Nov 30, 2015

††† የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት †††
ከአርባ ሁለት ጊዜ በላይ ስሟ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ሀገር ቅድስት ኢትዮጵያ በእግዚአብሔርየተወደደች ለመሆኗ ነቢያቱ መስክረዋል፡፡ ከነቢያት አንዱ አሞፅም፤ «የእስራኤል ልጆች ሆይ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን ?» ብሎ እግዚአብሔር መናገሩን ጽፏል /9÷7/፡፡ ከሁሉም ከፍ ባለመልኩ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት፤ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» ብሎ ሕዝበ ኢትዮጵያ እደ ሕሊናውን እና እደ ልቡናውን ዘወትር በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ በጾምና በጸሎት፣ በምጽዋትና በትሩፋት፣ ዘርግቶ በሃይማኖት ጸንቶ፣ በምግባር ቀንቶ የሚኖር በመሆኑ፤ ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር ምድሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር ተብለዋል፤ /መዝ.68÷31/፡፡
ለታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ዋናው ምክንያት በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው የሠመረ ግንኙነት ነው፡፡ ይኽም በመሆኑ የንግሥት ሳባ እና የንጉሥ ሰሎሞን ግንኙነት ሰፊውን ታሪክ ይዞ ይገኛል፡፡የንግሥተ ሳባ ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረው ታምሪን ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ንጉሥ ሰሎሞን ያሠራውን ቤተ መቅደስ ዓይቶ፣ የሰሎሞንን ጥበባዊ ዝና ሰምቶ በፍጹም መደነቅ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ ያየውንና የሰማውን ለንግሥቲቱ አጫወታት፡፡ እሷም የሰማችውን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ የሰሎሞንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበብ ተመልክታ እግዚብሔርን አመስግና ተመለሰች፡፡
ከንጉሥ ሰሎሞን ምኒልክን ፀንሳ ከኢየሩሳሌም ተነሥታ ባሕረ ኤርትራን ተሻግራ፣ ሐማሴን አውራጃ ስትደርስ አሥመራ ከተማ በሚገኘው ማይበላ ከተባለው ቦታ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ የሕፃኑንም ስም የንጉሥ ልጅ ስትል «እብነ መለክ» አለችው፡፡ ይኽ ስም በዘመን ሒደት ምኒልክ ተብሎ ተለወጠ፡፡
ምኒልክ ተወልዶ በአእምሮ እያደገ ሲሔድ አባቴ ማን ነው ? አድራሻውስ ወዴት ነው ? እያለ ጥያቄ ቢያበዛባት በሃያ ሁለት ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ላከችው፡፡ ምኒልክም አባቱ ንጉሥ ሰሎሞንን አግኝቶ ሕገ ኦሪትንና የዕብራይስጥ ቋንቋ ሲያጠና ከቆየ በኋላ፤ ዐሥራ ሁለት ሺሕ እስራኤላውያንን አስከትሎ ከምድረ እስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ጉዞውን አቀና፡፡
ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ለጉዞ የተነሡ ዕብራውያን ከቤተሰቦቻቸው መለየታቸው ሳያሳዝናቸው ከታቦተ ጽዮን መለየታቸው እጅግ ከበዳቸው፡፡ ወዲያው በፈቃደ እግዚአብሔር ታቦተ ጽዮንን ከመንበሯ አንሥተው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ወደ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡
ቀዳማዊ ምኒልክ እና እስራኤላውያን ታቦተ ጽዮንን ይዘው አክሱም የደረሱት ኅዳር 21 ቀን ነበር፡፡ ንግሥተ ሳባም የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በጣም ስላስደሰታት በክብር ተቀበለቻቸው፡፡ «ወአንበርዋ ውስተ ሕፅነ ደብረ ሀገረ ማክዳ» እንዲል በአክሱም ከተማ መካከል ደብረ ማክዳ /ዛሬ ቤተ ጊዮርጊስ ከሚባለው/ ላይ ደብተራ ኦሪት ሠርተው አስቀመጧት፡፡
እንኳን ለእናታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ለድንግል ማርያም አመታዊ ክብር አደረሳችሁ!
በበዓሉ በረከት ትባርከን::

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።