ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በእውነት ተነሥቷል፡፡ ሲነሣም ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሥጋውን የገነዙበትን ከተልባ እግር የተሠራ ንጹሕና ድርብ በፍታ የመግነዝ ጨርቅ (ከፈን) በመቃብር ትቶ ነው፡፡ መተዉ ብቻ ሳይሆን በፍታው በመቃብሩ ውስጥ በጣም በተሰናዳ መልኩ ተቀምጦ ነበር፡፡ ወንጌል ስለዚህ ነገር እንዲህ ትላለች ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ በገባ ጊዜ ‹‹በራሱ ላይ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምቶ እንዳልነበረ አየ›› (ዮሐ20.7)
ለመሆኑ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ መግነዙን በመቃብር በዚህ መልኩ ትቶ የመነሣቱ ምሥጢር ምንድር ነው@ ይህን በሚገባ መረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ ምክንያት የተቀመጠ አንድም ቃልና ፊደል እንዲሁም የተከናወነ ትንሽ ተግባር እንኳን እንደሌለ ያስረዳናልና በአትኩሮት እናንብበው!
1ኛ. ኢየሱስ ክርስቶስ የመግነዙን ጨርቅ (ከፈኑን) በመቃብር ትቶ የሄደው ከዚህ በኋላ ሞት እንደሌለበት ሊያስረዳን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሲናገር ‹‹ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት ምትም ወደፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና›› ይላል፡፡ (ሮሜ6.9)
እስኪ አልዓዛርን ተመልከቱ! ኢየሱስ ክርስቶስ ከአራት ቀን በኋላ ከሞት ሲያስነሣው እንዴት ነበር? ኢየሱስ ክርስቶስ‹‹አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና›› ብሎ ጠራው፡፡ ያን ጊዜ የሞተው አልአዛር ‹‹እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደተጠመጠመ ነበር፡፡›› (ዮሐ11.43-44) አልዓዛርን ያስነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የተነሣው በራሱ ሥልጣንና ፈቃድ ነው፡፡ ‹‹ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፡፡›› (ዮሐ10.16-17) አልዓዛርን የገነዙትና ከግንዘቱም የፈቱት ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ፍቱትና ይሂድ›› ብሎ አዟቸዋልና፡፡ (ዮሐ11.44ሐሐ) ኢየሱስ ክርስቶስን የገነዙት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ናቸው፡፡ ሲነሣ ግን መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ አላለም፡፡ አልዓዛር ከመቃብር ከነመግነዙ ወጣ ይህም ዳግመኛ ወደ ሞት መሄዱን ያመለክታል፡፡ መግነዝ የሞት ዕቃ ነውና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መግነዙን ትቶ ወጣ፡፡ ዳግመኛ መሞት በእርሱ ዘንድ የለምና፡፡ ስለዚህ መግነዙን በመቃብር ትቶ መነሣቱ ዳግም ሞት እንደማይገዛው ማሳያ ነበር፡፡
2ኛ. አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈኑን በመቃብር መጣሉ ከሞት በኋላ ያለውን ክብር ያሳያል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጧል፡፡ እንኳን የመግነዝ ጨርቅ ምድራዊ ልብስ እንኳን አያስፈልገውም፡፡ ሰዎች በዚህ ዓለም ሲኖሩ ልብስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፈጣሪ ለአዳም የቁርበት ልብስ ያለበሰው ስለዚህ ነው፡፡ (ዘፍ3.21) በዚህ ምክንያት ሰዎች እንደየክብራቸው እና እንደየሙያቸው ተለይተው የሚታወቁበትን ልየ ልዩ ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ከሞት በኋላ ግን ይህ ሁሉ አያስፈልግም፡፡ ልብሱም ክብሩም ሰማያዊ ነውና፡፡
ወደ ሰማይ ለሚወጣ ሰው ልብስ ምን ያደርግለታል? ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል ተማሪው ኤልሣ ይከተለው ነበር፡፡ በመጨረሻም መምህሩ ለተማሪው ምን እንደሚፈልግ ጠየቀው፡፡ በአንተ ያለ መንፈስ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይደርብኝ ባለው ጊዜ መጎናጸፊያውን (ልብሱን) ጥሎለት ወደ ሰማይ ወጣ፡፡ (2ነገ2.12) በቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት እንደምናገኘው ወንጌላዊ ዮሐንስም ሲሰወር ከቆመበት ስፍራ የተገኘው ጭራው፣ ልብሱና፣ ጫማው ነው፡፡ ወደ ሰማይ ሲወጡ ልብስ አያስፈልግም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ከሰማይ ነው፡፡ ሲመጣ እንደ እኛ ልብስ አስፈለገው፡፡ ስለዚህ ለብሶ ኖረ፡፡ ከሙታን ሲነሣ መኖሪያው ሰማይ መሆኑን ሲስረዳን የሞት ዕቃ የሆነውን ከፈኑን ትቶ ከመቃብር ወጣ፡፡
3ኛ. ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሞትን አጠፋልን፡፡ ከእንግዲህ በኋላ በክርስቶስ ባሪያዎች ዘንድ ፍልሰት እንጂ ሞት የለም፡፡ ስለዚህ ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ@ ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ?›› እያልን ከነቢያትና ከሐዋርያት ጋር በሞት ላይ እንዘምራለን፡፡ (ሆሴ13.14፤ 1ቆሮ15.55) ሞትን እንደ እንቅልፍ እንቆጥራለን እንጂ አንፈራውም፡፡ የሞት ፍርሃትና የመቃብር ጨለማ ከኛ ተወግደዋልና፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ ሲኦል ተበዘበዘች፡፡ መቃብር ተበረበረች፡፡ ማስፈራቷ ቀረ፡፡ በመቃብር ያለ ጨለማ በክርስቶስ ተወገደ፡፡ መላእክት ነጫጭ ልብስ ለብሰው ገብተው ተቀመጡባት፡፡ መቃብር ወደ ሕይወት ማለፊያ መንገድ እንጂ ሌላ ምንም አይደለችም፡፡ ሴቶች ጎበኟት፣ እነ ጵጥሮስ እነ ዮሐንስ ተመላለሱባት፡፡ እነዚህ ሁሉ ከእኛ ጋር ሳሉ መቃብር ምን ያደርገናል?
ስለዚህ ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን እንደ እንቅልፍ እንድንቆጥረው ወዳጁ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ‹‹አልዓዛር አንቀላፍቷል›› ብሎ በመናገር አሳየን፡፡ (ዮሐ11.11) ራሱም ስለ እኛ ሞትን ቀምሶ ‹‹ከእንቅልፍ እንደሚነቃ››ሰው ተነሥቷል፡፡ (መዝ77.65) ከእርሱ የተማረ ሐዋርያው ሉቃስም የሐዋርያት ሥራን ሲጽፍ ስለ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት ሞተ ላለማለት ‹‹አንቀላፋ›› ሲል ጽፏል፡፡ (የሐዋ7.60) እግዲህ ምን እንላለን በዚህ ሐሳብ የክርስቶስ የሆኑ ሁሉ ተባብረዋል፡፡ ስለሞቱ ሰዎች አትዘኑ ለማለት ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹አንቀላፍተው ስላሉት›› ሰዎች ያለ አግባብ አትዘኑ ሲል የዚህ እምነት ተጋሪ መሆኑን አሳይቷል፡፡ (1ተሰ4.13)
ሞት እንቅልፍ ከተባለ መቃብር ምን ሊሆን ነው@ መኝታ ቤት ነዋ! እንደምትሉኝ ጥርጥር የለውም፡፡ ልክ ነው! ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብርን በፍቅር ኃይል አሸነፋት፡፡ ዋለባት አደረባት ከዚያ በኋላ ማስፈራራቷን ተወች፡፡ ለቅዱሳን ዝግጁ መኝታ ክፍል አደረጋት፡፡ የመግነዙን ልብስ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ሰዎች አንጥፎላቸው ሄደ፡፡ በሞት ምክንያት የሚያዝኑ እንዳያዝኑ ዕንባቸውን የሚያብሱበት ፎጣ ከመቃብር ተወላቸው፡፡ ይህችውም ከፈኑ ናት!
ሰው መኝታ ቤቱን እንዴት ይፈራል? ቤተሰቦቹን ሲያይ የሚደነግጥ ማን ነው? በመቃብር የሚገኙ ምስጥና ትል ሁሉ ከቤተሰብ አባል እንደ አንዱ ናቸው፡፡ እንደዚህም ባናከብራቸው ባደፈ ልብስ ከሚገኙ ተባዮች ተለተው አይታዩም፡፡ ቅዱስ ኢዮብ ግን ‹‹መብስበስን፡- አንተ አባቴ ነህ፡፡ ትልንም አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ ብያለሁ፡፡›› ይለናል፡፡ (ኢዮ17.14) ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ መግነዙን ጥሎ ከመቃብር የወጣው ሞት በቅዱሳን ዘንድ የማይፈራ፣ መቃብርም እንደ መኝታ ክፍል የሚቆጠር መሆኑን ሲያመለክተን ነው፡፡
4. እንደሚታወቀው አይሁድ መነሣቱን ለማስካድ ‹‹ተሰረቀ›› የሚል ወሬ አስወርተው ነበር፡፡ ይህም ወሬ ‹‹እምነት›› እስከመሆን የደረሰና ብዙዎችን የሳበ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ መግደላዊት ማርያም የመሳሰሉትን ጽኑዓን የሃይማኖት አርበኞችን እንኳን ለጊዜው ጠልፎ ለመጣል የቻለ ወሬ ነበር፡፡ ‹‹ጌታዬን ሰርቀውታል›› እያለች ታለቅስ የነበረው ስለዚህ ነው፡፡ (ዮሐ20.2) ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አስቀድሞ ስለሚያውቅ የመግነዝ ልብሱን በመቃብር ትቶ ተነሣ፡፡ በዚህም ‹‹ተሰረቀ›› የሚለውን የአይሁድ ወሬ ከንቱ አደረገባቸው፡፡
እንኳን በዚያን ዘመን አሁንም ቢሆን መቃብር ሊበረብር የመጣ ሌባ ሳጥኑን፣ ልብሱንና የመሳሰለውን ቁሳቁስ ወስዶ ሥጋውን ትቶ ይሄዳል እንጂ ልብሱን ትቶ ሥጋውን ይዞ አይሄድም፡፡ ልብሱን ትቶ ሥጋውን የሚፈልግ ጅብ ወይም ሌላ አውሬ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ሥጋውን ሌባ ሰርቆት ቢሆን ኖሮ ልብሱን ትቶ አይሄድም ነበር፡፡ እንደ መቃብሩ ሁሉ ልብሱም እኮ አዲስ ልብስ ነው፡፡ ያውም ከተልባ እግር የተሠራና ውድ ዋጋ የወጣበት፡፡ መጽሐፋችን ስለ ዮሴፍ ‹‹በፍታም ገዝቶ አውርዶም በበፍታ ከፈነው›› ይለናልና፡፡ (ማር15.46) የአምላካችን የዘወትር ልብሱም ሆነ ከፈኑ ምእመናን ሊዳብሱትና ሊድኑበት የሚመኙት ልብስ ነው፡፡ ለዚህ አሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረችውን ሴት ብቻ ማስታወስ ይበቃል፡፡ (ሉቃ8.43) የኢየሱስ ክርስቶስ ልብስ እንኳን ምእመናን ሰቃዮቹ የአይሄድ ጭፍሮች እንኳን ‹‹አንቅደደው ነገር ግን ዕጣ እንጣጣልበት›› (ዮሐ19.24) እያሉ የሚጣሉበት ልብስ ነው፡፡ ዛሬም እንኳን ቢገኝ በሚያምኑ ዘንድ መድኃኒት በማያምኑ ዘንድ ደግሞ ቅርስ እና የገቢ ምንጭ መሆኑ የማይካድ ነው፡፡ ታዲያ ሌባ ይህንን ውድና ክቡር ልብስ ትቶ እንዴት ይሄዳል? ዛሬ ያ ልብስ የት ይገኛል በምን መልኩ የሚለውን ታሪካዊ ሂደቱን ለእናንተ ትቼዋለሁ!
አንድ ሰው አይሁድ ሥጋውን የፈለጉበት ምክንያት ነበራቸው ስለዚህ ሥጋውን የሚሰርቅ ቡድን አዘጋጁና ወሰዱት ከዛም ‹‹ተሰረቀ›› የሚል ወሬ አስወሩ፡፡ ሥጋውን መውሰድ ከፈለጉ መብታቸው አይደለምን? ሊል ይችላል፡፡ መብታቸው ሊሆን ይችላል ነገር ግን በአይሁድም ሆነ በኢትዮጵያውያን ሬሳን ዕርቃኑን የመሸከም ልማድ የለም፡፡ እንኳን የሞተን ሰው የተኛን ሰው እንኳን ተራቁቶ ቢያዩት ልብስ ጣል ያደርጉበታል፡፡ ይኸውም በኖኅ ታሪክ ይታወቃል፡፡ (ዘፍ9.23) ስለዚህ ሥጋውን ለመስረቅ የመጡት ሰዎች ከፈኑን ትተው ዕርቃኑን ተሸክመው ወሰዱት ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡
እንዳይደረስባቸው ቸኩለው ስለነበር ነው እንኳን እንዳይባል ልብሱ በጣም በተዘጋጀ መልኩ የተቀመጠ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ እንደሚተርከው ‹‹የተልባ እግሩ ልብስ›› ለብቻው በራሱ የነበረው ጨርቅ ደግሞ ‹‹ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደነበረ›› ተቀምጦ ነበር፡፡ (ዮሐ20.7) የችኮላ ጉዳይ ቢሆን የተረባበሸ ነገር እንጂ እንዲህ በሥርዓቱ የተሰናዳ ነገር ባልታየ ነበር፡፡ ቸኩለው ከነበረ ሌቦቹ ልብሱን በዚህ መንገድ አጣጥፈው ወይም በሥርዓት ጠምጥመው ጥለዉት ሄዱ ለማለት አይቻልም፡፡ ይህ ሁሉ ጌታችን በሥልጣኑ እንደተነሣ ከዛም በኋላ ከእንቅልፉ የተነሣ ሰው እንደሚያደርገውና መኝታውን እንደሚያነጥፍ ሰው አሰናድቶ ከመቃብር እንደወጣ ያሰረዳናል፡፡
5ኛ. ዳግመኛም ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመግነዙን ልብስ በመቃብር ትቶ መነሣቱ ለእኛ ትምህርት ነው፡፡ ትንሣኤ ዳግም ልደት ነው፡፡ ሰው ደግሞ ልብስ ለብሶ አይወለድም፡፡ ክርስቶስ ከመቃብር ያለ ልብስ ተወለደ፡፡ የመግነዝ ጨርቁን ጥሎ ተነሣ ማለቴ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ትንሣኤ የንስሐ ማሳያ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈኑን በመቃብር ትቶ መነሣቱ እኛ የንስሐ ትንሣኤ ስንነሣ ወይም ንስሐ ስንገባ ከእኛ ጋር ያልተፈጠረ በላያችን የደረብነውን ትርፍ ዓመላችንን ውልቅ አድርጎ መጣል እንዳለብን ያሳየናል፡፡
መቃብር እኮ ዓለም ናት፡፡ የእርስዋ የሆነውን በእኛ ዘንድ ካገኘች ትስበናለች፡፡ ጌታችን እንዳስተማረንም ዓለም የእርሷ የሆነውን ትወዳለች ትፈልጋለች፡፡ ስለዚህ ንብረቷን ሙጭጭ አድርገን ይዘን ዓለምን ለምን መጣሽ ብንል ቀልድ ነው፡፡ የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን በዝሙት ለመጣል ጥረት አደረገች፡፡ አልሸነፍ ባላት ጊዜ ልብሱን ይዛ ጎተተችው እርሱ ግን ልብሱን ትቶላት ሮጠ፡፡ (ዘፍ39.12-13) ስንወለድ ለብሰን ካልተወለድን ልብስን ያገኘነው ከዓለም ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ሐተታ ውስጥ ልብስ ምሳሌነቱ ለዓለማዊ ጠባይና ኃጢአት ነው፡፡ ስለዚህ የዓለም ገንዘብ በእኛ ዘንድ አይኑርብን፡፡ ንስሐ እንግባ ከዓለም የተማርነውን ኃጢአት ለዓለማውያን ትተን ክርስቶስን እንምሰል!
ምንጭ: ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
hibretyes@yahoo.com
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።