Apr 6, 2012

ሆሣዕና


ሆሣዕና ማለት በእብራይስጥ አሁን አድን ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቱና በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ከደብረ ዘይት ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም በክብር ሲገባ ከሰማይ የመጣ አዳኝና መድኃኒት መሆኑን ለመግለጽ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ደቀ መዛሙርቱ አመስግነውታል። ይህንን ያዩ ሁሉ ልብሳቸውን መንገድ ላይ ሳይቀር እያነጠፉ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ሰማያዊ ንጉሥ መሆኑን እየመሰከሩ በታላቅ አቀባበል ተቀብለውታል። በወላጆቻቸው ጀርባ ላይ ያሉ ህጻናት ሳይቀሩ ሆሣዕና እያሉ ድምጻቸውን ከፍ እያደረጉ ያሰሙ ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት:

ትንቢተ ነቢያትን ለመፈጸም

«እነሆ ንጉስሽ የዋህና ትሁትም ሁኖ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱም ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል»ዘካ 99 ተብሎ የተነገረ ትንቢት ነበርና ይህን ለመፈጸም «በፊታችሁ ወዳለች መንደር ሂዱ፤ በዚያም የታሰረች አህያ ውርንጫም ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ አላቸው»ማቴ 212 አህያዋ ከነውርንጫዋ ነጻነቷን አጥታ የለመለመ ሣር እንዳትበላና የጠራውን ውሃ እንዳትጠጣ የታሰረች ነበረች።
ምሳሌውም የሰው ልጅ በኃጢአት ማዕሰር ታስሮ፣ ነጻነቱን አጥቶ፣ ጸጋው ተገፎ፣ ክብሩ ጐስቁሎ፣ በእግረ አጋንንት ይረገጥ ነበረና «ለታሰሩት መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ ልኮኛል»ኢሳ 611 እንዲል አዳምና ሔዋን ከነልጆቻቸው ከኃጢአት እስራት የሚፈቱበትና ወደ ቀደመ ክብራቸው የሚመለሱበት ጊዜ እንደደረሰ ለማስረዳት ፈትታችሁ አምጡልኝ አላቸው።
ከዚህም በተጨማሪ «…በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል። በምድር የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል…» ብሎ ሥልጣነ ክህነት የሰጣቸው ሐዋርያትና ከእነርሱም በኋላ የሚነሱ ካህናት ሰዎችን ከኃጢአት እስራት እየፈቱ፣ ነጻ እያወጡ ወደ እርሱ እንዲያቀርቡ የተሰጠ ኃላፊነትን ያመላክታል።

ሥርዓተ ነቢያትን በመከተል

በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ቀደምት ነቢያት ከፊታቸው የሚመጣውን ዘመን ለማመላከት የመቅሰፍት፣ የመዓት፣ የመከራ፣ ዘመን ከሆነ ራቁታቸውን ሆነው በፈረስ ላይ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታዩ ነበር። የሰላም የደስታ የምህረትና የቸርነት ዘመን ሲመጣ ነጭ ልብስ ለብሰው በአህያ ላይ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው በአደባባይ ይታዩ ነበር። ጌታችንም ሥርዐተ ነቢያትን በመጠበቅ ሕዝቡም በሚያውቀው ትውፊትና ሥርዓት መሠረት በሰውና በአግዚአብሔር መካከል የነበረው ጸብ የሚቆምበት፣ የእግዚአብሔር ምህረት ለሰው ልጅ የሚሰጥበት፣ ፍቅር አንድነት የሚሰፍንበት ጊዜ መምጣቱን ለመግለጽ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል።
ኢየሩሳሌም ከተማ ከደብረ ዘይት ስትታይ 
በዚህ ሰዓት የፋሲካን በዓል ለማክበር ከየአገሩ የመጡ፣ የዘንባባ ዝንጣፊና የለመለመ ቅጠል በመያዝ ልብሳቸውን በየመንገዱ በማንጠፍ «በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፣ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር» ሉቃ 1938 በክብር ተቀብለውታል። ዘንባባ የሰላም፣ የደስታ፣ የድል አድራጊነት ምልክት ነው። አብርሃም ኮሎዶጎምርን ድል ባደረገ ጊዜ የዘንባባን ዝንጣፊ ይዞ እግዚአብሔርን አመስግኗል። ዮዲት ሆልኒፎሮስን ድል ባደረገች ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዛ ድል አድራጊነቷን ገልጻለች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን ዲያቢሎስን ድል የሚያደርግበት፣ የሰውን ልጅ የሚያድንበት፣ ሰላምን ለዓለም የሚሰጥበት ፍቅር አንድነት የሚታወጅበት ጊዜው እንደቀረበ የሚያሳይ ነበር።

የፈሪሳዊያን ተቃውሞ

ህፃናት ሳይቀሩ ብዛት ያለው ህዝብ ከፊትና ከኋላ ሆኖ ሆሣዕና አያሉ ሲያመሰግኑ ያዩ ፈሪሳዊያን በቅንአት መንፈስ አይናቸው ደም መሰለ። ለራሳቸው ክብር ሲጨነቁ የጌታ ክብር አልታይ አላቸው። ለራሳቸው ክብርና ዝና የሚጨነቁ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር አይታያቸውም። ሰለዚህም እርሱን ለማመስገን አይችሉም። የእነርሱ አለማመስገን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መመስገኑ እንዲቆጡ አደረጋቸው። የሚያመሰግኑትንም ለማስቆም ደቀ መዛሙርትህን ገስጻቸው አሉት። የሰው ልጅ የመጨረሻ ወድቀቱ የእግዚአብሔርን ክብር ሊጋፋ መሞከሩ ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታሰረችውን አህያ ፈታችሁ አምጡልኝ ብሎ እንድትፈታ እንዳደረጋት ሁሉ እኛም ከኀጢያት፣ ከበደል እስራት ተፈተን ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። በንስሐ ወደ እርሱ እንቅረብ። ያን ጊዜ እግዚአብሔር በሕይወታችን ይከብራል። 
ከኃጢአት ማዕሰር ተፈትተን ለእርሱ ክብር እንድንሰጥ ያበቃን ዘንድ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!

1 comments:

  1. This is so wonderful but would you allow us to follow this blog post? keep it up guys, we are proud of you!!! keep promoting orthodox tewahido church in the world....go go go...

    ReplyDelete

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።