May 16, 2012

በሩቅ ምሥራቅ የሚገኙ “የኢ/ኦ/ተ ምእመናን ጉባኤ” ለቅዱስ ሲኖዶስ መልእክት ጻፈ

(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 8/2004 .)በሩቅ ምሥራቅ የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ጉባኤየተባለና በትምህርትና በሥራ በሩቅ ምሥራቅ በዝርወት ተበትነው ባሉ ምእመናን ያቋቋሙት ጉባኤ ለቅዱስ ሲኖዶስ መልእክት ላከ፤ በቀሲስ / መስፍን ተገን ላይ የተፈፀመውን ሕገ ወጥ ተግባር ተቃወመ።
ሐዋርያዊትና ጥንታዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱሳን  ልጆቿ  የሃይማኖት  ጽናትና  ተጋድሎ  ዶግማዋ  ሥርዓቷና  ትውፊቷ  ተጠብቆ  ያልተበረዘ  ትምህርተ ሃይማኖትዋ  ከትውልድ  ወደ  ትውልድ  እየተሸጋገረ  ያለንበት  ዘመን  ደርሶአል::  ቅድስት  ቤተ  ክርስቲያናችን ምእመናንን  በፈሪሃ  እግዚአብሔር  በሃይማኖት  ጠብቃ  ለመንግሥቱ  ወራሾች  እንዲሆኑ  ከምታደርገው  ሰማያዊ ተልእኮዋ  በተጨማሪ  ለሀገር  ሉዓላዊነት  መከበር  ለሕዝቦች  አንድነት  ተከባብሮ  የመኖር  ባህል  መሰረት  ናት:: ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ፍትሕና አስተዳድር የዕውቀት ምንጭ ሁና ማገልገልዋም የማይዘነጋ ሐቅ ነውያለው መግለጫውቅድስት  ቤተ  ክርስቲያናችን  በዘመኑ  ሁሉ  መከራና  ፈተና  ያልተለያት  ቢሆንም  መሰረትዋና  ጉልላትዋ በሆነው  በጌታችንና  በመድኃኒታችን  በኢየሱስ  ክርስቶስ  ኃይል  ሁሉንም  አልፋ  እነሆ  አሁንም  ለብዙዎች  ተስፋ መጠጊያና ብቸኛ መጽናኛ በመሆን ከክርስቶስ የተሰጣትን አደራ በመፈጸም ላይ ትገኛለች:: አንዱ ፈተና ስታልፍ ሌላ  ፈተና  እየተደቀነባት እዚህ  የደረሰችው  አማናዊቷ  ቤተ  ክርስቲያን  ወአናቅጸ  ሲኦል  ኢይኄይልዋ  ነውና  እስከ ዓለም ፍጻሜ በጠላት ዲያብሎስ የሚደርሰውን ፈተና ሁሉ በአሸናፊነት እንደምትወጣው የታመነመሆኑን ያስረግጣል።

በዘመናችንም  ቤተ ክርስቲያን  ከውስጥና  ከውጪ  በሚነሳባት  ፈተና  ምክንያት  ሰማያዊ  የሆነውን ዓላማዋን  የሚፈታተንና  ልጆችዋንም  የሚያሳዝን  ተደጋጋሚ  መከራ  እየደረሰባት  ይገኛል::  በተለይም  በአንድነቷ ላይ የተነጣጠረውን አደጋ ተጠቃሽ ነው:: እኔ የእገሌ ወገን እኔ የነእገሌ ነኝ በሚል ሥጋዊ መለያየትና መንፈሳዊያን ሳይሆኑም መንፈሳዊያን መስለው በገቡ በውስጣቸው ግን ከዚች ዓለም ለሚገኝ ረብ ጥቅም ፍለጋ ከሚዞሩ ደግሞም ራሳቸውን  ክደው  ሰውን  ከሚያስክዱ  ከውሸተኞች  አገልጋዮች  በኩል  የመጣውን  መከራ  ሰላምዋንና  አንድነትዋን ከማናጋት አልፎ ንጹሕ የሆነውን ያልተከለሰውን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዋ ለትውልድ እንዳይተላለፍ መሰናክልእንደሆኑባት፤ዕንቊ የሆኑ  የሊቃውንቶችዋ  መፍለቂያ  በመሆን  ለህልውናዋና  ከሐዋርያት  አበው  ለተረከብነው ትውፊታዊ  ክርስቲያናዊ  ሕይወት  መሰረት  በሆኑ  ገዳማትና
አብነት  ትምህርት  ቤቶች  የተደቀነው  አደጋም  በጣም አሳሳቢ ደረጃእንደደረሰ የደብረ አሰቦትና ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳማት የደረሰው ቃጠሎና በልማት ሰበብ በታላቁ የብሕትውና ቦታ በዋልድባ ገዳም የተጋረጠው አደጋ ከጠቀሰ በኋላ ይህምበመሠረታዊ  የቤተ  ክርስቲያናችን  ህልውና  ጦርነት  እንደተከፈተብንያመለክታል፤ይኼም  እግዚአብሔርን  ብቻ  በመሻት የሚደርገውን የምንኩስናና የብሕትውና ኑሮ ወደ ከተማዊነትና ዓለማዊነት ለማሸጋገር የሚደረግው ሰይጣናዊ ሩጫ ነው::  መንግሥት  ሀገርን  ለመምራት  በሚከተለው  ፖሊሲና  የአካሄድ  ፍልስፍናም  በቤተ  ክርስቲያን  ላይ  ጫናና ተጽዕኖ ከመፍጠሩ በላይ ዘመኑን በመዋጀት የቤተ ክርስቲያን አካላት በሃይማኖታዊ መንገድ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ምንም እንዳልተፈጠረ በቸልተኝነት እንዲታለፍ መፈለጉንም አንድ ሌላ የንዝህላልነትና የግድየሌሽነት አባዜ እንደተጻናወተብን የሚያሳይ ነውብሏል።
በነዚህምክንያቶችና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ዕለት ዕለት ከምንሰማቸው አሳዛኝ ሁኔታዎች ተነስተን በሩቅ ምሥራቅ ባሉት ስድስት ሀገራት የምንገኝ ምእመናንና ምእመናት በችግሮቹ መንሥዔዎችና መፍትሔዎቻቸው ላይ እግዚአብሔር እንደፈቀደልን መጠን ተወያይተናል:: በሚፈጠሩ ችግሮችም ምእመናንን ለማጽናናትና አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ደካማ መሆናቸውንና ከዚህም በተጨማሪ ችግሩ እንደ ችግር ተወስዶ ከጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ተገቢ ትኩረት አለመሰጠቱ አሳዝኖናል:: ከሃገራችን ወጥተን በሩቅ ምስራቅ ኤስያ ባሉ ሃገራት በዝርው ተበትነን ያለን /// የቤተ ክርስቲያን ልጆች ምንም እንኳን  ቤተ ክርስቲያናችን ተከትላን  መጥታ እንደ ሌሎች አሃት አብያተ ክርስቲያናትና የምንፈልገውን አገልግሎት ልትሰጠን  አቅም ቢያጥራትም ማንነታችንን ላለማጣትና መንፈሳዊ ሕይወታችን ፈጽሞ እንዳይጠፋ፣ ቢሆንልም ቤተ ክርስቲያን የራሷ አጥቢያ በኤስያ ምድር እንዲኖራት የቻልንውን ሁሉ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በዚህም ከየሃገራቱ ተሰባስበን በአካል ለመገናኘት ባንችልም እንኳን ቴክኖሎጅ በፈጠረልን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዲዳረስ እንጥራለንብለዋል።
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን ከልጆቿ አልፋ ለዓለም ወንጌል ማዳረስ በሚገባት በዚህ ጊዜየቤተ ክርስቲያንን አንድነት፣ መጠናከርና መስፋፋት የማይፈልጉ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንንማመሳቸውበቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ከሚሰማውና ከሚታየው ዓይን ያወጣ ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ችግር ባሻገር የእኛንም መንፈሳዊ ሕይወት የሚያዳክም መጥፎ ዜናሆኖ ሳለቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔ ለመስጠት ቀርቶ አጀንዳዎችን ለመወያየትም  ብፁዓን
አባቶቻችን ያለባቸውን ተግዳሮት ስንመለከት ቤተ ክርስቲያናችን ችግሮቿን ለመፍታት ሥር የሰደደ ችግር ውስጥ እንዳለችበመገንዘባቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስብሰባው እየተከሄደ ባለበት ወቅት ብፁዓን አባቶቻችንን ያስቆጣና የመነጋገሪያ ርዕስ የሆነ በዜና ቤተ ክርስቲያን የወጣው ዘገባ፣በዘገባው የተሸረበውን ክፋትና ብፁዓን አባቶቻችንን በመክሰስና ሥማቸውን በማክፋፋት የተሰራውን ሥውር ተንኮል በሩቅ ምሥራቅ ያለን ምዕመናን ጠንቅቀን እንገነዘበዋለን። በጋዜጣው የዶ/ ቀሲስ መስፍን ተገኝ ስም ተጠቅሶ ከአገልግሎታቸው ለማስታጎል የተጠነሰሰው ሴራ አሳዝኖናል።ያየነውን እንመሰክራለን የሰማነውን እንናገራለን”  እንደሚል ስለ ቀሲስ / መስፍን ተገኝ የምናውቀውን ለመናገር ግድ ይለናልሲሉ ምስክረታቸውን ሰጥተዋል።
የቤተ ክርስቲያን ዕጣን በማናሸትበትና ቅዳሴና ማኅሌት በማይታሰብበት ሩቅ ምሥራቅ በስደት በዝርወት ያለነውን የቤተ ክርስቲያን ልጆች በሃይማኖት ለማጽናት ወንጌልን ለማስተማር ቀሲስ / መስፍን ዘመኑ በፈጠረው ቴክኖሎጂ ላደረጉልን አገልግሎት ዋጋቸው በሰማይ ታላቅ እንደሆነ ብናምንም ቅሉ ብፁዓን አባቶችና መላው የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እንዲያውቁትም እንፈልጋለን። ያሉበት ሃገር የኑሮ ሁኔታና ከእኛ ጋር ያለው የሰዓት ልዩነት ሳይገድባቸው በመርሃ ግብሮቻችን እየተገኙ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፤ ወደፊትም ያገለግሉናል ብለን እናምናለን። የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በሚኖሩበት ክፍለ ዓለም ሳይወሰኑ በፈቃዳቸው ቤተ ክርስቲያንንን እያገለገሉ ያሉትና እኛንም በስልክ፣ በስካይፕና በፓልቶክ  እየተገኙ የሚያጽናኑንና የሚያስተምሩን ቀሲስ / መስፍን ተገኝ ለቅ/ሲኖዶስ የጻፉትን ደብዳቤ በሚዲያ አንብበን አዝነናል፡፡ ነገሩን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገውም ቤተ ክርስቲያንን ከሃገር ቤት እስከ ውጭ ሃገር ድረስ በመከፋፈልና ለመናፍቃን አሳልፎ በመስጠት ግልጥ ጥፋታቸው እየታየባቸውና እየታወቀባቸው ባሉ አካላት በቤተ ክርስቲያን ቅን አገልጋይ አባቶች ላይ ይህ ዓይነት ድርጊት መፈጸሙ ነው፡፡ሲሉ አስረግጠዋል።
በመሆኑም በመምህራችንና አባታችን ላይ የሚነገረው የሐሰት ወሬ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማዳከም የታለመ የክፉዎች ሴራ እንደሆነ በዚህ በሩቅ ምሥራቅ የምንገኝ ምዕመናን እንረዳዋለን። /ሲኖዶስ ጉዳዩን አጣርቶ የርሳቸውንም የእኛንም የተሰበረ ልብ እንዲጠግን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡ አባቶችም ለጉዳዩ መፍትሔ እንደሚሰጡልን በማመን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እናሳስለንበመላት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም  እኛ  ባወጡት  የአቋም  መግለጫ የሚከተሉትን ነጥቦች አስቀምጠዋል፦
“1.   በመከራው ያለው መጋደላችን ከሥጋና ከደም ሳይሆን ከጨለማ ሰራዊት ከክፉ መናፍስት ጋር ነውና የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ  ቤተ  ክርስቲያን  አንድንቷ  ተጠብቆ  አሁን  ከገጠማት  ፈተና ለመውጣት  በሚደረገው  መንፈሳዊ  ትግል  የድርሻችንን  ለመወጣትና  ከአባቶች  በሚሰጠን  መመርያ መሰረት የበኩላችንን እንድምንተባበርና በእግዚአብሔር ኃይል እንደምንታዘዝ እናሳውቃለን::
2.  በተለያዩ  አካላት  በገዳማትና  በአድባራት  በአብነት  ትምህርት  ቤቶቻችንም  የሚደርሱ  የጥፋት   ተልእኮዎችን እንቃወማለን::
3.  የመንፈስ  ቅዱስ  ጉባኤ  የሆነውን  የቤተ  ክርስቲያናችን  ቅዱስ  ሲኖዶስ  በቤተ  ክርስቲያን  የሚፈጸሙ ጥፋቶችና ምዕመናን እያዘኑበት ያለውን የአስተዳደርና የኑፋቄ ችግር እንዲያስቆምልን በትሕትና እንጠይቃለንብለዋል።
በመጨረሻምምዕመናን ራሳቸውን የመፍትሔ አካላት እንዲሆኑና እየደረሱ ያሉ ፈተናዎች ከእያንዳንዳችን መንፈሳዊ ሕይወት ዝለትና ድካም የተነሳም ጭምር ስለ ሆነ በንስሐ ወደ አምላካችን ተመልሰን ሁሉን ወደሚችል ፈጣሪያችንና አባታችን እግዚአብሔር በጾም በጸሎት እንድናመለክት ይገባናልሲሉ አሳስበዋል።

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።