Apr 17, 2014

ከጸሎተ ሐሙስ እስከ ቀዳም ሥዑር


ጸሎተሐሙስ

በብሉይ ኪዳን የቂጣ በዓል የሚለውን ትርጉም ከመስጠቱ በተጨማሪ ጌታችን ምስጢረ ቁርባንን ከምስጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ  የገለጠበት ዕለት ስልሆነ ታላቅ የምስጢር ቀን ነው። በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደተለመደው ይከናወናሉ ለየት ያለው ሥርዓት መንበሩ /ታቦት/ ጥቁር ልብስ ይለብሳል ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል ቤተክርስቲያኑ በማዕጠንት ይታጠናል።

በዘጠኝ ሰዓት

ዲያቆኑ ሁለት ኮስኮቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ ጸሎተ አኮቴት  የተባለ የጸሎት ዐይነት ተጸልዮ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ / በሊቀ ጳጳሱ/ እጅ ተባርኮ የሕጽበተ እግር ሥርዓት ከካህናት እስከ ምእመናን ከወንዶች እስከ ሴቶች በካህኑ እስተናጋጅነት ይከናወናል።
ሥርዓተ ኅጽበቱ የሚከናወነውም በውኃ ብቻ ሳይሆን የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዐቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን። ምስጢሩም የሚከተለውን ይመስላል። ወይራ ጸኑዕ ነው ክርስቶስ ጽኑ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም /የሚያጥበውና የሚታጠበው ክርስቲያን/ መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው። የወይኑ ቅጠል በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ነው። ማቴ 2626.
ይህም ሥርዓት ጌታችን የደቀ መዛሙርትን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለምእመናን ለማሳየት ነው። ዮሐ 1314 በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም «ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ» እያሉ ይዘምራሉ። ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ።

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ

ቅዳሴው የሚከናወነው በተመጠነ ድምጽ ነው በቀስታ ስለሚጮህ ነው። የድምጽ ማጉያ አይጠቀሙም ምክንያቱም ዲያቆኑና ካህኑ ዜማውን በቀስታ የሚሉት ይሁዳ በምስጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን በሌላ በኩል የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደነበር ለማስታወስ ነው።
በመቀጠል ክቡር ይእቲ፥ ዕጣነ ሞገር ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል። ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ።

ዕለተ ዓርብ ነግህ

ዕለተ ዓርብ የአዳምን ነጻነት ለመመለስ የአዳምን ዕዳ በደል አምላካችን የተሸከመበት ዕለት የኀዘን ዕለት የድኅነት ዕለትም ነው። በዚሁ ዕለት ሁሉም ነገር እንደተለመደው ይከናወናል መሪው እዝል ይመራል ሕዝቡ ይከተላል አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ። በየመሀሉ «ውጸቡሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት፣ ሲነጋም ሊቃነ ካህናት ተማከሩ» የሚለው ዜማ በመሪ በተመሪ በሕዝብ ተሰጥዎ ይከናወናል። ምንባቡም ስግደቱም ድጓውም እንደ አለፈው ይቀጥላል።

በሦስት ሰዓት

ሥዕለ ስቅለቱ መስቀሉ ወንጌሉ መብራቱ ጽንሐሑ በመቅደሱ በር ላይ ይዘጋጃል ዲያቆኑ በቃለ ማኅዘኒ በሚያሳዝን ቃል ግፍኦሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍኡኒ ይላል። ካህናቱም ምእመናኑም በዜማ እየተቀበሉ ይሰግዳሉ።
ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ። በየመሀሉ የሰዓቱ ድጓ ይቃኛል።

ስድስት ሰዓት

የዕለቱ መሪ እዝል ይመራል ሦስቱ ካህናት ጽንሐሑን ይዘው ከርቤ እያጠኑ ዲያቆናት መብራት እያበሩ ለመስቀልከ ንስግድ እያሉ ያዜማሉ ምእመናን ዜማውን እየተቀበሉ ይሰግዳሉ ከዚያም ዲያቆኑ ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ የሚለውን ምስባክ ሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ በየመሀሉ ድጓው ይዜማል ከዚህ ቀጥሎ ምእመናን ይቀመጣሉ ሦስቱ ካህናት ጥቁር ልብስ ለብሰው በሚያሳዝን ዜማ አምንስቲቲ ሙኪርያ አንቲ ፋሲልያሱ፣ ጌታየ ሆይ ስለ እኔ ሞትህ ወዮ እኔ ልሙትልህ እያሉ ሦስት ጊጌ ያዜማሉ።
ሕዝቡ ይቀበላል በዚያው አያይዘው ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግስትከ እያሉ በዜማ ይጸልያሉ ሕዝቡ ይቆማል ሥርዓተ ስግደቱም ይከናወናል።

በዘጠኝ ሰዓት

ሌላው እንደተለመደው ሆኖ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ ሦስት ጊዜ ካህናቱ በዜማ ይሉታል ምእመናንም ይቀበላሉ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ ስግደት እንደተለመደው ነው በሦስት ሰዓት በስድስት ሰዓት በዘጠኝ ሰዓት ወንጌላቱ ተነበው እንዳለቁ ለምእመናን ትምህርተ ወንጌል ይሰጣል። ይህ ግን እንደ ቋሚ ሥርዐት ሳይሆን እንደ ሁኔታው አመቺነት  ነው።

አሥራ አንድ ሰዓት

ካህናት በአራቱ መዓዘን ቁመው አራት መቶ እግዚኦታ ያደርሳሉ ዕለቱን የሚመለከቱ መዝሙራት ተመርጠው ይነበባሉ። ንሴብሖ  እየተባለ ቤተ መቅዱስን በመዞር በከበሮ በጽና ጽል በሕማሙ ያዳነን እግዚአብሔር ይመሰገናል። ዑደት የሚደረገው ሥነ ስቅለቱን በመያዝ ነው። ምእመናን በሰሙነ ሕማማት  የሠሩትን ኃጢያት እየተናዘዙ በክህናት አባቶች ንስሐ ይቀበላሉ፤ በወይራ ቅጠልም ቸብ ቸብ ይደረጋሉ የመከራው ተሳታፊዎች መሆናቸውን ለመግለጥ ነው። በታዘዙት መሠረትም  ስግደታቸውን ያጠናቅቃሉ።
ከዚያ በኋላ በካህኑ ኑዛዜ ምእመናን ወደ የቤታቸው ይሰናበታሉ። መስቀል መሳለም አሁንም የለም የቻለ ከሐሙስ ጀምሮ አሊያም ከዓርብ ማታ ጀምሮ እስከ ዕለተ ትንሣኤው ድረስ ያከፍላል/ይጾማል/ የተጀመረውም በዕለተ ስቅለቱ በሐዋርያትና በእመቤታችን እንደሆነ አበው ያስተምራሉ።

ቀዳም ሥዑር

የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾምስዑር/የተሻረች/” ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም።  ቀዳም ሥዑር በጾም ምክንያት የተሻረችው ቀዳሚት ሰንበት ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኅልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው። ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመለጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፉ ያድራል ጥዋት  አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትስ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል። ገብረ ሰላም በመስቀሉ እየተባለ እየተዘመረ ቀጤማውም ቤተ  መቅደሱን ዞሮ በካህኑ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል። የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዘ በመግባት ነው።
ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጎደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰብከ ታወጀ በማለት ካህናት ቀጤማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩታል። በአጠቅላይ ሥርዓተ ሕማሙን፣ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም ልንጠቀምበት ይገባል።
በሊቀጠበብት ሐረገወይን አገዘ 
(ምንጭ፡ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት  መጋቢት 2002)

ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።