በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሠሮ ለሰይጣን
አግአዞ ለአዳም
ሰላም
እምይእዜሰ
ኮነ
ፍሥሐ ወሰላም።”
ፍሥሐ ወሰላም።”
የጌታችን ትንሳኤ በአበው ዘንድ በምሳሌ የተመሰለ፣ በነቢያት በትንቢትና በምልክት የተነገረ፣ በተስፋ የተጠበቀ የድኅነታችን ታላቅ በር ነው፡፡ የጌታችንን የወንጌል ምሥራች የሰበኩ ሐዋርያትም የጌታን ትንሳኤ በደስታና በጽናት መስበካቸው ትንሳኤው በኃጢአትና በሞት ላይ የተደረገ ታላቅ ድልና የድኅነት የምሥራች በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም የትንሳኤው ምስክሮች ሆነዋል፡፡ /የሐ.ሥራ 2፡32/ ጌታ የተነሳበት ሰንበተ ክርስቲያንም የበዓላት በኩር፣ የዘላለም ሕይወት ቀብድ፣ ዘላለማዊት መባሏ የጌታ ትንሳኤ የምዕመናን የዘላለም ሕይወት ትንሳኤ በኩር በመሆኑ ነው፡፡ /1ኛቆሮ. 15፡20/
በዚህ ጽሑፍ በመጀመሪያ ጌታ ከትንሳኤው ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ከሐዋርያት ጋር እንዴት እንደቆየና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ቀናት በእንዴት ያለ ትውፊት እንደምታሳልፋቸው በአጭሩ ጠቅለል በማድረግ ይቀርባል፡፡ ቀጥሎም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት የሰሩ አበው በእነዚህ ቀናት /ከትንሳኤ እስከ ዕርገት/ ባሉ እሁዶች የቅዳሴ ምንባባት ስለትንሳኤ ያስተላለፏቸውን ትምህርቶች በተረዳነው መጠን ከብዙ በትንሹ እናቀርባለን፡፡
እነዚህ 40 ቀናት የደስታ ቀናት ናቸው፡፡ የጌታን የትንሳኤ የምሰራች ያሰፈሩ ወንጌላውያን፣ በሐዋርያት ትውፊት ላይ የተመሠረተው የቤተ ክርስቲያን አኗኗር ስለነዚህ ቀናት ምን ያስተምሩናል? ከቅዱስ መጻሕፍና ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ስለነዚህ ዕለታት ከምንማራቸው ብዙ ትምህርቶች ጥቂቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1/ የጌታ ትንሳኤ ደስ የሚያሰኝ የምሥራች መሆኑ
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አስከፊውና የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው /1ኛ ቆሮ. 15፡26/ የበደል ፍርዳችን በሞት ፍርድ ተጀምሮ፣ ሞትን በማሰብ በጭንቀትና በፍርሃት በመራራ ሕይወት ኖሮ በመጨረሻ በሞት የሚፈጸም ሆኗልና ሞት የሰው ልጆች የብክነትና የጥፋት መሳሪያ ክፉ ጠላት ነው፡፡ የጌታ ትንሳኤም በዚህ ክፉ ጠላት ላይ የተደረገ ድል ነውና ለክርስቲያኖች ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ይህንንም ሲገልጽ ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፤ «እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፤ ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተከፈለ፡፡» በማለት የጌታ ሥጋዌ በሞቱና በትንሳኤው ሞትን ለመሻር እንደሆነ ተናግሯል /ዕብ. 2፡14-16/፡፡ በጥንት ዘመን ሞት አስከፊ፣ ሁሉም የሚፈራው፣ በዲያብሎስ እጅ የመውደቂያ መንገድ ስለነበር ሙት አካል መንካት እንኳ መርከስ እስዲሆን ድረስ የሚጠሉትና የሚፈሩት ነገር ግን ከጥቂቶች በቀር የማያመልጡት የሕይወት መጥፎ ፍጻሜ ነበር፡፡
ከጌታ ሞትና ትንሳኤ በኋላ ግን ሞት ሃይሉን በማጣት «ክርስቲያኖች የሚረግጡት፣ ጥርሱ የወለቀ፣ ሃይሉ የደከመ ያረጃ አንበሳ» ሆኗል /ቅዱስ አትናቴዎስ/፡፡ ጥንታውያን አበውና ነቢያት በሰቆቃ የተቀበሉት፣ ጌታ በአልዓዛር መቃብር ያለቀሰለት፣ የሰው ዘርን ያጐሰቆለውና ያጠፋው ክፉ ሞት በጌታ ሞትና ትንሳኤ ድል ተደርጓልና፤ ቅዱሳን የሚናፍቁት /ፊሊ. 1፡23/፣ ሰማዕታት ትንሳኤያቸውን ክርስቶስን እየመሰከሩ በድፍረት የሚቀበሉት፣ ጻድቃን በፈቃዳቸው በሕይወታቸው ላይ የሚያውጁት የመንግስተ ሰማያት ማለፊያ /ፋሲካ/ ሆኗል፡፡ ስለነዚህ ምክንያቶች በእውነትም የጌታ ትንሳኤ ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ሃዋርያትም በትንሳኤው መደሰታቸው፣ የስብከታቸው ማዕከል ማድረጋቸው በዚህ የተነሳ ነው፤ «ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው» እንዲል /ዮሐ. 20፡20/፡፡ ጌታም ቀድሞ በትንሳኤው እንደሚደሰቱ እንዲህ ብሎ ነግሯቸው ነበር «እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ ነገር ግን እንደገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም፡፡» /ዮሐ. 16፡22/፡፡
2/ ከትንሳኤ እስከ እርገት ጌታ በመካከላቸው ነበር
በእነዚህ ቀናት ጌታችን ሃዋርያትን እየታያቸውና ከፍርሃታቸው እያጽናናቸው አብሯቸው ቆይቷል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጌታችን ቶማስ ምንም ሳይጠይቀው ቀድሞ የተወጋውን ጐኑንና እጆቹን አሳይቶ «እመን እንጅ የማያምን አትሁን» ማለቱ፣ ምንም እንኳ ከእነርሱ የተለየ ቢመስልም «እጆቹንና ጐኑን ካልዳሰስኩት አላምንም» ሲል መስማቱንና በመካከላቸው መሆኑን ለማሳየት፣ በዚህም ሐዋርያትን ለማስደሰትና ከነበሩበት ፍርሃት ማጽናናት ነው» በማለት ገልጦታል፡፡ መጽሐፍም «ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገር እየነገራቸው፣ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው» ይላል፡፡ /ሐዋ. 1፡3/፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ቀናት ከጌታ ጋር አንድ የሚያደርጓትን ምስጢራት አዘውትራ ትፈጽማለች፡፡ በጥንት ቤተ ክርስቲያን ንዑሰ ክርስቲያኖች ከወጡ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተዘግቶ ነበር ቅዳሴ የሚቀደሰው፡፡ ይህም ቅዳሴ የጌታ የትንሳኤው ምሥጢር በመሆኑ ነው፡፡ ከትንሳኤ በኋላ ጌታ ከሐዋርያት ጋር በተዘጋ ቤት ውስጥ እንደተገናኘ አሁንም በምስጢራቱ ይገኛልና ይህን ለማዘከር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በእነዚህ ቀናት ዘወትር ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ምዕመናንም በሚቻላቸው መጠን ስጋወደሙ አዘውትረው በመቀበል እነደሐዋርያት አብረውት ይቆያሉ፡፡
3/ እነዚህ ቀናት የመብል ቀናት ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የዘላለም ማዕድ ናትና፡፡
ጌታ መንግሥተ ሰማያተን በማዕድ መስሎ ተናግሯታል /ማቴ. 22፡1-14/፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ሥጋዊው ምግብና መጠጥ ባይኖርም የእግዚአብሔርን ፍቅር እየበላን እየጠጣን፣ እግዚአብሔርን በማወቅ እየረካን፣ ራሱ እግዚአብሔር ምግብና መጠጥ ሆኖን እንኖራለንና በርግጥም መንግሥተ ሰማያት ራሷ ማዕድ ናት፡፡
በእነዚህ ቀናት ሰንበታት የሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት በመብል ላይ ያተኩራሉ፡፡ ጌታም ከትንሳኤው በኋላ ከሐዋርያት ጋር ደጋግሞ ሲበላ ታይቷል።
በእነዚህ ቀናት መጾም መስገድም በቤተ ክርስቲያን ስርዓት አይፈቀድም፡፡ በመሰረቱ ትንሳኤ የሥጋም የነፍስም ደስታ ስለሆነ በእነዚህ ቀናት ሁለቱም ይደሰቱ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ጾምን ከልክላለች፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት እንደፈለጋችሁ እየበላችሁ ኃጢኣት ሰሩ ማለት አይደለም፡፡ ምንጊዜም ግማሽ እውነት ሙሉ እውነት አይሆንም፤ እንዲያውም ግማሽ እውነት ብቻውን ውሸትም ሊሆን ይችላል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በእነዚህ ቀናት የሥጋ ምግብን ብቻ ሳይሆን የነፍስ ምግብንም በብዛት ታቀርባለች፡፡ በየቀኑ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ቃለ እግዚአብሔርን እንድንመገብ ታዛለች፡፡ የሥጋን ምግብ ተቀብለን ነፍሳችንን ግን ካስራብናት ግማሽ እውነት ነውና ውሸት ሆኖ ችግር ውስጥ ይከተናል፡፡
4/ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የምንጠብቅባቸው ቀናት ናቸው
በእነዚህ ቀናት እንዳንጾምና እንዳንሰግድ መከልከሉ አንዱ ምክንያት ጸጋ እግዚአብሔርን እንድናስብ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ከዓመቱ አብዛኞቹ ቀናት የጾም ቀናት መሆናቸው እውነት ነው፡፡ ነገር ግን አብዝቶ መጾምና መስገድ ለክርስቲያን አስፈላጊ ቢሆንም የድኅነት መጠበቂያ እንጅ የድህነት ምንም አይደለም፡፡ ጾምና ስግደትም ቢሆን ያለ ጸጋ እግዚአብሔር አጋዥነት አይሆንም፡፡ /ዮሐ. 15፡5/
አንዳንዶቻችን በእነዚህ ቀናት ጾምና ስግደት ስለሌለ እንቸገራለን፤ ቀናቱንም ከመደሰት ይልቅ የምንጠላቸው፤ ከመናፈቅ ይልቅ እስከሚያልቁ የምንጓጓላቸው ይሆናሉ፡፡
ይህም በእነዚህ ቀናት ጸጋ እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ብሎ ካለማመንና ይህም እንዲሆን ካለመጸለይ የተነሳ የሚመጣ ነው፡፡ ጾምና ስግደት /ትህርምት/ ንጽሕናን ለመጠበቅ አስፈላጊ ቢሆንም ያለነዚህ ነገሮች ጸጋ እግዚአብሔር ሰውን በንጽሕና መጠበቅ ይቻለዋልን? ብሎ መጠራጠር ግን በራስ ጽድቅ መተማመን ነውና ኃጢኣት ነው፡፡ ስለዚህ በረቂቅ የመንፈስ ቅዱስ ጥበብ የምትመራ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ችግራችንን የምንመረምርበት ወቅት ይሆነን ዘንድ እነዚህን ቀናት አዘጋጅታልናለች፡፡
ምንም እንኳን ከብዙ በትንሹ ጠቅለል አድርገን ያየናቸው ቢሆንም እያንዳንዶቹ እሁዶች የራሳቸው መልዕክት ስላላቸው በአጭሩ እንደሚከተለው እናቀርባለን፤
1/ የትንሳኤ እሁድ
ምንባባት፡- 1ኛ ቆሮ. 15፡20-47
2ኛ ጴጥ. 1፡1-13
3ኛ የሐ. ሥራ. 2፡22-37
ምስባክ፡- እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት
ሐሴትንም እናድርግ በርሷም ደስ ይበለን
አቤቱ እባክህ አሁን አድን
ወንጌል፡- ዮሐ. 20፡1-19
መልዕክት
የትንሳኤ መልዕክት የድኅነት ደስታ ነው፡፡ ሰው የሚደሰተው በድኅነት ነው፡፡ ስለዚህም ምስባኩ ድኅነትን ደስታንና ይህችን የትንሳኤ ዕለት አጣምሯቸዋል፡፡ እመቤታችንም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ሐሴት አደርጋለሁ /ሉቃ. 1፡47/ ማለቷ ይህንኑ ያሳያል፡፡ የመጀመሪያውን የጥፋት የሞት የፍርድ ሃዘን ቀጸሜ የሰማች ሄዋን ናትና፤ የጌታን የትንሳኤ ደስታም ቀድማ ማርያም መግደላዊት መስማቷን ወንጌሉ ይነግረናል፡፡ ሁሉም ምንባባት በትንሳኤ ያገኘነውን ድህነትና በዚህም የሚጠብቀንን ዘላለማዊ ደስታ በተለያየ መንገድ የሚገልጡ ናቸው፡፡
2/ ዳግም ትንሳኤ
ምንባባት፡- 1ኛ ቆሮ. 15፡1-20
2ኛ ዮሐ 1፡1-ጳጉሜ
ዮሐ. ሥራ 23፡1-10
ምንባባት፡- እግዚአብሔር ይነሳ ጠላቶቹም ይበተኑ
የሚጠሉትም ከፊቱ ይሸሹ
ጢስ እንደሚበን እንዲሁ ይሁኑ
ወንጌል፡- ዮሐ. 20፡19 - ፍጻሜ
መልዕክት
የጌታ ትንሳኤ ድል ነው፡፡ ጌታችን በትንሳኤው ሞትንና ዲያብሎስን ድል አድርጓል፡፡ የሰው ዘር ሁሉ በዚህ ድኅነት እንዳይጠቀም የሚያደርገው በጌታ ትንሳኤ አለማመኑ ነውና ጌታ በትንሳኤው ድል እያደረጋቸው ያሉት ጠላቶቹ ጥርጥርና ተጠራጣሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ዕለት የሚነበቡት ምንባባት በዚህ ይተባበራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጌታ መነሳቱን፣ ለሐዋርያትና ለርሱ ለብዙዎችም መታየቱን ከገለጠ በኋላ በትንሳኤ የማያምኑ ግን፣ የክርስትናን ወንጌል ከንቱ የሚያደርጉ፣ ለሆዳቸው የሚኖሩ፣ ምስኪኖች ይላቸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በበኩሉ እንደታማኝ ሐዋርያነቱ የህይወትን ቃል ማየቱን፣ አካሮ መብላቱን መጠጣቱን፣ መዳሰሱን ተናግሮ ደስታችን ከእርሱ ጋር ይፈጸም ዘንድ በትንሳኤ እንድናምን «ሕይወት ተገለጠ» ብሎ ይመሰክራል፡፡ በሐዋርያት ሥራም በትንሳኤ ሙታን ምክንያት በፈሪሳውያንና በስዱቃውያን መካከል መከፋፈል መሆኑን ያሳያል፡፡ ወንጌሉ በበኩሉ ቶማስ መጠራጠሩንና ጌታ ጐኑንና እጆችን አሳይቶ እንዳሳመነው፣ ነገር ግን «ያመንክ እንጂ ያላመንከ አትሁን» ብሎ እንደገለጸው ያስረዳል፡፡ ምስባኩም ጠቅለል አድርጐ የጌታ የትንሳኤው ጠላቶች እንደሚበተኑ፣ የጌታን ትንሳኤ የሚጠራጠሩ እንደሚጠፉ ይናገራል፡፡ በአጠቃላይ የዚህ እሁድ መልዕክት «የጌታን ትንሳኤ ያመኑ እንደሚድኑና ሐሴት እንደሚያደርጉ ያላመኑ ግን ጠላቶች ናቸውና እንደሚጠፉ» ያሳያል፡፡
3/ ሦስተኛ እሁድ
ምንባባት፡- 2ኛ ቆሮ. 5፡11-ፍጻሜ
2ኛ ጴጥ. 3፡14- ፍጻሜ
ዮሐ. ሥራ 21፡31- ፍጻሜ
ምንባባት፡- እግዚአብሔር አሁን እነሳአሁ ይላል
መድኃኒት አደርጋለሁ በላዩም እገለጣለሁ
የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው፡፡
ወንጌል፡- ሉቃ. 24፡13-33
መልዕክት
በዚህ እሁድ የሚታሰቡት የኤማሁስ መንገደኞች ናቸው፡፡ ጌታ በተነሳበት ዕለት ስለሞቱ እያወሩ እየተጨነቁ ሲሄዱ ቀርቦ እንደጠየቃቸውና እነርሱም ሳያውቁት በኢየሩሳሌም ስለሆነው ነገር እንደነገሩት፣ ጌታ በመሞቱም «እስራኤልን ይበዣል ያልነው እርሱ ነበር» በማለት ተስፋቸው እንደጠፋ እንደነገሩት፣ ጌታችንም መጻሕፍትን ተርጉሞ ክርስቶስ ሊሞትና በሦስተኛው ቀን ሊነሳ እንደሚገባው እንዳስረዳቸው፣ ህብስቱን ሲቆርስም እርሱ መሆኑን እንዳወቁትና ከመካከላቸው እንደተሰወረ ያስረዳል፡፡ የዚህ እሁድ ትኩረት ቅዱሳት መጻሕፍት የጌታ የትንሳኤው ምስክሮች መሆናቸውን ማሳየት ነው፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ቅዱስ ጳውሎስ ለእግዘብሔር የሚኖርና ለማንም ሳይል ስለ እግዚአብሔር ሲል የሚሰብክ መሆኑን ተናግሮ ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲህ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በበኩሉ ለድኅነታችን እንድንጠነቀቅ በመምከር አንዳንዶች የቅዱስ ጳውሎስን ጨምሮ ብዙ መጻሕፍትንም ቢያጣምሟቸውም በትክክል ለተረዳቸው ግን መጻሕፍት የጌታ የትንሳኤው ምስክሮች፣ የድህነት ቃላት መሆናቸውን ይናገራል፡፡ የሐዋርያት ሥራው ታሪክም ቅዱስ ጳውሎስ በአይሁድ እጅ የተቀበለውን መከራ በማሳየት ታመኝነቱን ያረጋግጣል፡፡ ሁሉንም ጠቅለል አድርጐ የዕለቱ ምስባክ እግዚአብሔር መነሳቱን መድኃኒትም ማድረጉን፣ በትንሳኤው ለአለም ሁሉ መድኃኒትነቱ መገለጡን፣ የእግዚአብሔር ቃላት መጻሕፍትም ንጹሐን ምስክሮቹ መሆናቸውን ይናገራል፡፡
ከወንጌሉ ታሪክ እንደምንማረው መጻሕፍት ከእውነተኛው ምንጭ ከክርስቶስ ስንማራቸው ልቦናን እስከማቃጠል ደርሰው ጽኑ ምስክሮች ቢሆኑም ጌታ ህብስቱን ቆርሶ እስኪሰጣቸው ድረስ ግን አላወቁትም ነበር፡፡ ይህም መጻሕፍት የጌታን ትንሳኤና ሕማማት ቢገልጡም ይህ መገለጥ ፍጹም የሚሆነው ግን በሥጋወደሙ መሆኑን ያሳያል፤ በሥጋወደሙ የጌታን ሞትና ትንሳኤ በተግባር እንመሰክራለንና፡፡
4/ አራተኛ እሁድ
ምንባባት፡- ቆላ. 3፡1- ፍጻሜ
1ኛ ጴጥ. 3፡15- ፍጻሜ
የሐ. ሥራ. 11፡1-19
ምስባክ፡- እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም
እግዚአብሔር ደግፎኛልና ነቃሁ
ከሚከብቡኝ ከአእላፍ ሕዝብ አልፈራም፡፡
ወንጌል፡- ሉቃ. 24፡33-45
መልዕክት
ክርስትና ትንሳኤ ልቦና፣ ዕርገተ ልቦና ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ሕይወታችሁ ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሯል» በማለት የክርስቲኖች ሕይወት ሰማያዊ መሆኑን ከገለጠ በኋላ ሁሉም በየበኩሉ ይህን ሕይወቱን እንዲኖር ይመክራል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም «በበጐ ህሊና» እንድንኖር ይመክርና ስለዚህ ስንል መከራ ብንቀበል ከክርቶስ ጋር እንደምንከብር ይናገራል፡፡ የሐዋርያት ስራም አህዛብን እግዚአብሔር መቀበሉንና በዚህም ከአይሁድ የመጡ ክርስቲያኖች መደሰታቸውን ያሳያል፤ ይህም በጐ ህሊና ነውና፡፡ ወንጌሉም የሚገለጠው ሐዋርያትና አርድእት በነበሩበት ጌታ መታየቱንና በዚያም የሆነውን ደስታ ያበስራል፡፡ የሁሉም ሃሳቦች ማጠቃለያ ከምስባኩ ይገኛል፡፡ ጌታ መሞቱን፣ መነሳቱን በዚህም ለሰማያዊ ህይወት፣ ለበጐ ህሊና የሚሆኑ አእላፍ ምዕመናንን «በትንሳኤ ልቦና» ማስነሳቱን፣ ይህም የቅድስት ሥላሴ ፈቃድ ስለሆነ የጸና መሆኑን ይገናራል፡፡
5/ አምስተኛ እሁድ
ምንባባቱ፡- ሮሜ. 4፡14
ራዕይ. 20፡1- ፍጻሜ
የሐ. ሥራ. 10፡39-44
ምስባክ፡- በሉ እጅግም ጠገቡ
ምኞታቸውንም ሰጣቸው
ከወደዱትም አላሳጣቸውም
ወንጌል፡- ዮሐ. 21፡1-15
መልዕክት
ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን የወንጌል ክፍል የጻፈው ወንጌልን ከፈጸመ በኋላ ነው፡፡ ይህም የጥብርያዶስ ባህር ማዕድ በሊቃውንት ትርጓሜ ከዚህ ዓለም በኋላ ጌታ ከምዕመናን ጋር ከሚያደርገው ዘላለማዊ ማዕድ ጋር እንዲያያዝ አድርጐታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በተዘዋዋሪ መንገድ ከህግ በላይ የሆነውን ሰማያዊውን ህይወት በአብርሃም የተስፋ ቃል መቀበላችንን ሲገልጽ ጌታንም በዳግም ምጽአት የሚፈርድ መሆኑን ገልጧል፡፡ በራዕይ ዮሐንስም ጌታ በህያዋንና በሙታን እንደሚፈርድና ለዘላለም የሚሆን ክብርን ለቅዱሳን እንደሚሰጥ፣ ይገልጣል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ምድር ላይ እግዚአብሔርን እንቀምሰዋለን እንጅ አንጠግበውም፤ በዘላለም ህይወት ግን እንጠግበዋለን፤ ከወደድነውም አያሳጣንም፤ ምኞታችን መንግሥተ ሰማያትንም ይሰጠናል፤ እርሷም ዘላለማዊት ማዕድ ናት፡፡ ሐዋርያት ያጠመዷቸውን አሳዎች የያዘው መረብም አለመቀደዱ መንግሥተ ሰማያት ሰላም ያለባት፣ ለሁሉም የምትበቃ መሆኗን ያሳያል፤ «ጌታ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ» ያለው ይህንኑ ነው፡፡
6/ ስድስተኛ እሁድ
ምንባባት፡- ሮሜ. 6፡1-15
1ኛ ጴጥ. 4፡4-12
የሐ. ሥራ. 23፡15-22
ምስባክ፡- መዝ. 16፡16 የናሱን ደጆች ሰብሯልና
የብረቱንም መወርወሪያ ቆርጧልና
ከበደል ጐዳናቸው ተቀበላቸው፡፡
ወንጌል፡- ዮሐ. 21፡15- ፍጻሜ
መልዕክት
በጌታችን ሞትና ትንሳኤ ድኅነትን አግኝተናል፡፡ ይህንንም ሞትና ትንሳኤ በጥምቀት መካፈላችንን ቅዱስ ጳውሎስ በዕለቱ ምንባብ ይናገራል፡፡ ትንሳኤውን መካፈላችንም አሁን በትንሳኤ ልቦና ከኃጢአት በመራቅ በኋላም በመጨረሻ ትንሳኤ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የጥምቀት ልጆች ኃጢአትን ይሰሩ ዘንድ እንደማይገባቸው ይናገራል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን የትንሳኤ ሕይወት እንኖር ዘንድ፣ በፍቅርም የኃጢአታችን ብዛት ይሸፍናልና እንዋደድ ዘንድ ይመክረናል፡፡ የዕለቱ የወንጌል ምንባብም ጌታ በትንሳኤው ምሽት ለሐዋርያት ሐጢአትን ይቅር የማለት ስልጣን መስጠቱንና በዚህም የጌታ የትንሳኤው ኃይል የኀጢአት ሥርየትና ትንሳኤ ልቦና ሆኖ መሰጠቱን ያሳየናል፡፡ በዚህም ቅዱስ ጴጥሮስን ከክህደት በመመለስና «መሞት እንኳ ቢያስፈልገኝ ከአንተ ጋር እሞታለሁ» ያለው ቃል በትንሳኤ ልቦና ምዕመናንን በመጠበቅ፣ በኋላም በሰማዕትነት እንደሚያገኘው አመልክቶታል፡፡ ምስባኩም የሞትና የኃጢአት ደጆች መሰበራቸውንና፣ ዓመጻና ኃጢአትን በትንሳኤው ማሳደዱን በትንሳኤው ያመኑትንም ከበደል ጐዳና አውጥቶ ወደ ትንሳኤ ልቦና እንደመለሳቸው ይገልጣል፡፡ በአጠቃላይ የዕለቱ ምንባባት መልእክታቸው ይህ ነው፤ በትንሳኤ ዘጉባኤ ተነስተን በመንግስት ሰማያት ከጌታ ጋር እስክንኖር ድረስ በዚህ ምድር ላይ ትንሳኤ ልቦና ቀርቶልናል፤ ትንሳኤ ልባናም ከኃጢአት በመራቅ ልቦናን ሰማያዊ አድርጐ መኖር ነው፡፡ ድቀተ ልቦና /የልቦና መውደቅ/ በኃጢኣት መኖር እንደሆነ ሁሉ፣ ትንሳኤ ልቦና /የልቦና ትንሳኤ/ ከኃጢአት ርቆ በንጽሕና መኖር ነውና፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ትንሳኤ ልቦናን ያድለን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።