Apr 2, 2014

ኢትዮጵያዊው ብርሃን

እንኩዋን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓለ-ፅንሰት በሰላም አደረሳችሁ

ለጽንሰትከ፡- ተክለ ሃይማኖት ሆይ አስቀድሞ በማህጸን ለተጸነስከው ጽንሰትህና በታህሳስ 24 ቀን ለተወለድከው ልደትህም ሰላም እላለሁ፡፡ለዝክረ ስምከ፡- ተክለ ሃይማኖት የስምህ የመነሻ ፊደሉ ትእምርተ መስቀል ለሆነው ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁኝ እርሱም ገናናና የከበረ ስም ነውና፡፡ለስእርተ ርዕስከ፡- ተክለ ሃይማኖት ሆይ በአምላክ ህሊና ለሚቆጠሩና ለሚታሰቡ የራስ ጸጉሮችህ ሰላም እላለሁ እሊኸውም የክብር መጎናጸፊያ ያላቸው እንደ ሦስቱ የይሁዳ ልጆች ናቸውና፡፡ለርዕስከ፡- ተክለ ሃይማኖት ሆይ መልከ መልካማ ሙሽራ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን በንጹህ የአፌ ወርቅ ለመሰለችው ርዕስህ ሰላም እላለሁ፡፡ለገጽከ፡- ተክለ ሃይማኖት ሆይ ከጸሃይ ከጨረቃ ስነጸዳል ይልቅ ለክርስቶስ የምስጋና ጸዳል ለተዋበው ፊትህ ሰላም እላለሁ፤ ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መልከዓ ላይ የተወሰደ፡፡
አቡነ ተክለሃይማኖት በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤በ፲፩፻፺፯ . ታሕሣሥ ፳፬ቀን ተወለዱ:: በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ወይም ደስታዋ ማለት ነው፡፡ አባታቸው የቤተክርስቲያንን ትምህርት ሲያስተምሯቸው አካባበቢያቸው ደግሞ በዘመኑ የነበሩ ልጆች ይማሩ  የነበረውን ፈረስ መጋለብን፣ ቀስት መወርወርን፣ እርሻን እና አደንን አስተምረዋቸዋል፡፡
በሰባት ዓመታቸው ከግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር በክህነት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ መረጣቸው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ለክህነት መጠራት በዚህ ዓለም ትዳር መሥርቶ፣የዓለሙንም ሥራ ሠርቶ መኖር አያስፈልግም ከሚልፍልስፍና የመነጨ አይደለም፡፡ከ8ኛው መ/ክ/ዘ ጀምሮ በሀገሪቱ  የመንፈስ መቀዛቀዝ ይስተዋል ነበር፡፡ ዮዲት ጉዲት መንግሥቱን ይዛ በክርስትናው ላይ ከዘመተች በኋላ ሰሜኑ እና ደቡቡ ተቆራርጧል፡፡ የሃሳብን ልዕልና የሚያመጣው የመንፈስ ልዕልና ተዳክሟል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን የሚዋጅ ኢትዮጵያዊ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ነው የተክለሃይማኖት የጥሪ ምክንያት፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾለ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ሃይማኖት» አለው ፡፡ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ «አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ. . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም።ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»/ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ ፳፰ - ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባታቸው ዕረፍት በኋላ ቅስናን ከአቡነ ቄርሎስ ተቀብለው በጽላልሽ አካባቢ በክህነት ከአባታቸው ጋር አገልግለዋል፡፡ አባታቸው ሲያርፉ በወንጌሉ ማንም ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ያለውን ሁሉ ትቶ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ያለውን በመከተል ሀብታቸውን ለድኾች መጽውተው ለወንጌል ስብከት ወጡ፡፡የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ከመሄዳቸው በፊት ቅስናን ተቀብለው በሸዋእና በዳሞት ማገልገላቸውን ይገልጣል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዳሞት እና በሸዋ ካገለገሉ በኋላ መጀመርያ ደቡብ ወሎ ቦረና ወደ ነበረው ወደ ደብረ ጎል ገዳም ገብተው አሥር ዓመት (12 የሚልም አለ) በትምህርት እና በሥራ አሳልፈዋል፡፡ በዚያም ዋሻ ፈልፍለው አስደናቂ ሕንፃ ሠርተው ነበር:: ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳንመንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:- «እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ፲፩ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡ «ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡ «የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ፴፬/ እንዳለው አባታችንም የአውሬውን፥የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል። «ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡«ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡ደብረሊባኖስገዳም
ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ እንደሚለው አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ሐይቅ የገቡት በሠላሳ ዓመታቸው ነው፡፡ይህም የሚያሳየን በሸዋ እና በወላይታ ያገለገሉት ገና መሆኑን ነው፡፡ 1216 ዓም አካባቢ ወደ ሐይቅ የገቡት አቡነ ተክለሃይማኖት በሐይቅ ከመመንኮሳቸው በፊት ሰባት ዓመት ከመነኮሱም በኋላ ሦስት ዓመት በትምህርት በሥራ እና በአገልግሎት ቆይተዋል፡፡ሐይቅ እስጢፋኖስ በዚያ ዘመን እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ያለ ዩኒቨርሲቲ ነበረ፡፡ወደዚያ የሚገባ ሁሉ ሦስት ነገሮችን ይማራል፡፡ ትምህርት፣ የጥበበእድ ሥራ እና ሥርዓተ ምንኩስና፡፡ ትምህርቱ የቤተክርስቲያኒቱን መላ ትምሀርት ያካትታል፡፡ የሞያ ትምህርቱም መጻፍ፣ መደጎስ፣ ሕንፃ ማነጽ፣ ልብስ መሥራት፣ እርሻ፣የከብት ርባታ እና የሥዕል ሥራን ይመለከታል፡፡ ከእነዚህጎን ለጎን ደግሞ ጽሙድ እንደ ገበሬ ቅኑት እንደበሬ እንዲሆኑ ሥርዓተ ምንኩስናን ይማራሉ፡፡
በእነዚህ ትምህርቶች የታነፁት መነኮሳት ከገዳሙ ሲወጡ ዛሬ የፒኤች ተማሪ ዴዘርቴሽን እንደሚያቀርበው የተማሩትን ጽፈው አንድ የብራና መጽሐፍ አዘጋጅተው ይወጣሉ፡፡ በዚህም  ምክንያት ሐይቅ ከስምንት መቶ መነኮሳት በላይ በአንድ ጊዜ የሚማሩባት በመጻሕፍትም የበለጸገች ዩኒቨርሲቲ ነበረች፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እዚህ ነው አሥር ዓመታትን ያሳለፉት፡፡ ከሐይቅ ወጥተው በዘመኑ በሥርዓተ ምንኩስና እና በትምህርት ብሎም በጥበበእድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ ነበረው ወደ ደብረ ዳሞ ሄዱ፡፡በዚያም ከአቡነ ዮሐኒ ዘንድ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ሥርዓተ ምንኩስና እና ጥበበ እድ ሲማሩ ሰባት ዓመት አሳለፉ፡፡ያነጹት ፍልፍል ድንጋይ ዋሻ፣ መጻሕፍት ሲጽፉ ቀለማቸውን ያስቀምጡባቸው የነበሩትን ሽንቁሮች ዛሬም በደብረ ዳሞ ማየት ይቻላል፡፡ ቀሪዎቹን አምስት ዓመታት ሌሎችን የትግራይ ገዳማት እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ቆይተው ከሸዋ በወጡ በሃያ ሁለት ዓመት እድሜያቸው ሃምሳ ሁለት ሲሆን ለበለጠው ክብር እና ርእይ በግብጽ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ተሻገሩ፡፡ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ በሐይቅ በኩል አድርገው ደብረ ጎልን ተሳልመው በሚዳ እና በመርሐ ቤቴ በኩል ወደ ሸዋ በመምጣት ከዮዲት ዘመን በኋላ በመንፈሳዊ ሕይወት የተጎዳውን ሸዋን እና ደቡብ ኢትዮጵያን በመዘዋወር ለአሥር ዓመታት ያህል አስተምረዋል፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተግተው በማስተማራቸው የተኛው ሁሉ ነቃ፣ የደከመው በረታ፣የጠፋውም ተገኘ፡፡በስብከታቸው እንደገና ለነቃው ለመካከለኛው እና ለደቡብኢትዮጵያ ሐዋርያትን ለማፍራት እንዲችሉ አንድ ገዳም ለመመሥረትና ደቀ መዛሙርትን ለማስተማር አሰቡ፡፡ እናምወደ ደብረ አስቦ ገዳም ገቡ፡፡ ቦታውን አስተካክለው እናከደብረ ዳሞ እና ከሐይቅ የተከተሏቸውን ጥቂት ደቀመዛሙርት ይዘው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ልክ እንደ ሐይቅእስጢፋኖስ ሁሉ ሦስቱን ነገሮች ያካተተ አገልግሎት ጀመሩ፡፡ምንኩስና፣ ትምህርት እና ሥራ፡፡ መነኮሳቱ መንፈሳዊ  ትምህርት ይማራሉ፤ በሕገ ገዳም ይመራሉ፤ለራሳቸው እና ለአካባቢው ሕዝብ ርዳታ የሚሆን እርሻያርሳሉ፡፡ደቀ መዛሙርትን አፍርተው፣ ገዳማቸውንአደራጅተው፣ ስብከተ ወንጌልንም አስፍተው አስፍተውሰያደ ላድሉ በሕይወታቸው የመጨረሻ ዓመታት ወደ ደብረአስቦ ዋሻ ገብተው በአንድ እግራቸው በጾም እና በጸሎት ተወሰኑ፡፡ በጸሎት ብዛትም እግራቸውን በማጣታቸው ስለክብራቸው ከእግዚአብሔር ክንፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለትአይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁእያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አገልግሎታቸውን ፈጽመው ነሐሴ ሃያ አራት ቀን 1287 ዓም 99 ዓመታቸው ዐረፉ፡፡

ጸድቁ አባታችን አቡነ ተክልሃይማኖት ጸሎትና በረከታቸው ፣አማላጅነታቸው፣ ቃልኪዳናቸው በቤተክርስቲያናችን በሀገራችን ጸንቶ ይኑር አሜን..አጽራራ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን ሀገራችንን ፍቅር አድነት ሰላም ያድልልን አሜን…!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር:: ወወላዲቱ ድንግል:: ወለመስቀሉ ክቡር:: አሜን…!!!

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።