Apr 12, 2012

"ኑ በዳዊት ከተማ ዛሬ ምን እየተፈጸመ እንደነበር ተማሩ"


/ ሽመልስ መርጊያ

ሕማሙ ለእግዚእነ (በቅዱስ ኤፍሬም)

ይህን እጅግ የሚያስፈራውን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሕማሙን ታሪክ ለመናገር፣ በከንፈሬም ለመንካት እጅግ እፈራሁ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነም ይህ የሕማሙን ታሪክን መተረክ የሚያሸብር ነው፡፡ በዛሬው ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጥአን ተላልፎ ተሰጠ፡፡ ስለምን ምክንያት ነበር ቅዱስ የሆነው አምላክ እርሱ ያለኃጢአቱ  ለፍርድ ተላልፎ የተሰጠው? አንድም ኃጢአት ሳይሠራ ጌታችን ዛሬ በኃጥአን እጅ  ፍርድን ሊቀበል ተላልፎ ተሰጠ፡፡
ቅረቡ ስለምን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ፍርድን ሊቀበል ተላልፎ እንደተሰጠ እንመርምር፡፡ ስለእኛ አዎን ስለበደለኞች ጌታችን ተላልፎ ተሰጠ፡፡ በዚህ የማይደነቅ ማን ነው? ለእርሱስ ክብርን የማይሰጠው ማን ነው? ባሮቹ በመበደላቸው ጌታቸው ስለእነርሱ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ የገሃነምና የጨለማ ልጆች በጨለማ በቅጽበት ሊያጠፋቸው ኃይሉ ያለውን  ፀሐይን ሊይዙት ወጡ፡፡ ነገር ግን ጌታችን የእነርሱን አንገተ ደንዳናነት ያውቃል፡፡ በእርሱ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ይረዳል ፡፡ ቢሆንም በራሱ ሥልጣን ለበደለኞቹ በትሕትና ራሱን  አሳልፎ ሰጠ፡፡ ስለዚህም የተናቁ ሰዎች እጅግ ንጹሕ የሆነውን ጌታ ሊያስሩት በቁ፡፡ ከመካከላቸውም አንዱ ማንንም እጅግ ጽኑ በሆነና በማይበጠስ ሰንሰለት የሚያስረው ላይና እኛንም ከእስራታችን የፈታ ጌታ ላይ ተሳለቀበት፡ ለራሳቸው ሊሆን የሚገባውን በወይን እርሻቸው ላይ የበቀለውን እሾኽ  ጎንጉነው አክሊል አድርገው በራሱ ላይ አኖሩ፡፡ በተሳልቆምንጉሥ ሆይብለው  ዘበቱበት፡፡

ሕግን የማያውቁ ብሩህና ንጹሕ በሆነው ፊቱ ላይ ምራቃቸውን ተፉበት ፡፡ስለዘህም በእብሪት የፈጸሙትን ተመልክተው በሰማያት ያሉ ሥልጣናትና የመላእክት አለቆች በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፡፡ ጌታን ባሮች ሲሰድቡትና ሲያመናጭቁት፤ ሲያፌዙበት፣ ምራቃቸውን ሲተፉበት፣ በጥፊም ሲመቱት የታገሠውን መታገሥ ሳሰላስል እነሆ ልቡናዬ ለሁለተኛ ጊዜ ሲታወክብኝ፣ እንባንም  ሲያፈስ ተመልከቱ፡፡ እጅግ ጥልቅ የሆነውን፣ ስለእኛ ያለውን ርኅሩኁ፣ ታጋሽና መሐሪ የሆነውን ተወዳጅ ጌታችንን በደንብ አስተውሉ፡፡ በደስታ መፍሰሻ ገነት ታማኝ አገልጋይ ባሪያ ነበረው፡፡ በበደለ ጊዜ ለቅጣት ተላልፎ ተሰጠ፡፡ ነገር ግን ጌታው የባሪያውን ደካማ የሆነችውን ነፍሱን ተመልክቶ ለባሪያው ራራለት ምሕረትም አደረገለት፡፡ ስለዚህም ባሪያው በእርሱ ላይ ይሳለቅበት ዘንድ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡
ሕሊናዬ እጅግ ከመደነቁ የተነሣ ዝም ማለትን ተመኘሁ፡፡ ነገር ግን በዝምታዬ የመድኀኒታችንን ድንቅ ጸጋ ከመናገር መከልከልን ፈራሁ፡፡ እነሆ ስለእኛ የተቀበለውን ሕማም ሳስበው አጥንቶቼ ተነዋወጹብኝ፡፡ ዓለማትን የፈጠረ እርሱ ጌታችን በዛሬው ቀን ፍርድን ይቀበል ዘንድ ከቀያፋ ፊት ቆመ፡፡ ልክ እንደወንጀለኛ ከባሮቹ አንዱ ጌታችንን በጥፊ ጸፋው፡፡ ይህንን ልቡናዬ ባሰበው ጊዜ በፍርሃት ይርዳል፡፡ ባሪያው ተቀምጦአል፡፡ ነገር ግን የእርሱ ጌታ ግን ቆሞአል፡፡ በኃጢአት የተዳደፈው አንዱ አንድም ኃጢአት በሌለበት ላይ ፍርድን ሊያስተላልፍ ተቀምጦአል፡፡ ሰማያትም ተሸበሩ፤ የምድርም መሠረቶች ተነዋወጡ፣ መላእክትና ሊቃነ መላእክት በሽብር ተሞሉ፣ ገብርኤልና ሚካኤል ፊታቸውን በክንፎቻቸው ሸፈኑ፡፡ ባሪያው የጌታውን ፊት በጥፊ ሲጸፋው ሲመለከቱ ዙፋኑን የሚሸከሙት ኪሩቤል በመንኮራኩራቸው ሥር ተሸሸጉ ሱራፌልም በመገረም ክንፎቻቸውን እርስ በእርሳቸው አጣፉ፡፡ ጌታቸው ጽኑ ስቃይን ሲያደርሱበት ሲመለከቱ የምድር መሠረቶችም እንዴት የመሬት መንቀጥቀጥን ይቋቋሙ?
አስተዋልኹኝ እናም ተሸበርኹ እንደገናም በእጅጉ ተገረምኹ፡፡ ፍቅር የተባለውን የጌታዬን መከራ አስተውዬዋለሁና፡፡ ይህን በምናገርበት ጊዜ ውስጣዊው አካሌ እንዴት እንደሚነዋወጥብኝ ትመለከታላችሁን? ምክንያቱም በቸርነቱ ሰዋዊ ባሕርያችንን የፈጠረውን በጥፊ መታው፡፡ ወንድሞች እንፍራ እንጂ ዝም ብለን አንስማ፡፡ እነዚህን ሁሉ ጸዋትኦ መከራዎች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ መዳን ሲል የተቀበላቸው ናቸውና፡፡
አንተ ኃጢአት የተሞላህ ባሪያ ሆይ ስለምን ምክንያት ጌታህን በጥፊ እንደመታኸው ንገረን፡፡ ባሮች ከሚጠፉት ጌቶቻቸው ዘንድ ነጻ ለመውጣት ሲሉ በክርስቶስ ላይ መከራን አጸኑበት፡፡ ነገር ግን እናንተ ጎስቋሎች ሆይ ያለአግባብ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ሁሉን ነጻ የሚያወጣችሁን ገደላችሁት፡፡ እናንተ ስለፈጸማችሁት ጭካኔ ከቀያፋ ዘንድ አንዳች ብድራትን ጠብቃችሁ ይሆን? በእውኑ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያውያን ላይ የሠለጠነ ጌታ እንደሆነ አልተማራችሁምን? እናንተ የሁሉ ፈጣሪ የሆነውን ጌታ ለሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ በዚህም ለዘለዓለም የባሮች ባሪያ ሆናችሁ ትቀራላችሁ፡፡ ከጸጋው ርቃችሁና ተዋርዳችሁ ለዘለዓለም እሳት ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ፡፡ ወንድሞች ሆይ እጅግ የሚደንቀውን፣ የንጉሣችን የክርስቶስን ትሕትና  ተመልከቱ! በባሪያው በጥፊ ተመታ፣ እርሱ ግን በትሕትናና በአክብሮት ስለምን እንደመታው በእርጋታ ጠየቀው፡፡
የባሪያውን ቁጣ ጌታው ታገሠ፡፡ ባሪያው ትዝእርተኛ ነበር፤ ጌታው ግን የዋህ ነበር፡፡ በተቆጣ ሰዓት የሚያውከውንና በእርሱ ላይ የሚታበየውን የሚታገሠው ሰው ማን ነው? ጌታ ሆይ የአንተንስ ፍጹም የሆነ ትዕግሥት በቃላት ሊገልጸው የሚችለው ሰው ማን ነው? በእርሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርሰቶስ የተወደዳችሁና የምትናፈቁ በማፍቀርና እርሱን በመናፈቅ ሆናችሁ ወደዚህ ቅረቡ፡፡ በዳዊት ከተማ ዛሬ ምን እየተፈጸመ እንደነበር ተማሩ፡፡
የሚወደዱና የተመረጡ የአብርሃም ልጆች በዛሬው ዕለት በጌታችን ላይ ምን እየፈጸሙ ነውበዛሬው ዕለት ከበደል ንጹሕ የሆነውን ጌታ ለሞት አሳልፈው ሰጡ፡፡ በበደለኞች እጅ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያለበደሉ በእጨንት ላይ ሰቀሉት፡፡ የእርሱን መከራ በማሰብ ሰውነታችንን በእንባ እንጠበው፡፡ ምክንያቱም በደለኞች የክብርን ንጉሥ ጌታን ለሞት አሳልፈው ሰጥተውታልና፡፡ አንድ ሰው የሚወደውን የእውነተኛ ወዳጁን ሞት ድንገት ቢሰማ በዐይኖቹም ፊት የወዳጁን አስከሬን ቢመለከት ፊቱ በሃዘን ይደምናል፡፡ የፊቱም ብርሃን ይጠቁራል፡፡ እንዲሁ ሰማያውያን፥ አረመኔዎች በመስቀል ላይ ጌታችንን በጭካኔ ሰቅለውት ሲመለከቱ፥ ብሩህ ገጽታቸው ጠፋ፤ ብርሃንን መስጠት ከለከሉ የጌታቸውን ስቃይ መመልከት አልፈቀዱም ራሳቸውን የሃዘን ማቅ አለበሱ፡፡ እንዲሁ ከአብ የሚሰርጸው መንፈስ ቅዱስ የተወደደ የእግዚአብሔር አብ ልጅን መከራ ሲመለከት የቤተ መቅደስን መጋረጃ ለሁለት ሰነጠቀው፡፡ ቤተመቅደሱን ያስጌጡት ጌጦች ድንገት በርግብ አምሳል ተለይተው ወጡ፡፡ የሰማያት ንጉሥ መከራን ከባሮቹ ሲቀበል ተመልክተው ፍጥረታት ሁሉ በፍርሃትና በሽብር ተሞሉ፡፡ ስለመተላለፋችን የተቀበለውን መከራ ማናናቅና በእርሱ ላይም መሳለቅ አይገባንም ፡፡
እኛ ግን ስለእኛ የተቀበለውን መከራና ስቃይ ሰምተን እንስቃለን ራሳችንንም በምድራዊ ደስታ ደስ እናሰኛለን፡፡ ነገር ግን በሰማይ ያለችው ፀሐይ የጌታዋን መከራ ተመልክታ ብርሃኗን በጽልመት ቀየረችው፡፡ ይህን እኛ በተመለከትን ጊዜ አርዓያዋን መከተል አይገባንምን? የሁሉ ጌታ የሆነ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለአንተ ተጨነቀ ተሰቃየ፡፡ አንተ የተዋረድክና የተናቅህ ሰው ግን ጌጠኛ በሆኑ ልብሶች ራስህን ታስጌጣለህ፡፡
የጌታህን መከራ በምትሰማበት ጊዜ ልብህ አይደነግጥምን? ሕሊናህስ አይነዋወጥብህምን? ብቻውን ንጹሕ የሆነ እርሱ ስለአንተ መተላለፍ ለውርደት ሞት ራሱን አሳልፎ ሰጠ ፡፡ አንተ ግን ይህን እንደማይጠቅም ተራ ነገር ቆጠርኸው ፡፡ አእምሮ ያለው የክርስቶስ መንጋ ሁሉ ይህ በእረኛው ላይ የተፈጸመውን በማስተዋል ይመልከት፡፡ ማንም የራሱን ጥቅም አይመልከት፤ ለራሱም አክብሮትን አይሻ፤ ምክንያቱም ፍጹምና ንጹሕ የሆነው እርሱ ስለእኛ ሲል ነውና ይህን ጽኑ መከራ የተቀበለው፡፡ በሚጠፉ ጌጠኛ ልብሶች ራሱን ማንም አያስጊጥ ከንቱ በሆነ ደስታና ምድራዊ መብልና መጠጥ ራሱን ደስ አያሰኝ፡፡ ነገር ግን በትኅርምትና በእውነተኛ አክብሮት ሆኖ ለፈጠረው ጌታ ራሱን ያስገዛ ፡፡አይሁድን የምንመስላቸው አንሁን፡፡ እነርሱ በክፋታቸው የደነደኑ ባለመታዘዛቸው የጸኑ ናቸውና፡፡ እነርሱ የእግዚአብሔርን ጸጋ እና በረከት ባለመቀበል የተቃወሙ ናቸው፡፡
ኃያሉ አምላክ ለአብርሃም ስለገባው ቃል ኪዳን ሲል ወደ እነርሱ በረድኤት ቢቀርብም አልተቀበሉትም፡፡ ከሰማያዊ መናን ይመገቡ ዘንድ ሰጣቸው፡፡ ነገር ግን እቢ አሉ፡፡ የምግብን ጣዕም የሚያበላሸውን የግብጽን ሽንኩርት ተመኙ፡፡ በምድረ በዳ ከድንጋይ ውሃ አፍልቆ አጠጣቸው፤ ነገር ግን እንዲህ ያደረገላቸውን ጌታ በመስቀል ላይ ቸንክረው ሆምጣጣ ወይንን አስጎነጩት፡፡ ወንድሞች ሆይ ፈጣሪያቸውንና ጌታቸውን ለሰቀሉት አይሁድ ደቀመዛሙርት እንዳንሆን እንጠንቀቅ ፡፡ የጌታችንን ሕማምና መከራ በማሰብ እግዚአብሔርን በመፍራት እንመላለስ፡፡ ሁልጊዜ ሕማሙን በሕሊናችን እንሳለው፡፡ ምክንያቱም በመስቀል ላይ መዋሉ ስለእኛ መዳን ሲል ነውና፡፡ ስለእኛ ድህነት በመስቀል ላይ ተቸነከረ፡፡ መከራ የማይስማማው ኃጢአትም ያልተገኘበት ጌታ ስለእኛ ሲል የመስቀል ሞትን ሞተ፡፡
ወንድሞች ሆይ ለዚህ ውለታው ምንን እንመልስለታለን? ለምንፈጽማቸው ተግባራት ሁሉ ጠንቃቆች እንሁን፡፡ እርሱ ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ በክፉ ሥራችን አናስነቅፈው፡፡ ውድ በሆነ ደሙ ንጹሕና ቅዱስ ለሆነው ጌታ የተገዛችሁ አናንት የቤተክርስቲያን ልጆች ሆይ ወደዚህ ቅረቡ፡፡ በእንባ በመሆን የእርሱን ስቃይና ሕማም በሕሊናችን እናሰላስለው፡፡ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በመሆንም እናስበው፡፡ ለራሳችንም እንዲህ እንበል፡- “ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለእኛ በኃጢአት ስለጎሰቆልነው ስትል መራራ ሞትን ተቀበልኽ፡፡
ወንድሞች ሆይ የምትሰሙት ምን እንደሆነ በጥንቃቄ አስተውሉ፡፡ ኃጢአት የሌለበት የኃያሉ የእግዚአብሔር አብ አንድያ ልጅ ስለኃጢአታችን ለሞት ተላልፎ ተሰጠ፡፡ ልቡናችሁን ክፈቱ፡፡ ስለእኛ መተላለፍ ሲል ስለተቀበለውም መከራ በጥልቀት ተማሩ፤ አስከትላችሁም ለራሳችሁ እንዲህ በሉ፡-
እርሱ የእግዚአብሔር በግ የሆነው ክርስቶስ
ፈጣሪያችን በዛሬው እለት ለሞት ተላልፎ ተሰጠ
በዛሬዋ እለት አይሁድ ተሳለቁበት
በዛሬዋ ቀን አይሁድ ሰደቡት፣
በዛሬዋ እለት  ስለእኛ ሲል ፊቱን በጥፊ ተጸፋ፣
በዛሬዋ ቀን  በእርሱ ላይ ዘበቱበት፣
በዛሬዋ እለት አይሁድ በራሱ ላይ የሾኽ አክሊል ደፉበት
በዛሬዋ እለት ስለእኛ በመስቀል ላይ ቸንክረው ሰቀሉት፡፡
ልባችሁ በፍርሃት ይራድ፡፡ ነፍሳችሁም ይህን በማሰብ ትሸበር፡፡ ሁሌም የጌታችሁን መከራና ሕማማት በማሰብ እንባችሁን አፍስሱ፡ሁል ጊዜ የክርስቶስ ሕማሙን የምታስቡ ከሆናችሁ፡፡ እንባችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ መዓዛ እንዳለው መሥዋዕት ይሆንላችኋል፡፡ ነፍሳችሁም እንደ እንቁ ታበራለች፡፡ ሕማሙን ሁል ጊዜ አስቡ፡፡ ሁል ጊዜም እንባችሁ ይፍሰስ፡፡ ስለእኛ መዳን ሲል የተቀበለውን መከራ በማሰብ ሁል ጊዜ እርሱን አመስግኑት፡፡ መከራ መቀበሉ ስለእኛ ጥቅም ነውና፡፡ እንዲህ ሆነን በተገኘን ጊዜ ዓለምን ሊያሳልፍ ሲገለጥ እንባችሁ በክብሩ ዙፋን ፊት ትምክታችሁ ይሆንላችኋል፡፡ ፍቅር የሆነውን የጌታንን መከራ በማሰብ ጽኑ፡፡ የእርሱን መከራ በማሰብ ፈተናዎችን ሁሉ በጽናት ተወጡአቸው፡፡ ከነፍሳችሁ ለጌታ ምስጋናን አቅርቡ ፡፡
በዐይኖቹ ፊት ሰማያዊውን ጌታንና ስቅለቱን ሁል ጊዜ የሚያኖርና የሥጋ ሥራዎች በመስቀሉ ላይ የቸነከራቸው እርሱ ብፁዕ ሰው ነው፡፡ እርሱ ጌታውን መስሎታል፡፡ ይህን መተግበር እግዚአብሔርን የሚያፈቅሩ ባሮች ዓላማና ግብ ነው፡፡ እነርሱም በመልካም ሥራዎቻቸው ጌታቸውን ይመስሉ ዘንድ የሚተጉ ናቸው፡፡ ንጹሕና ቅዱስ የሆነው ጌታ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ እያያችሁ እናንተ በምድራዊ ደስታና ፈንጠዝያ ሕይወታችሁን ማሳለፍን ትወዳላችሁንእናንተ ወራዶች ሆይ በመስቀል ላይ የዋለው ጌታ ለአመጻችሁ ብድራታቸሁን እንዲመልስባችሁ አታውቁምን? አናንተ ጌታችን ስለተቀበላቸው መከራዎች ስትሰሙ እንደ ተራ ነገር ትቆጥራላችሁ ትሳለቁማላችሁ፤ በሚያልፈው ምድራዊ ደስታም ሐሴትን ታደርጋላችሁ፡፡ የሚያስፈራው ሰዓት ይመጣል፡፡ በዛን ሰዓት ያለማቋረጥ ታለቅሳላችሁ፤ ስለሕመማችሁም ጽናት በእሳት ውስጥ ሆናችሁ አብዝታችሁ ትጮኸላችሁ፤ ለጩኸታችሁም መልስ የሚሰጣችሁ ወገን የለም፡፡ ለነፍሳችሁም ምሕረትን ብትናፍቁም አታገኙም፡፡ ጌታ ሆይ ለአንተ እገዛለሁ፡፡ ቸር ለሆንከው ለአንተም ምስጋናን ዘወትር አቀርባለሁ ፡፡ ብቻህን ቅዱስ ወደሆንከውም አንጋጥጣለሁ፡፡ የሰውን ልጅ ሁሉ በምታፈቅረው በአንተ ፊትም በመገዛት እንበረከካለሁ፡፡ አንተንም  አከብርሃለሁ፡፡ ምክንያቱም የአብ አንድያ ልጁ የሆንኸው፣ የፍጥረት ሁሉ ገዢ፣ ኃጢአት የሌለብህ፣ ስለእኔ ስለተናቅሁት ኃጢአተኛ ሰው ስትል፣ ኃጥአን ነፍሳት ከኃጢአት እስራት ነጻ ይወጡ ዘንድ ራስህን ለመስቀል ሞት አሳልፈህ ሰጥሃልና፡፡  ስለዚህ ድንቅ የሆነው ቸርነትህ ጌታሆይ ምን ልክፈልህ!


የሰው ልጆችን ለምታፈቅረው ለአንተ ክብር ይሁን፣ ርኅሩኅ ጌታ ሆይ ለአንተ ክብር ይገባል፣ ስለእኛ መዳን ራስህን ለሞት አሳልፈህ ሰጥተሃልና ለአንተ ክብር ይሆን፣ መተላለፋችን ይቅር ላልከው ጌታ ሆይ ለአንተ ምስጋና ይገባል ፡፡ እኛን ለማዳን ስትል ከሰማየ ሰማያት በመውረድ ወደዚህ ዓለም ለመጣኸው ክብር ይሁን ፡፡ ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ በመንሳት እኛን መስለህ ለተገለጥኸው ለአንተ ውዳሴና አምልኮት ይጋባል፡፡
ትንሣኤያችንን ለአወጅክልን ንጉሣችን፣ በአንተ እንድንታመን ላበቃኸን፣ ወደ ላይ ወደ አባትህ ላረግኸው፣ በታላቅ ክብር በአባትህ ቀኝ በዙፋንህ ላይ ለተቀመጥኸው ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡ በአባትህ ክብር ከቅዱሳን መላእክቶችህ ጋር ዓለምን ለማሳለፍ በአስፈሪ ግርማ ለምትገለጠው፣ የአንተን ቅዱስ የሆነውን ሕማም ባቃለሉት ላይም ልትፈርድ ለምትመጣው ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡
በዚያን ጊዜ በሰማያት ያሉ ሥልጣናት፣ መላእክትና ሊቃነ መላእክት፣ኪሩቤልና ሱራፌል  በአንድነት  በታላቅ ማስደንገጥና ግርማ ስለአንተ ክብር ይገለጣሉ፡፡ የምድር መሠረቶች ሁሉ ይነዋወጣሉ፣ እስትንፋስ በአፍንጫው ያለው ሁሉ ከጌታ ግርማና ማስደንገጥ የተነሣ ይርዳል ይንቀጠቀጣል ፡፡ በዚያን ጊዜ እጆችህ በክንፎቻቸው ይጋርዱኛል ፡፡ ነፍሴንም ከሚያስፈራው እሳት ይጋርዱዋታል፡፡ ከጥርስ ማፏጨት ከጽኑ ጨለማ  ከማያቋርጥ ወዮታ እጆችህ ይታደጉኛል ፡፡ እኔም አንተን በማመስገን እንዲህ ማለት እጀምራለሁ “እኛን ኃጢአተኞችን በብዙ የትሕትና ሥራዎችህ በፍቅር ልታድነን ለወደደኸው ለአንተ ክብር ምስጋና ውዳሴና አምልኮ ይሁን” በማለት አመሰግሃለሁ፡፡
ለዘለዓለሙ አሜን !!

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።