍሳቸው አስገዝተው በጦም በጸሎት ራሳቸውን ገዝተው በመኖራቸው ሥጋቸውን ያከብሩዋታል፡፡ የነፍሳቸውን መዓዛ በመጠበቃቸው ምክንያት ሥጋቸውን መልካምን መዓዛ እንዲኖራት ያደርጉአታል፡፡
ነፍሳችን ንጽሕናዋን በጦም ካልጠበቀችው በቀር ንጽሕናዋን ማጣቱዋ የማይቀር ነው፡፡ ያለጦም የነፍስን ንጽሕና ጠብቆ መቆየት የማይቻል ነው፡፡ ሥጋም መንፈስ ለሆነችው ነፍሳችን መገዛትና መታዘዝ አይቻላትም፡፡ አእምሮአችን በምድራዊ ነገር ስለሚያዝብን ጸሎታችንም የሰመረ አይሆንልንም፡፡ ሥጋችንም ነፍሳችንን ፍርሃት ውስጥ ትጨምራታለች፡፡ በአእምሮአችን ውስጥም ክፉ አሳቦች ተቀስቅሰው ኅሊናችንን ያሳድፉታል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ጸጋ ከእኛ ትወሰዳለች፡፡ ከዚህም የተነሣ በግልጥ አጋንንት እንደ ፈቀዱት ወደ ኃጢአት ይመሩናል፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጦመ በኋላ ተራበ፡፡ ሰይጣንም ወደ እርሱ ይቀርብ ዘንድ መራቡን ገለጠ፡፡ እንዲህ በማድረግም ጠላታችንን እንዴት ድል እንደምንነሳው በእርሱ ጦም አስተማረን፡፡ ይህ አንድ ጦረኛ ላይ የሚታይ የአሰለጣጠን ስልት ነው፡፡ ለተማሪዎቹ ጠላትን እንዴት ድል መንሳት እንደሚቻል ሊያስተምር ሲፈልግ ፍልሚያን ከጠላቱ ጋር ይገጥማል፡፡ እውነት በሆነው ውጊያም ውስጥ እንዴት ድል መንሳት እንደሚቻል  ጠላቱን ድል በመንሳት ተማሪዎችን ያስተምራቸዋል፡፡ በጌታ ጦምም የሆነው ይህ ነው ፡፡ ጠላት ሰይጣንን ወደ እርሱ ለማቅረብ መራቡን ገለጠ፡፡ ወደ እርሱም በቀረበ ጊዜ እርሱ ብቻ በተካነበት ጥበቡ በመጀመሪያውም በሁለተኛውም በሦስተኛው ፍልሚያ በመሬት ላይ ጥሎ ድል ነሳው፡፡ (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
እየጦምክ ነውን? ጦምህን በሥራ ተግብረህ አሳየኝ፡፡ ድሀ አይተህ እንደሆነ ራራለት፡፡ ወዳጅህ ከብሮ እንደሆነ ቅናት አይሰማህ ፡፡ አፋችን ብቻ አይጡም፤ ዐይናችንም፣ ጆሮአችንም፣ እግራችንም፣ እጃችንም፣ የሰውነት አካላቶቻችን ሁሉ ክፉ ከመሥራት ይጡሙ፡፡ እጆቻችን ከስስት ይጡሙ፤ እግሮቻችን ኀጢአትን ለመሥራት ከመፋጠን ይጡሙ፡፡ ዐይናችም የኀጢአት ሥራዎችን ከመመልከት ይጡሙ፡፡  ጆሮዎቻችንም ከንቱ ንግግሮችንና ሐሜት ከመስማት ይከልከሉ፡፡ አንደበታችንም የስንፍና ንግግርንና የማይገቡ ትችቶችን ከመሰንዘር ይቆጠብ፡፡ ወንድማችንን እያማን ከዓሣና ከእንስሳት ተዋጽኦች መከልከላችም ምን ይረባናል?


0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።