በሊቀጠበብት ሐረገወይን አገዘ
(ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት መጋቢት 2002)
ሥርዐት ምንድን ነው?
“ወንድሞች ሆይ፡ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሔድ ወንድም ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን። …በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዐት አልሔድንምና። “2ኛ ተሰ. 3፡ 6። ሥርዐት የሥነ ፍጥረት ሕይወት ምሕዋር፣ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ነው። የመዓልቱ በሌሊት፣ የሌሊቱ በመዓልቱ በመሠልጠን ሥርዓተ ዑደትን እንዳይጥስና የመዓልቱ በመዓልቱ የሌሊቱ በሌሊት እየተመላለሰ ዕለታዊ ግብሩን እንዲያከናውን ማንኛውንም ፍጡር ፈጣሪው በሥርዐት አሰማርቶታል። መዝ. 105፡19-24። በተለይ መንፈሳዊያን ልዑካን መንፈሳዊውን ተልእኮ ያለ ሥርዓትና ያለ ሕግ ማካሔድ እንደማይችሉና እንደማይገባም ሐዋርያው አስተማረ። ያለ ሥርዐት ከሚካሔድ ወንድም ተለዩ” አለ።
ስለሆነም በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ እሴቶች ከዚህ ኃይለ ትምህርት የተገኙ መሆናቸውን እያሰብን በሰሙነ ሕማማት የሚከናወኑ የሕማማት ሥርዐቶችን ቀጥለን እንመለከታለን።
ሰሙነ ሕማማት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዕለተ ትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በማለት ታከብረዋለች። የዚህ ስያሜ መነሻም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራው፣ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበረው የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ ወቅትም የሚታሰብበት ስለሆነ ሰሙነ ሕማማት ተብሏል። የዚህ ጾም መነሻም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ላይ ተደንግጓል። ጥንታዊ ቀዳማዊ መሆኑም ይታወቃል።
በሕማማት የማይፈቀዱ
ዐውደ ምኩናን |
በዚህ በሰሙነ ሕማማት ሳምንትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለየት ያለ የአገልግሎት ሥርዐት ሠርታለች ከጸሎተ ሐሙስ በቀር ቅዳሴ አይቀደስም። ይህ ብቻ አይደለም። የዘወትር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሆነው ሥርዐተ ጥምቀተ ክርስትና፣ ሥርዐተ ፍትሐት፣ ሥርዐተ ማኅሌት፣ሥርዐተ ተክሊልና ሌሎችም የተለመዱ አገልግሎቶች አይካሔዱም። በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታህ ማለት የለም።በአጠቃላይ ከዓመት እስከ ዓመት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለምዕመናን ይሰጡ የነበሩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች አቁመው በሌላ ወቅታዊ ማለትም የጌታችንን ሕማሙን መከራውን መከሰሱን መያዙን ልብሱን መገፈፉን (ተአስሮ ድኅሪት)
በጲላጦስ አደባባይ መቆሙን፤ መስቀል ላይ መዋሉን ሐሞት መጠጣቱን እና ሌሎችንም ለኅጢአተኛው የሰው ልጅ ሲባል የተከፈለውን ዕዳ በሚያስታውሱ አገልግሎቶች ይተካሉ።እነዚህንም ሥርዐታዊና ምስጢራዊ የሰሙነ ሕማማት አገልግሎቶች ከዕለተ ሆሳዕና እስከ ቀዳም ሥዑር ድረስ እንዴት እንደሚከናወኑ በኣጭር በአጭሩ እንመለከታለን።
ዕለተ ሆሣዕና
ሆሣዕና በአርያም ማለት በአርያም/በሰማይ/ ያለ መድኃኒት ማለት ነው። ጌታችን በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ስለሆነ የከበረ በዓሉ ምስጋና በዋዜማው ይጀመራል። ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ካህናቱ “በእምርት ዕለት በዓልነ፣ በታወቀ የበዓላችን ቀን ከበሮ ምቱ” በማለት የዋዜማውን ምስጋና ቀለም እጅግ ሰፊ ስለሆነ በዚህ መዘርዘር አይቻልምና ከዋዜማው ፍጻሜ በኋላ ያለውን ሥርዐት እንመለከት።
ተአስሮ ድኅሪት
|
በዝምታ የሰነበቱት ከበሮና ጸናጽል የምሥጋናው ባለ ድርሻዎች ይሆናሉ በዚህ የተጀመረው ማኅሌት ሌሊቱን ሙሉ አድሮ መዝሙር በሚባለው… ምስጋና በኩል አድርጎ ሥርዐተ መወድስ ተደርጎ ሰላም በተባለ የምስጋና ማሳረጊያ ይጠናቀቃል።
ሥርዐተ ዑደት ዘሆሣዕና
ሥርዐተ ማኅሌቱ ተፈጽሞ ሥርዐተ ቅዳሴው ከመጀመሩ በፊት እስከ አሁን ከነበረው ሥርዐት ለየት ያለ ሆኖ እንመለከታለን። ይኼውም ሊቃውንቱ የዕለቱን ድጓ እየቃኙ እየመሩና እየተመሩ፣ ዲያቆኑ ከመዝሙረ ዳዊት የዕለቱን በዓል የተመለከተ ምስባክ በዜማ እያሳመረ፣ ካህናቱ በዓሉን የተመለከተ ወንጌል በአራቱም መዓዘን እያነበቡ ቤተ መቅደሱን አንድ ጊዜ ይዞሩታል።ለምሳሌ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ባለው በር ፊት ለፊት በመቆም መምህሩ “አርእዩነ ፍኖቶ ወንሑር ቤቶ፤ ወደቤቱ እንገባ ዘንድ መንገዱን አሳዩን፡፡” የሚለውን ድጓ ይቃኛሉ ካህናቱ እየተከተሉ ያዜማሉ ዲያቆኑ “ዘመሩ ለእግዚአብሔር ዘየሐድር ውስተ ጽዮን ፤ በጽዮን የሚገለጥ እግዚአብሔርን አመስግኑ” እያለ ያዜማል፡፡ ካህኑም በማቴዎስ ወንጌል 21÷1-13 ያለውን ኀይለ ቃል ያነባል፡፡በዚህ አይነት መልክ በአራቱም መዓዘነ ቤተ ክረስቲያን ሥርዐተ ዑደቱ ይፈጸማል፡፡
ይህን ሥርዐት ሊቃውንቱ ሲተረጉሙት አንደኛ ጌታችን በአህያ ውርንጫ ተጭኖ በሕፃናት አንደበት እየተመሰገነ ኢየሩሳሌም የገባበትን የምሥጋና ጉዞ ለማመልከት ሲሆን ሁለተኛ ሕገ ወንጌል በአራቱም መዓዘነ ዓለም ለሕዝብ ለአሕዛብ መዳረሱን ለማመልከትና ሕዝብና አሕዛብ በሕገ ወንግል አንድ አካል ማሆናቸውን በገቢር ለማሳየት መሆኑን ያስተምራሉ፡፡
ሥርዓተ ቅዳሴ ዘሆሣዕና
በዕለተ ሆሣዕና አሁንም የቅዳሴው አገባብ ሥርዓት ከሌሎች ዕለታት ለየት ያለ መሆኑን እንመለከታለን ዲያቆናቱ ሕብስቱን በመሶበ ወርቅ ወይኑን በጽዋዕ ይዘው በምዕራብ በር በኩል ይቆማሉ ሠራኢው ዲያቆን በዜማ አሰምቶ “አርኅው ኈኀተ መኳንንት አለቆች ደጆችን /በሮችን/ ክፈቱ” ይላል፡፡ ካህኑም በመንጦላዕት ውስጥ ሆኖ “መሉ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው” ብሎ ይጠይቃል ዲያቆኑም “ይህ የክብር ንጉሥ የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር ነው” ብሎ ይመልሳል ዲያቆኑ ሦስት ጊዜ የከፈቱልኝ ጥያቄያዊ ዜማውን ካዜማ በኋላ ካህኑ “ይባዕ ንጉሠ ስብሐት፤ የክብር ንጉሥ ይግባ” ብሎ ፈቅዶለት ይገባል፡፡
ይህንንም አበው እንደሚከተለው ያመስጥሩታል አንደኛ ቅዱስ ገብርኤልና ወላዲተ አምላክ በምሥጢረ ብስራት ጊዜ የተነጋገሩት እንደሆነና በመጨረሻም ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ፣ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ መቀበሏን ሲያሳይ ሁለተኛው ፈያታይ ዘየማንና መልአኩ ኪሩብ በማእከለ ገነት የተነጋገሩትን በድርጊት ለማሳየት መሆኑን ያስተምራሉ፡፡ ዋናው ምሥጢር ግን ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሊገባ ሲል ብዙዎቹ እንዳይገባ ቢፈልጉም ከፊሎቹ ግን እንዲገባ መፍቀዳቸውን ያሳያል፡፡
እንደተለመደው ሥርዐተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ እግዚአ ሕያዋን /የሕያዋን ጌታ/ የሰኘው ጸሎት በካህናት ተደርሶ ለምእመናን ሥርዐተ ፍትሐት ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሥርዐተ ፍትሐት ስለማይደረግ፡፡ በሰሙነ ሕማማት የማይከናወኑ ምሥጢራት በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡
ምእመናንም ተባርኮ የተሰጣቸውን የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ወደየቤታቸው ያመራሉ የዘንባባው ምሥጢር የተጀመረው በታላቁ አባት በአብርሃም ነው፡፡ ኩፋ.13፡21 ይህን የአባታቸውን ሥርዐት አብነት አድርገው እስራኤል የኤርትራን ባሕር ሲሻገሩ፣ ዮዲት ድል በአደረገች ወቅት ዘንባባ እየያዙ እግዚአብሔርን አመስግነውበታል። ጌታችን በዕለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም ሽመግሌዎችና ሕፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እንደተቀበሉት እናነባለን፡፡ሉቃ.12፡ 8
ኢትዮጵያውያን ምእመናንም ክርስቶስ የሰላም የነጻነት የድኅነት አምላክ መሆኑን ለመመስከር ዘንባባውን ይዘው ወደቤታቸው ይሄዳሉ፤ እንደቀለበት ያሠሩታል፤ያሠሩታልም። አሁን ደግሞ ወደ ሌሎች ዕለታት ሥርዐት አንሻገር፡፡
ዕለተ ሰኑይ/ሰኞ/ በነግህ
ከሁሉም በፊት የሰዓቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል በዕለቱ ተረኛ መምህር /መሪጌታ/ የዕለቱ ድጓ ይቃኛል:: ድጓው ከአራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋር እንዲስማማ ሆኖ ነው የሚቃኘው ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ የድጓው መሪ መምህር ሰኞ በቀኝ ከሆነ ማክሰኞ በግራ በኩል ባለው መምህር ይመራል እንዲህ እየተዘዋወረ ይሰነብታል ድጓው ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ከተዘለቀ በኋላ፡-
ተእህዘ በእደ አይሁድ |
ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም አማኑኤል አምላኪ
ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዘ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡
ኦ እግዚእየ ኢየስስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም::
ኀይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኮቴት እየተባለ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ 12 ጊዜ ማለት ነው በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ /በንባብ/ ይደገማል፡፡ከዚያ በመቀጠል
ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዘ እስከ ለዓለመ ዓለም ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡
ለመንግሥቱ፣ ለሥልጣኑ፣ ለምኩናኑ፣ ለኢየስስ፣ ለክርስቶስ፣ ለሕማማ፣ /ለዓርብ ለመስቀሉ/ ይደሉ እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ ይጀምራል በመጨረሻ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱሰ ይነበባሉ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር መስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ የተባለው ጸሎት በካህኑ ሲነበብ ምእመናንም አቤቱ ይቅር በለን እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡
ከዚያም ሁለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል፡፡ ዜማው የሚጀመረው አሁንም በቀኝ በግራ በመቀባበል ነው፡፡ አንዱ ይመራል ሌላው ይቀበላል፡፡ እንዲህ በማለት
ኪርያላይሶን/5 ጊዜ/ በመሪ በኩል
ኪርያላይሶን/2 ጊዜ/ ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል
ኪርያላይሶን ታኦሰ ናይን
ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን
ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን
ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን
ኪርያላይሶን አማኑኤል ናይን
ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን
በዚህ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል። በመጨራሻም በግራ በቀኝ በማስተዛዘል አርባ አንድ ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል። ከላይ የተጠቀሱት የጌታችን ኅቡዓት ስሞች ናቸው። ኪራላይሶን ማለት አቤቱ ይቅር በለን ማለት ነው። በመቀጠል መልክአ ሕማማት በሊቃውንት ይዜማል ፤ከዚያም ካህኑ ፍትሐት ዘወልድ፣ ጸሎተ ቡራኬ፣ ወዕቀቦሙ፣ ኦ ሥሉስ ቅዱስ፣ ኦ ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ፣ ነዋ በግዑ የተሰኙ ምንባባትን እያፈራረቁ ያነባሉ። ካህኑም በጸሎታቸው ፍጻሜ 41 ኪራላይሶን በሉ ብለው መልእክት ያስተላልፋሉ። ሕዝቡም መልእክቱን ተቀብሎ ይጸልያል። ዲይቆኑም “ሑሩ በሰላም እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ፤ ንዑ ወተጋቡኡ ውስተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ሠልስቱ ሰዓት ”ብሎ ያሰናብታል።
አሁን የተመለከትነው ሥርዓት ሰኞ በነገህ/በጠዋት/ የሚከናወነውን ነው። በሦስት፣ በስድስት፣ በዘጠኝ፣በአስራ አንድ ሰዓት የሚከናወነው ሥርዓትም አሁን በተመለከትነው መሠረት ነው። የሚለያዩት ምንባባቱ ብቻ ናቸው። የሰሙነ ሕማማት ዜማም ከሰኞ እስከ ረቡዕ ግእዝ፣ ሐሙስ አራራይ፣ ዓርብና ቅዳሜ እዝል ነው። አሁን በተመለከተነው መሠረት ሰኞ ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ ከምንባባቸው በቀር ከላይ በተመለከትነው አኳኋን ሥርዓታቸው ይፈጸማል።
አሁን የተመለከትነው ሥርዓት ሰኞ በነገህ/በጠዋት/ የሚከናወነውን ነው። በሦስት፣ በስድስት፣ በዘጠኝ፣በአስራ አንድ ሰዓት የሚከናወነው ሥርዓትም አሁን በተመለከትነው መሠረት ነው። የሚለያዩት ምንባባቱ ብቻ ናቸው። የሰሙነ ሕማማት ዜማም ከሰኞ እስከ ረቡዕ ግእዝ፣ ሐሙስ አራራይ፣ ዓርብና ቅዳሜ እዝል ነው። አሁን በተመለከተነው መሠረት ሰኞ ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ ከምንባባቸው በቀር ከላይ በተመለከትነው አኳኋን ሥርዓታቸው ይፈጸማል።
ወስብሐት ለእግዚአብሄር
ቃለ ህይወትን ያሰማልን የአገልግሎት ዘመናችሁን ይባርክልን!!!
ReplyDelete