Jan 18, 2013

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ::

ጥምቀት
ምንጭ: ማኅበረ ቅዱሳን  ጡመራ  መድረክ  
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

በሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሥርዓተ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዲት ጥመቀት” በማለት የሥርዓተ ጥምቀትን አለመደገምና አለመሠለስ ገልጦ ተናግሯል /ኤፌ.4፥5/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘውና፥ የታናሽ እስያ ክፍል በሆነችው ቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም. የተሰበሰቡ 150 የሃይማኖት አባቶቻችን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ለኀጢአት ማስተሥረያ /ኀጢአትን በምታስተሠርይ/ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት የጥምቀትን አንድ መሆንና ኀጢአትን በደልን የምታርቅ፣ የምታስወግድ ስለመሆኗ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናግረዋል፡፡ ሃይማኖታቸውንም ገልጠዋል፡፡

ጥምቀት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙ “ጥምቀት” በቁሙ፡- “ማጥመቅ፣ መጠመቅ፣ አጠማመቅ፣ ጠመቃ፣ የማጥመቅና የመጠመቅ ሥራ፣ ኅፅበት፣ በጥሩ ውኃ የሚፈጸም” በማለት ተርጉመውታል፡፡ ምሥጢረ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን ሥርዓተ ጥምቀትን የመሠረተው በሦስት ዓይነት መንገዶች እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡

ሦስቱ መንገዶች የሚባሉትም ትምህርት፣ ትዕዛዝና ተግባር ናቸው፡፡ ይኸውም ሊታወቅ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.3 ቁጥር 5 ላይ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አትደነቅ፡፡” በማለት የአይሁድ አለቃ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ጌታችን ያስተማረውን ትምህርት ልብ ላለው ጥምቀት በጌታችን ትምህርት መመሥረቷን ይረዳል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትዕዛዝም ጭምር ጥምቀትን መሥርቷል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ የጌታችንን ትዕዛዝ እንዲህ ያስነብበናል፡- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡” /ማቴ.28፥19/ መምህረ ትሕትና የሆነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተግባር መምህር ነውና ተጠመቁ ብሎ ካስተማረውና ካዘዘው በተጨማሪ ሥርዓተ ጥምቀትን በተግባር ጭምር መሥርቷል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 3 በማርቆስ ምዕራፍ 1 እና በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ላይ በስፋት እንደተመዘገበው ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ባሕረ ዮርደኖስ ሄዶ ከባሪያው ከዮሐንስ እጅ ሥርዓተ ጥምቀትን ፈጽሟል፡፡ በዚህም ትሕትናንና የትሕትናን አሠራር ፈጣሪያችን አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በበዓላት አከባበር ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ ጥር 10 ቀን /የከተራ ዕለት/ ታቦታተ ሕጉ ከመንበረ ክብራቸው በመነሣት ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ይጓዛሉ፡፡ ይህም ጌታችን በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ ምድርን እንደቀደሳት በማሰብና እርሱኑ አርዓያ በማድረግ ሀገሩን መንደሩን ለመቀደስና ለመባረክ የሚፈጸም ዑደት ነው፡፡

ሥርዓተ ጥመቀት በአጋጣሚ ወይም በድንገት የተጀመረ /የተመሠረተ/ አይደለም፡፡ በዘመነ ብሉይ በርካታ ምሳሌዎች የተመሰሉለት፣ በርካታ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ነው እንጂ፡፡ በነቢዩ ሕዝቅኤል እግዚአብሔር አምላካችን አድሮ ሲናገር “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፣ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኲሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ፡፡” ብሏል፡፡ /ሕዝ.36፥25/ ከኀጢአት የሚያነጻ ከርኲሰት የሚቀድስ ለመንግሥተ ሰማያት የሚያዘጋጅ የሚያበቃ ጥሩ ውኃ ተብሎ የተገለጸ ጥምቀት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሥርዓተ ጥምቀትን የመሠረተው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሆኑ በአጭሩ ከገለጽን፤ ጌታችን የተጠመቀው ለምንድር ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሣ፡-

ጌታችን እርሱ ባወቀ ጥምቀትን የፈጸመበት ዋነኛ ምክንያቶች እንደ ሊቃውንት አባቶቻችን አስተምህሮ በሦስት መንገዶች ይታያል፡፡ እነዚህም

1ኛ ምሥጢረ ሥላሴን /ሦስትነቱን ያስረዳን ዘንድ ነው/ ማቴ.3፥13-17 በዘመነ ብሉይ በነበሩ ሰዎች በረቂቅና በምሳሌ ይታወቅ የነበረውን የልዩ ሦስትነቱንና አንድነቱን ምሥጢር በተረዳ በታወቀና በጎላ ሁኔታ እንረዳ ዘንድ ጌታችን ተጠምቋል፡፡ በቅዱስ ወንጌላችን በግልጽ እንደሚታየው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የስም፣ የአካል፣ የአካለ ግብር ሦስትነት እንዳላቸው በጊዜ ጥምቀቱ ለክርስቶስ እንረዳለን፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ፡- “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት እኔ ባይ አካል እንዳለው ገልጿል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ እርሱም እንደ ባሕርይ አባቱ የራሱ እኔ ባይ አካል እንዳለው ገልጦ አሳይቶናል፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሆኖ ከሰማይ በመውረድ ታይቷል፤ በዚህም መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ እኔ ባይ አካል እንዳለው ተረድተናል፡፡ ስለሆነም ጌታችን ጥምቀትን የፈጸመው የሦስትነቱን ምሥጢር ይገልጽልን ዘንድ ነው፡፡

2ኛ ለትምህርት ለትሕትና ለአርዓያነት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዓተ ጥምቀትን የፈጸመው እንደእኛ የሰው ልጆች የልጅነትን ጸጋ ለማግኘት አይደለም፡፡ እርሱ አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው፤ ተቀዳሚም ተከታይም የሌለው የአብ የባሕርይ ልጁ ነውና፡፡ /ዮሐ.1፥18፣ ዮሐ.3፥16/ እንዲሁም እንደ ንዑስ ክርስቲያን ሥረየት ኃጢአትንም ለማግኘት አይደለም፡፡ ነውርም ኀጢአትም በደልም ምንም ምን ክፋት የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ ነውና ነቢዩ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም እንዳለ /ኢሳ.53፥9፤ ማር.2፥10፣ ሉቃ.7፥49/ ነገር ግን በርዕሳችን እንደተገለጠው ጌታችን ሥርዓተ ጥምቀትን የፈጸመው ለትምህርት፣ ለትሐትናና ለአርአያነት ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን የሚሰጥ እርሱ እንደ ደካማ ሰው ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ሄዶ ከዮሐንስ ዘንድ ሲጠመቅ ትሕትናን አስተምሮናል፡፡ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ሳይል ፤ ከዮሐንስ ዘንድ ሄዶ ተጠመቀ፡፡ የቱንም ያህል ክብር ሥልጦን…. ቢኖረን እኛም ከካህናት ዘንድ መሄድ እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፤ /ዮሐ.131-17 እና 1ኛ ጴጥ.2፥26/

3ኛ. ጥምቀታችንን ይባርክልን ዘንድ
እንፈጽመው ዘንድ የሚገባንንና የሚያስፈልገንን ሥርዓት ሁሉ የሠራልን ፈጣሪያችን ነው፡፡ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀን አርባ ሌሊት በመጾም ጾማችንን እንደባረከልን /ማቴ.4፥1-10/ በጥምቀቱ ጥምቀታችንን ይባርክልን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሉቃስ በወርኀ ጥር በ11ኛው ቀን ማክሰኞ ሌሊት 10 ሰዓት ተጠምቋል፡፡


እኛ የሰው ልጆች ሥርዓተ ጥምቀት እንዲፈጸምልን የሚያስፈልገው፡-
የልጅነት ጸጋን እናገኝ ዘንድ ነው፡፡ ዮሐ.1፥5
አስቀድመን ከሥጋ እናት አባታችን በዘር በሩካቤ እንደተወለድንና የሥጋ ልጅነትን እንዳገኘን ሁሉ በማየ ገቦ ስንጠመቅ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጌታችን “ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው” ብሎ ከማስተማሩ በፊት “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ያለው፡፡ /ዮሐ.3፥3 እና 6/ በምሥጢረ ጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ስለመገኘቱ አስተምሯል፡፡ ሐዋርያውም በጥምቀት ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ አስመልክቶ ሲናገር “አባ አባት ብለን የምንጮኸበትን /የምንጣራበትን/ የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈስ ጋር ይመሰክራል፡፡” ብሏል፡፡ /ሮሜ.8፥15-16/ ጌታችንንም ለተቀበሉት ሁሉ በስሙም ላመኑበት በጠቅላላው የእግዚአብሔር ልጆች ይሁኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አለመወለዳቸው ተገልጿል፡፡ /ዮሐ.1፥11-13/

እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች ሁለት ልደታት እንዳሉን እናስብ፡፡ ይኸውም መጀመሪያው ከሥጋ እናትና አባታችን የተወለድነው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር የምንወለደው ነው፡፡ ከተወለድን በኋላ እድገታችን በሁለቱም ወገን መሆን ያስፈልጋዋል፡፡ ሰው ሥጋዊም መንፈሳዊም ነውና፡፡

ሥርየተ ኀጢአትን ለማግኘት
በአምልኮ ባዕድና በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ከጥምቀት በአፍአ ሆነው የቆዩ ሰዎች ከነበረባቸው ኀጢአት ይነፁ ዘንድ ሥርዓተ ጥምቀት ተሠርታለች፡፡ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በ50ኛው ቀን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብቱ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ማደሩን የሰሙ አይሁድ፤ ከቅዱሳን ሐዋርየት ዘንድ ቀርበው የሚናገሩትን ቃለ እግዚአብሔር መስማት ጀመሩ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነቱን፣ በኃይለ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንና ወደ ሰማይ ማረጉን ነገሯቸው፡፡ አይሁድም ይህንን በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?” አሏቸው፡፡ ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ ኀጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡….” አላቸው /ሐዋ.2፥37-38/ ይህ የሐዋርያው ቃል የሚያስረዳን የጥምቀትን መድኀኒትነት ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለጥነው አባቶቻችን በሃይማኖት መግለጫቸው “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፥ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ማለታቸው ጥምቀት ከደዌ ነፍስ የምታድን መሆኗን መመስከራቸው ነው፡፡ /ጸሎተ ሃይማኖት/

ዘላለማዊ ድኅነት
የሰው ልጅ ድኅነት ቅጽበታዊ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና የድኅነት በር ከፋችና ሌሎችን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለመፈጸም የሚያበቃን ምሥጢር ምሥጢረ ጥምቀት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው ሐዋርያዊ መመሪያ ውስጥ “ሑሩ ውስተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት፡፡ ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ይደየን፡፡ ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ /ማር.16፥15-16/

እንግዲህ በጥምቀት ያገኘነውን ጸጋና ክብር ሁላችን ልናስብ ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም ክብራችንን መጠበቅ ያሻናል፡፡

ፈጣሪያችን በዓሉን በዓለ ሰላም ፤ በዓለ ክብር ፤ በዓለ ፍስሐ ያድርግልን - አሜን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።