Apr 30, 2013

ሰሙነ ሕማማት



                                           ምንጭ፦   ማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ መምህር ኃይለ ማርያም ላቀው
ፍቅር የተከፈለ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ደኅንነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለ ካሠልንቅዱስ ሳምንትተብሏል፡፡ በተጨማሪምየመጨረሻ ሳምንትተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሙዓለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡
ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፣ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፣ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ እንዲሁም ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ እንዲከበር ይተላለፋል፡፡ ይህ ብያኔ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ ሆኗል፡፡ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ ከዓመፀኞችም ጋር ተቆጠረ፡፡ እርሱ ግን ግፍን አላደረገም ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፡፡” /ኢሳ.53÷4-12/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ ምእመናን ክርስቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መሆኑን በማዘከር በሰሙነ ሕማማት ከማንኛውም የሥጋ ሥራ መታቀብ ዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር በኀዘን ልናከብረው ይገባል፤ ብድራትን የማያስቀረው አምላክም መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ ያደርገናልና፡፡

ሰሙነ ሕማማት አስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከጾሙ ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር፡፡ በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም ሕማማቱም ትንሣኤውም ተያይዘው እንዲከበሩ ተደረገ፡፡ ምዕራባውያን ከአርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል፡፡ የምሥራቃውያን /ኦሪየንታል/ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን አርባውን ጾም ጨርሰን ከኒቆዲሞስ በኋላ ያለውን ተከታዩን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን፡፡ከእነዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት /በሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ/ ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሰኞ
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሳዕና ማግሥት ጌታችን ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ነገሮችን አድርጓል፡፡ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል፡፡/ማቴ.21÷12-17 ማር.11÷17 ሉቃ.19÷45-46፡፡/ በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥበማግሥቱ ተራበየሚል ቃል እንመለከታለን፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስእግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም” /ኢሳ.46÷25/ ይላል፡፡ በቅዱስ ወንጌልምበመጀመሪያ ቃል ነበርይላል፡፡ ቃል ቀዳማዊ እንደ ሆነ፣ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበር፣ ያም ቃል እግዚአብሔር ነው ተብሎ ተጽፏል፡፡ ዮሐ.1÷1-2፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱም ሲያስተምርየእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፡ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው” /ዮሐ.4÷34/ ሲል ተናግሯል፡፡ ነቢዩ እግዚአብሔር እንደማይራብ ተናግሯል፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፣ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፡ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ ፤ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ 5000 የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ተራበ! ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በእርግጥ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመሆኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረሃብ ንዴት ያለበትና የአንዲት የበለስ ዘለላ ረሃብ አይደለም፡፡ ረሃቡ የበለስ ፍሬ ሳይሆንበለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱእንዲል የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባርን ፍሬ የሻ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅበአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማትብሏል፡፡

እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የአመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመሆን መብቃታቸውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡- “አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሶኩሰ ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኽውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፡፡ብሎ ተርጉሞታል፡፡ እሾኽ የእርግማን ምሳሌ ነው፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡ ዛሬ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይሆን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ ይለናል፡፡ ማቴ.3÷8፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እናፍራ፡፡ ገላ.5÷22፡፡ ጌታችን በዳግም ልደት ሲመጣ ከሰው ልጅ ሃይማኖት መገኘቱ አጠራጣሪ እንደሆነ ተናግሯል፡፡የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይሆንን?” ቀጣይ ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን ከእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ ፍቅሩን ለማትረፍ እንትጋ፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።