Mar 1, 2015

የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት፦ምኩራብ

ምንጭ ፦ ማ/ቅ ድረ ገጽ

“ዘወትርም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር” ሉቃ.19፥47 

ምኲራብ የአይሁድ የጸሎት ቤት ሲሆን በብሉይ ኪዳን ዘመን የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና በሥርዓቱ የተመሠረተ ነበር፡፡ ናቡከደነጾር ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ ሕዝቡንም ወደባቢሎን አፈለሰ፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎትና ለማኅበረተኛነት ልዩ ቤት ሊሠሩ እንደጀመሩ ይታሰባል፡፡ /የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት/ አይሁድ በምኲራቦቻቸው የሕግንና የነቢያትን መጻሕፍት /የብራና ጥቅሎች/ በአንድ ሣጥን ውስጥ ያስቀምጣሉ በመሆኑ እኒህን የጸሎት ሥፍራዎቻቸውን ለትምህርትና ለአምልኮ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በሕገ ኦሪት የአይሁዳውያን ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ሕግና ልማዳቸው ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ተግባራት ከሚሄዱበትም ይልቅ በዓመት አንዴ የሚቀርበውን መሥዋዕትና መባዕ ለመስጠት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር ከሕግ ጸባያዊ /ከተፈጥሮ ሕግ/ እኩል ሕግ መጽሐፋዊንም /የመጽሐፍት ሕግን/ ሲፈጽም ስለኖረ እንደ ሕጉ ወደ ቤተ መቅደስ በመሄድ ሥርዓት ይፈጽም ነበር፡፡ “ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንደአስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ” እንዲል /ሉቃ.2፥42/ አምላካችንና መድኃኒትችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሥርዓት የሐዲስ ኪዳን አስተምህሮውን /ወንጌልን/ መስበክ ከጀመረም በኋላ አጽንቶ ይፈጽም ነበር፡፡ መጽሐፍም ይህን ሲያጸናልን፡- “ዕለት ዕለትም በቤተ መቅደስ /ምኩራብ/ ያስተምር ነበር፡፡” /ሉቃ.19፥47/ ይለናል፡፡ ጌታችን በምኩራብ እየተገኘ ሲያስተምር ትምህርቱን ሕግን አውቆ እንደሚያሳውቅ ሠራዔ ሕግ ስለሆነ በሙሉ ሥልጣንና ኃይል ያስተምር ነበር፡፡ “በሰንበት በምኩራብ ገብቶ ያስተምራቸው ጀመረ፡፡ ትምህርቱንም አደነቁ፤ እንደጻፎቻቸው ያይደለ እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና” እንዲል /ማር.1፥21/፡፡ ይህም ስለምን ነው ቢሉ ባያውቁትም ቅሉ ከርሱ ባገኙት ሥልጣንና ከመምህራኖቻው በተማሩት እውቀት ተመርተው ያስተምሩ ነበር፤ እርሱ ግን ዓለምን በመዳፉ የያዘ ለእነርሱም በሕገ ኦሪት አማካኝነት እውቀት ዘበፀጋን ከፍሎ የሰጠ ነውና ከራሱ አንቅቶ ያስተምር ነበርና ነው፡፡ 
ከላይ በተጠቀሰው መሠረትና መንገድ በምኩራብ እየተገኘ በግልጥ ያስተምርና ይፈውስ ነፍሳትንም ወደመንጋው ይጨምር ነበር፡፡ አስተምህሮውን ለምን በግልጥ አደረገ ቢባል አንደኛው ምክንያት አይሁድ ለመማርና ለመለወጥ ያይደል እንከን ያገኙበት ዘንድ ዕለት ዕለት ከትምህርት ገበታው ላይ ይገኙ ለነበሩት ለፈሪሳውያንና ለጸሐፍት ምክንያትን ያሳጣ ዘንድ ነበር፤ ይኸውም በሥውር ፈጽሞት ቢሆን ኖሮ ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በመላው ይሁዳ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል ብለው ለከሰሱት ምክንያት ማሳመኛ አይደለም በሆነ ነበርና ነው፡፡ እንዲሁም ሕዝብን በእርሱ ላይ በማነሳሳት ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ የካህናት አለቆችና ጸሐፍትን መጽሐፍ እንዲህ ይላል “የካህናት አለቆችና ጻፎችም ቆመው በብዙ ያሳጡት ነበር፡፡” /ሉቃ.23፥5-10/ ስለሆነም አይሁድ እንኳን በምክንያት ተደግፎላቸው ቀርቶ ነቁጥ ከማይገኝበት ከጌታችን በሆነው ባልሆነው ምክንያት ይፈልጉ ነበርና ለዚህ የተመቸ እንዳይሆን /ለእነርሱም የመሰናከያ ምክንያት እንዳይሆን/ ይህን አድርጓል፡፡ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “በአባቱ እቅፍ ያለ ልጁ እርሱ ገለጠልን” /ዮሐ.1፥18/ እንዲል ትንቢታትንና ምሳሌያትን እያፍታታ፣ የተሰወረውን እየገለጠ ሊያስተምር ወደዚህ ዓለም መጥቷልና ማስተማሩን በግልጥ አደረገ፡፡ እርሱም ቢሆን አንዳች ነገርን እንዳልሰወረ በሊቀካህናቱ ፊት ባቆሙት ጊዜና ስለትምህርቱ በጠየቁት ጊዜ እንዲህ በማለት መስክሯል፡- “እኔ ለዓለም በግልጥ ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብም በቤተ መቅደስም ሁል ጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም የተናገርሁት አንዳች ነገር የለም፡፡” /ዮሐ.18፥20/ በሌላ መልኩ ይህ ቤተ መቅደስ /የጸሎት ሥፍራ/ በኦሪት የሚፈጸሙ ሥርዓቶችን /መሥዋዕትንና መብዓ ማቅረብን የመሳሰሉትን/ የሚያከናውኑበት ሥፍራ የነበረ እንደመሆኑ መጠን በሥፍራው የመሥዋዕት እንስሳት፣ የመሥዋዕት ማቅረቢያና ማሟያ ግብአቶች ለሽያጭ ይቀርቡ ነበር፤ አይሁድ አምልኳቸውን ከመፈጸም ይልቅ ቅሚያ፣ ዝርፊያ፣ ማታለል ይፈጽሙበት ነበር፡፡ ጌታችን “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” /ማቴ.21፥13/ በማለት ተቃውሟቸዋል ሻጮችንም ሆነ ገዢዎች የነበሩትን ሁሉ በጅራፍ ገርፎ አባሯል፡፡ ሻጮችንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ…..” /ማቴ.21፥12/ እና “ማንም ዕቃ ተሸክሞ በመቅደስ እንዲያልፍ አልፈቀደም” /ማር.11፥16/ የሚሉት ኃይለ ቃላት ይህንኑ ድርጊቱን የሚያስረዱን ናቸው፡፡ 
እንዲሁም ቤተ መቅደስን የመንጻት ሥርዓት በፈጸመበት ወቅት ካስተላለፋቸው መልእክታት አንዱ የጥንቱ የመስዋዕት አቀራረብ ሥርዓት ማክተሙን ማወጅ ነበር ስለዚህም ለመሥዋዕት የቀረቡ በጎችንም እንዲያወጡ አዘዘ፡፡ እውነተኛው የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕትም እርሱ መሆኑንና ጊዜው መድረሱን አጠየቀ ከፊቱ መንገዱን ሊያዘጋጅ በኤልያስ መንፈስ ይመጣል የተባለው መጥምቁ ዮሐንስም “እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት በተደጋጋሚ ያወሳው ስለዚህ ነበር /ዮሐ.1፥29 እና 36/፡፡ ጌታችንም ቢሆን በመዋዕለ ሥጋዌው ስለ ኦሪት አንዳንድ ሥርዓቶችን ማለፍ ለሐዋርያትና ለሚከተሉት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር “ኦሪትም ነቢያትም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ድረስ ነበሩ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ ይጋፋል፡፡” /ሉቃ.16፥16 “ከኦሪት አንዲት ቃል ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል” እንዳለ ጌታችን በቃሉ፡፡ ምክንያቱም እርሱ ያስተማረው ወንጌል ጥንት በመጻሕፍተ ነቢያት የተገኘ ስለነበረ ነው፡፡ 
እንግዲህ ቅዱስ ያሬድ ከደረሳቸው የዜማ ድርሳናት ውስጥ በዐብይ ጾም የሚዜመው ጾመ ድጓ የዓብይ ጾም ሳምንታትን በ9 ከፋፍሎ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ጽሑፋችን ምኩራብ ስለተሰኘው ሳምንትና ጌታችን በቤተ መቅደስና በምኩራብ እየተገኘ ስላስተማረባቸው ጊዜያት የምናስብበትን ጾሙን በቃለ እግዚአብሔር አስረጅነትና ሕይወትነት የሥርዐቱን ፍጹም መንፈሳዊነት ተረድተን የምንጾመው ነው፡፡ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለት ዕለት በቤቱ የሚነገረውን ቃሉን ለመስማትና ለመተግበር ያበቃን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።