ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የዐቢይ ጾም የመጀመሪያውን እሁድ ዕለት “ዘወረደ” በማለት ትጠራዋለች። እግዚአብሔር በገባዉ ቃልኪዳን መሰረት “…የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” እንዳለ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ የጠፋዉን አዳም ፍለጋ ከአባቱ እሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መዉረዱን የምናዘክርበት በዓል ነዉ።
ሰዉ የተሰጠዉን የሞት ማስጠንቀቂያ ባለመጠበቁ ፍርድ ተፈርዶበት፣ መዊተ ስጋ መዊተ ነፍስ ነግሶበት፣ በህይወተ ስጋም እያለ በሞት ጥላ ስር የሚኖር እና በሞት ፍርሃት የታጠረ ነበር። ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይቶ የተስፋ ቦታዉን ለቆ ከዓለመ መላዕክት ወደ ዓለመ እንሰሳ ተጥሎ የፀጋ ልጅነቱን እና ክብሩን አጥቶ በባርነት ዉስጥ እኩያት ፍትወታት ሰልጥኖበት ይኖር ነበር። (መዝ፡- 18፡4-5) ምንም እንኳን ሰዉ እግዚአብሔርን ከሰማይ ከመንበሩ የሚያስወርድ ስራ ባይኖረዉም አምላኩን (ወልድን) ከመንበሩ የሚስብ ፍቅር ባይኖረዉም እግዚአብሔር ግን ሰዉን እንዲሁ ወዶታልና ይፈልገዉ ዘንድ ፣ ከወደቀበት ያነሳዉ ዘንድ ወረደ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ህይወት እንዲኖረውእንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና። ” (ዮሐ 3፡16) ተብሎ እንደተፃፈ እግዚአብሔር ሰዉን የወደደዉ እንዲሁ ነዉ እንጂ ሰዉ የሚወደድ ነገር ኖሮት አልነበረም።
ሰዉን ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ አዉጥቶ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰዉ ዘንድ ከዚያም በላይ ያደርሰዉ ዘንድ አካላዊ ቃል ወልደእግዚአብሔር ወረደ። ሰዉ ሆነ። ይህ ሚስጢረ ተዋህዶ ነዉ። ተዋህዶ እንበለ ተፈልጦ (ያለመለያየት) የሌለበት ነዉና አካላዊ ቃል ወርዶ በተዋሃደ ቅፅበት የትስብዕት ወይም የስጋ ዕርገቱ በዚህ ጊዜ ነዉ። ምክንያቱም በምድር በከርሰ ድንግል እያለ በሰማይ ከአባቱ እና ከሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አልተለያዩምና ነዉ። በዚህም የትስብዕት ዕርገቱ በፅንሰት፣ የቃል ዕርገቱ በዓርባ ቀን ድህረ ትንሣኤ መሆኑ በዚሁ ዕለት በሚነበበዉ ወንጌል ላይ “ከሰማይ ከወረደዉ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። እሱም በሰማይ የሚኖረዉ የሰዉ ልጅ ነዉ።” (ዮሐ 3፡13) በሚለዉ የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር በምድር እያለ እየተመላለሰ “በሰማይ የሚኖረዉ የሰዉ ልጅ ነዉ”። ባለዉ አምላካዊ ቃል ይታወቃል። ለዚህ ነዉ ታላቁ ሊቅ አባታችን ቅዱስ ያሬድ እመቤታችንን ባመሰገነበት ድርሳኑ በአንቀፀ ብርሃን ላይ “… ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ የሚመግብ ጌታቸዉ በብብትሽ (በክንድሽ) ተቀምጦ ጡትሽን እንደ ሕጻን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርያም ፈለጉና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞዉ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት። የጌታ ትሕትናዉን ባዩ ጊዜም ዓይኖቻቸዉን ወደ ላይ ወደ አርያም ከፍ ከፍ አደረጉ፣ ክንፋቸዉንም ዘርግተዉ ለሁሉ ጌታ ላንተ በሰማይ ምስጋና ይገባሃል። እያሉ ጌታቸዉን አመሰገኑ። ” በማለት የተናገረው።
በቤተክርስቲያን በዚህ ዕለት የሚዘመረው መዝሙር ፤የሚነበበው ምንባብ ፤ የሚቀደሰው ቅዳሴ ከዚህ እንደሚከተለው ነው
መዝሙር
ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ባኡ ቅድሜሁ በተጋንዮ ወውስተ አ|ዕፃዲሁ በስብሐት አምንዎ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ወንትፋቀር በበይናቲነ እስመ ለዓለም ምሕረቱ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ እስመ ሰንበትሰ በእንተ ሰብእ ተፈጥረት እስመ ለዓለም ምሕረቱ ምሕረተ ወፍትሐ አሐሊ ለከ እዜምር ወእሌቡ ፍኖተ ንጽሕ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ አባግዓ መርዔቱ።
ትርጉም፦ እግዚአብሔርን በመፍራት ተገዙለት ለእርሱ መገዛትም ደስ ያሰኛችሁ። እግዚአብሔር ቸር ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነው ። እኛስ ሕዝቡ የመሰማሪያው በጎች ነን፡፤ ወደ ደጁ በመገዛት፣ ወደ አደባባዮችም በምስጋና ግቡ፤ ጾምን እንጹም፤ጓደኞቻችንን እናፍቅር፤እርስ በርሳችንም እንፋቀር ። ሰንበት ስለሰው ተሠርታለችና ሰንበትን እናክብር። እውነትንም እንሥራ፤ አቤቱ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ፤ እዘምራለሁ፤ንጹሕ መንገድንም አስተውላለሁ።
ምንባባት
መልዕክታት
ዕብ.13÷7-17 የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡
ያዕ.4÷6-ፍጻ. ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡
ግብረ ሐዋርያት
ሐዋ.25÷13-ፍጻ. ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡
ምስባክ
መዝ. 2፡11 “ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ። አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር።”
ትርጉም፦ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።ጥበብን አጽኑአት ፤ እግዚአብሔር እንዳይቆጣ።
ወንጌል
ዮሐ.3÷10-24 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን አንዴት ይህን አታውቅም?” አለው፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም፡፡ በምድር ያለውን ስነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁን ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ አንጂ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፡፡ ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም አንዲፈርድ እግዚአአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም አልላከውምና፡፡ በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል፤ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አላመነምና፡፡ ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጥቶአልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደብርሃን አይመጣም፡፡ አውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ አብሮአቸው ተቀመጠ፡፡ ዮሐንስም በዮርዳኖስ ማዶ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ያጠምቅ ነበር፤ በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ እየመጡ ያጠምቃቸው ነበር፡፡ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልገባም ነበርና፡፡
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
ጾማችን የጸጋ ፤ የበረከት ያድርግልን
ምንጭ፦ ስንክሳር- የዲያቆን መልአኩ እዘዘው ገጽ
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።