ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ
እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ፡፡ እነሆ÷እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም፡፡” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም አንደሚገባው እመሰክራለሁ፡፡ በኦሪት ልትጸድቁ የምትፈልጉ እናንተ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋዉ ወድቃችኋል፡፡ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ÷ በእምነትም ልንጸድቅ ተስፋ አናደርጋለን፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና፡፡ ቀድሞስ በመልካም ተፋጠናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና፡፡ ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል፡፡ ወንድሞቼ ሆይ÷ እኔ ግዝረትን ገና የምስብክ ከሆነ÷ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል፡፡ የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል፡፡
ወንድሞቼ ሆይ÷ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ፡፡ “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና፡፡ እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትንካከሱ ከሆነ ግን÷ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ፡፡
እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ፡፡ ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልና÷ መንፈስም ሥጋ የማይሻውን ይሻልና የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፡፡ የመንፈስን ፈቃድ የምትከተሉ ከሆናችሁ÷ ከኦሪት ወጥታችኋል፡፡ የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት÷ ርኲሰት÷ መዳራት÷ ጣዖት ማምለክ÷ ሥራይ ማድረግ÷ መጣላት÷ ኲራት÷ የምንዝር ጌጥ÷ ቅናት÷ቊጣ÷ ጥርጥር÷ ፉክክር ÷ምቀኝነት መጋደል÷ ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡
አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር÷ ደስታ ÷ሰላም÷ ትዕግሥት÷ ምጽዋት÷ ቸርነት÷ እምነት÷ ገርነት÷ ንጽሕና ነው፡ ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ፡፡ አሁንም በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስም እንመላለስ፡፡ ኩሩዎች አንሁን፤ እርስ በርሳችን አንተማማ፤ እርስ በርሳችንም አንቀናና፡፡
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።