ዕእምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሓተ፡፡ በእንተ ጸላዒ፡፡ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ፡፡መዝ።፹÷፪
አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካሪያስ እንደተነገረው ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያያቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል’ ዘካ።፱፣፱። በማለት እንደሚመጣና የሠላምንም ብሥራት እንደሚያበሥር ተናገሮ ነበር። ሲመጣም ‘ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት።’’ በማለት ሊደረግለት የሚገባውን ገልጿል። ፪ኛ ነገ። ፱፣፩፫ ። የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ መዝ።፩፩፯፣፪፮ በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይታደላል። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ የቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ። ፪፩፣፩፡፩፯)፤ የቅዱስ ማርቆስ፣(ማር።፩፩፣፩፡፲)፤ የቅዱስ ሉቃስና (ሉቃ።፩፱፣፪፱፡፫፰)፤ የቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ።፩፪፣፩፪፡፩፭) ወንጌላት ይነበባሉ ። ታዲያ አኛ ይህን ዐቢይ በዓል የምናከብረው እንዴት ነው፧ በነቢያቱ ከላይ እንደተገለጠው በወንጌላቱም አንደተፈጸመው እርሱ ወደ እኛ የሚመጣበት ጊዜ መቼ ነው፧ ሲመጣስ ምን እናድርግ፧ የእግዚአብሔርን መምጫ ጊዜ ማሰብና መዘጋጀት ያለብን እንዴት ነው፧ ምክንያቱም በዓሉ ከምንም በላይ የሚጠቅመን ለእኛ ነውና ። ስለዚህ ይህን በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ልንተገብረው ይገባል።
ትርጉም፦ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፡፡ ስለ ጠላት÷ ጠላትንና ግፈኛን ታጠፋው ዘንድ፡፡
ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መገቢያ ዋዜማ ነው። ሆሣዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ስም በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ… ‘ ወዘተ። በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።
አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካሪያስ እንደተነገረው ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያያቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል’ ዘካ።፱፣፱። በማለት እንደሚመጣና የሠላምንም ብሥራት እንደሚያበሥር ተናገሮ ነበር። ሲመጣም ‘ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት።’’ በማለት ሊደረግለት የሚገባውን ገልጿል። ፪ኛ ነገ። ፱፣፩፫ ። የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ መዝ።፩፩፯፣፪፮ በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይታደላል። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ የቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ። ፪፩፣፩፡፩፯)፤ የቅዱስ ማርቆስ፣(ማር።፩፩፣፩፡፲)፤ የቅዱስ ሉቃስና (ሉቃ።፩፱፣፪፱፡፫፰)፤ የቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ።፩፪፣፩፪፡፩፭) ወንጌላት ይነበባሉ ። ታዲያ አኛ ይህን ዐቢይ በዓል የምናከብረው እንዴት ነው፧ በነቢያቱ ከላይ እንደተገለጠው በወንጌላቱም አንደተፈጸመው እርሱ ወደ እኛ የሚመጣበት ጊዜ መቼ ነው፧ ሲመጣስ ምን እናድርግ፧ የእግዚአብሔርን መምጫ ጊዜ ማሰብና መዘጋጀት ያለብን እንዴት ነው፧ ምክንያቱም በዓሉ ከምንም በላይ የሚጠቅመን ለእኛ ነውና ። ስለዚህ ይህን በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ልንተገብረው ይገባል።
ለጌታ የማያስፈልግ ፍጥረት የለም ይልቁንም የክብር ዘውድ አድረጎ በመልኩ የፈጠረው ሰው ያስፈልገዋል።ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ ማንም የለም።እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ዓላማና ዐቅድ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር የሚከብርበትን ሥራ ልንሠራ ይገባል።አህያ በሰው ሰውኛ ሲታይ የንቀትና የውርደት ሲመስል ይችላል ።የአህያን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ግን
፩። በለዓም በሥጋዊ ገንዘብ መንፈሳዊ ዓይኑ ታውሮ እግዚአብሔር ያልረገማቸውን እስራኤላውያንን ሊራገም ሲሄድ እስራኤላውያንን እንዳይራገም ለመንገር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ በሚሄድበት መንገድ ላይ ቆሞ ሳለ ከበለዓም ይልቅ ያየችው የበለዓም አህያ ነበረች ። አህያይቱም መልአኩን አክብራ መንገዱን እንደለቀቀችለት ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ዘኅ።፪፪፣፪፫።
፪። በትንቢተ ኢሳያስ ፩፣፫ ‘ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጪ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እሥራኤል ግን አላወቀም’’ እንደተባለው ጌታ በተወለደ ጊዜ ትንቢቱን ምሳሌውን የሚያውቁ እሥራኤላውያን ባላወቁ ባለተቀበሉ ሰዓት በዚያ በብርድ ወራት እናቱ የምታለብሰው ልብስ አጥታ ቅጠል አልብሳው በነበረ ጊዜ ለጌታ ሙቀት የገበሩለት እረኞቻቸውን ተከትለው የመጡ ከበቶች ላሞችና አህዮች ናቸው። ‘ወአስተማወቅዎ አድግ ወላህም’’ እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም።።
፫። በሆሣዕና ዕለት ከሌሎች እንስሳት ይለቅ ጌታን ለመሸከም ለከብር የተሸከመችው አህያ ናት። ጌታን የተሸከመችው አህያ ከዚያ በፊት ያላየችውና ያልተደረገላት ክብር ተደርጉላታል። አህያ ከዚህ በፊት ለኛ እህል ተሸክማ ስትሄድ ሂጂ እያልን በዱላ እንደበድባት ነበር፡ ነውም። ነገር ግን በሆሣዕና ዕለት እንኳን በዱላ ልትደበደብ ቀርቶ ሰዎች በእርሷ ላይ ለተቀመጠው ጌታ ሲሉ ልብሳቸውን ሁሉ እያነጠፉላት በንጣፍ ላይ ተራምዳለች ።
ስለዚህ ክርስቶስ በአህያይቱ ላይ እንዲቀመጥባት ልብስም አንደ ተጎዘጎዘላት እኛም ጌታ በፀጋውና በረድኤቱ እንዲያድርብን ልባችንን ከኃጢአትና ከተንኮል አንጽተን ፍቅርንና ትሕትና ልንጎዘጎዝ ይገባል።ጌታ በኛ ላይ በፀጋው ሲያድር በእርሱና በቅዱሳኑ ዘንድ ያለን ክብርና ፀጋ ታላቅ ነው። በነገር ሁሉ መከናወን ይሆንልናል።ክርስቶስን በመሸከሟ የአህያይቱ ታሪክ እንደተለወጠ ሁሉ በክርስቶስ ማደሪያነታችን ያለፈው መጥፎ ታሪካችን ይለወጣል።እንግዲህ በእለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሕዝቡ ሁሉ በደስታ በዝማሬ እንደ ንጉሰ እንደተቀበሉት እኛም ሀሴትን አድርገን ‘ሆሣዕና እምርት እንተ አቡነ ዳዊት…’’ በማለት እናመሰግናለን። ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን።አሜን።
ሰሙነሕማማት
ከሆሣዕና ማግስት ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ዋዜማ ያለው ሳምንት ሰሞነ ሕማማት ይባላል። ይህ ሳምንት በክርስቶስና በአይሁድ መካከል ያለው ፍጥጫ የመጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሰበት ብዙ ስድብን የተሸከመበት፣የተንጓጠጠበትና ከዚያም አልፎ የተሰቀለበት ሳምንት ነው። ቤተክርስቲያናችን በእነዚህ ቀናት ውስጥ የጌታን መከራና ሞት የሚያስታውሱ ምንባባት ከቅዱሳን መጻሕፍትና ድርሳናት ተውጣጥተው በግብረ ሕማማት ይነበባሉ ።ምዕመኑም ስግደት ይሰግዳሉ ። አዳም ከፈጣሪው ተጣልቶ የኖረውን የጨለማና የመከራ ዘመን በማስታወስ መንበረ ታቦቱ በጥቁር ልብስ ይሸፈናል። ልብሰ ተክህኖውም ጥቋቁር ነው። በዚሁ ከሆሣዕና ምሽት ጀምሮ ሳምንቱን የዓመተ ፍዳ መታሰቢያ ቀናት ስለሆነ ጸሎተ ፍትሐት አይደረስም። ጌታችን በቢታንያ ሳለ ይሁዳም ጌታውን አሳልፎ እንዴት እንደሚሰጥ ከእነርሱ ጋር ሲያሴርና ምን እንደሚሰጡት ሲደራደር የነበረበትን ሳምንት እኛ ግን ሳምንቱን በሙሉ ‘…ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ዓለመ ዓለም …’’ እያልን እንዘምራለን። አምላካችን ክርስቶስ እንደ ወንበዴ ተይዞ በጴንጠናዊው በጲላጦስ በሄሮድስ በቀያፋና በሀና ፊት ሊፈረድበት ሲቆም እኛም ከእርሱ ጋር ቆመን አሁንም ‘…ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከዓለመ ዓለም …’’ በማለት እናወድሰዋለን። ስለ ህማሙ ስንወያይ ጌታችን በሥጋ በተገለጸበት ጊዜ መንገላታት የደረሰበት በዚህ ሳምንት ብቻ አየደለም ፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ዓለም ኑሮው መንገላታት ደርሶበታል። ‘የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው።’’ ኢሳ።፭፫፣፫ ድካሙ በአንድ ሳምንት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በምድር እያለ ጊዜውን በመከራ አሳለፈ። ይህ ሳምንት ግን በተለዬ ሁኔታ የእርሱ ሥቃይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ነው።
ይህ ሳምንት በብርሃንና በጨለማ መካከል ከፍተኛ ትግል የተካሄደበት ጊዜ ነው ። በመጀመሪያ ጨለማው ብርሃንን ጠልቶት ገፋው፤ሰዎች ሥራቸውን ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ ።ወደኋላ ግን ጨለማ ብርሃንን የሚከስትበት ብርሃንም በብርሃንነቱ የሚጠላበት ሰዓት መጣ። በአጠቃላይ ችግሩ የብርሃንና የጨለማ ትግል ነው። ይህም ትግል በጌታችን በመዋዕለ ስብከቱም በግልጽ ይታይ ነበር በጣም የሚደንቀው ግን ይህን ትግል አምላካችን አልተቃወመውም። ‘ተጨነቀ፣ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሽላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አለከፈተም።’’ ኢሳ። ፭፫፣፯። ጌታ ሆይ የክፉዎችን ሥራ በአርምሞ ተቀብለህ ወደ ስቃይ ወረድህ። እየሰደቡና እየገፉ በመስቀል አዋሉህ። ይህም ግሩም የሆነውን ኃይልህ ክብርህን ምስጋናህን ለዘላለም እንዳንናገር አያግደንም ። አንተ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆንክ በተረዳ ነገር እናውቃለን። ስለዚህ እንዲህ እያልን እንዘምራለን ‘።።ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እከለዓለመ ዓለም…’’ ክርስቶስ በሚሰደብበት በሰሞነ ህማማት እኛ ባሪያወቹ ግን እንዲህ እንላለን ‘ጌታ ሆይ እኛ አንተን እናውቅሃለን ።አንተ ለእኛ አንግዳ አይደለህም ። እነዚህ ሰዎች አንተ ደካማ እንደሆንክና በእነርሱ እጅ እንደወደቕ ይገምቱ ይሆናል። በፈጹም እኛ የማይነገረውን የአንተን ኃያል እናውቃለን ። አንተ በበሽታዎች ላይ ኃይል ያለህና ሁሉን የምትፈውስ ነህ።በአጋንንት ላይ ሥልጣን ያለህና የምትገስጸው ነህ። በፍጡራን ላይ ሁሉ የሰለጠንክ ኃያል ጌታ ነህ። ማእበሉን የገሰጥክ ንፋሱን ጸጥ ያደረግህና በፈሳሹ ላይ የተራመድክ ግሩም አምላክ ነህ። ሁሉም ለአንተ ይገዛሉ። እኛ ኃይል እንዳለህና ሁሉን እንደምትችል እንረዳለን። በሰሞነ ሕማማት ያለው ሐሙስ ጸሎተ ሐሙስ ፤ ዓርብ ደግሞ ስቅለተ ዓርብ (ጌታ የተሰቀለበት) ፤ ቅዳሜ ደግሞ ቅዳም ስዑር ይባላሉ።
ጸሎተ ሐሙስ
ጸሎተ ሐሙስ ጌታ በፍጹም ትሕትና የሐዋርያትን እግር ያጠበበትና ግብር ያገባበት የምሥጢረ ቁርባንን ሥርዓት ያስተማረበት በመሆኑ በቤተክርስቲያን ምሳሌውን የተከተለ ልዩ ትውፊታዊ ሥርዓት ይካሄዳል።በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያናችን ሥረዓት የግብረ ሕማማቱ መጽሐፍ እንደሚያዘው ቅዳሴ ይቀደሳል። ከቅዳሴው ቀደም ብሎ የደብሩ ወይም የገዳሙ አስተዳዳሪ ወገቡን በአጭር ታጥቆ ከወይን ቅጠል ጋር የተቀላቀለውን ማይ በብርት አድርጎ በጌታ አምሳል የካህናቱንና የምእመናኑን እግር በማጠብ ትሕትናን ያስተምራል።ከቅዳሴም በኋላ ምእመናኑ የተዘጋጀውን ዳቦ ጉልባን በአንድነትና በፍቅር ይመገባሉ።
ስቅለት
ይህ በዓል መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዓለም ቤዛ በመልእልተ መስቀል የተሰቀለበት የዕለተ ዓርብ መታሰቢያ ሆኖ ከትንሣኤ በፊት ባለው ዓርብ ይከበራል ። በዚህ ዕለት ምእመናንና ካህናት በአንድነት በቤተክርስቲያን ይሰበሰባሉ።አጎበር ይሠራል ።ንዋያተ ቅዱሳት ይደረደራሉ ቀለም ያልገቡ ጸሊማን (ጥቋቁር) አልባሳት ይለብሳሉ። ሕማማተ መስቀሉን የሚያወሱ ምንባባት ይነበባሉ፣ስግደት በሰባቱ ጊዜያት ይሰገዳል። በመጨረሻ ካህናት የጌታን ግርፋት በማሳሰብ በወይራ ቅጠል የምእመናንን ትከሻ ቸብ ቸብ መታ መታ በማድረግ የማሰናበቻ ስግደት እየሰጡ ሕዝቡም ስግደቱንና ጸሎቱን እያደረሰ ወደ ቤቱ ይመለሳል።
ቀዳም ስዑር
ቅዳም ስዑር ማለት የተሻረ ቅዳም ማለት ነው፡፡ ትርጓሜውም እሑድ ቅዳሜ መጾም የማይገባ ሆኖ ሳለ ጌታ በከርሠ መቀብር በማደሩ ምክንያት በአከፍሎት ስለተጾመ ቅዳም ስዑር ይባላል። በዚህ ዓመታዊ ዕለት ምአመናንና ካህናት በቤተክርስቲያን ይሰበሰባሉ። ’’ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ።’’ አየተባለ ለሕዝቡ ቄጠማ ይታደላል። የምሥራች ምልክት ነው። ካህናት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ቃጭል ይዘው በእየቤተ እየዞሩ የምሥራቹን ቄጠማ ይሰጣሉ ። ሕዝቡም ለመግደፊያ የሚሆን ገንዘብ ይሰጣል። ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ በክርስቶስ ሞትም በኃጢአት ምክንያት የመጣው ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች የመወገዱ ምሳሌ ነው። እንግዲህ በስጋው ሰው ሆኖ የጎበኘን በባሕርይው ልዑል የሆነው ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተመሰገነ ይሁን።
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።