Apr 8, 2011

የዐቢይ ጾም ፯ኛ ሳምንት (ኒቆዲሞስ)


                       የዐቢይ ጾም ፯ኛ ሳምንት (ኒቆዲሞስ)
ዮሐ። ÷፩፡፩፩
ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው÷ “መምህር ሆይ÷ ልታሰትምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና፡፡ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልምአለው፡፡ ኒቆዲሞስም÷ “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ ወመለድ እንደምን ይችላል፧ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን፧አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው÷ “እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ ስለአልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደ ወደደው ይነፍሳልና፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደመጣ ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የሚወለድ ሁሉ እንዲሁ ነው፡፡ኒቆዲሞስም መልሶ÷ “ይህ ሊሆን እንዴት ይቻላል፧አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን እንዴት ይህን አታውቅም፧አለው።
በዚህ የሰባተኛ የአብይ ጾም ሳምንት አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀንና ሌሊት ወንጌልን ያስተምር እንደነበረና በዘመኑ የነበረው የሕግ ሰው ኒቆዲሞስ በጌታ ትምህርት እጅግ ተማርኮ ሳለ ቀን ቀን ወደ ጌታ ዘንድ እየመጣ እንዳይማር አይሁድ ይቃወሙኛል የሚል ፍራቻ ስላደረበት ሌሊት ሌሊት እየመጣ ከጌታ ዘንድ እንደተማረ ይነገርበታል። በተለይም ታላቅ የሕግ መምህር የተባለው ኒቆዲሞስ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ አይችልም ብሎ ጌታ ያስተማረው ትምህርት እጅግ እንደከበደውና እንረዳበታለን።
ከዚህ ትምህርት እያንዳንዳችን የምንረዳው የመንፈስን ነገር ለማወቅ መንፈሳዊ መሆን እንደሚገባ እንጂ የዓለም ዕውቀት ያለው እና በምርምር ብቻ የእግዚአብሔርን ነገር አውቃለሁ ማለት አለመቻሉን ነው። ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያስተምረናል፦
“እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው፧ እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው፧ እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።፩ኛ ቆሮ።፪፡፭፡፲፮

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።