May 27, 2011

“ኢይብቁል ብክሙ መሪር ሥርው (መራራ ሥር አይብቀልባችሁ)”ዕብ.12፡15

አብርሃም ልጆች ነን የሚሉ ነገር ግን የአብርሃምን ሥራ የማይሠሩና የነቢዩ ዳዊት ልጆች ነን የሚሉ የእርሱን ፈለግ የማይከተሉ ዕብራውያንን ቅዱሱ ጳዉሎስ «መራራ ሥር አይብቀልባችሁ» ሲል መከራቸው፡፡ ዕብራውያን በእግዚአብሔር እናምናለን፤ የእሱ ልጆች ነን እያሉ ይመጻደቁ ስለነበሩ መልካም ሥራ በመሥራት ወደ እግዚአብሔር እንዳይቀርቡ የከለከላቸውን መራራውን ሥር እንዲያስወግዱ አሳሰባቸው፡፡ ሁሉን የሚያይና የሚያውቅ አምላከ ሰማይ ወምድር ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ውጫቸውን ያሳመሩ ነገር ግን ውስጣቸውን በኃጢአት ያሳደፉትንና በመራራ ሥር የተመሰለው ኃጢአት በውስጣቸው የበቀለባቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን ሲገስጽ «እናንተ ግብዞች ጻፎች፤ ፈሪሳዉያን በውስጡ ቅድሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ ወዮላችሁ፡፡» ብሏቸውል፡፡ /ማቴ.2325/
ኃጢአትን በሐልዮ ጸንሶ በነቢብ መውለድ፣ በነቢብ ወልዶም በገቢር ማሳደግ መራራ ሥር ነው፡፡ /ማቴ.2416/ ይህም ማለት ኃጢአትን ማሰብ አስቦም ሥራ ላይ ማዋል በአጠቃላይ በኃጢአት መውደቅ በሰው ልቡና ውስጥ የሚበቅል መራራ ሥር ነው፡፡ በዚህም «ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ» /ዘዳ.1819/ የተባለውም የሰው ልጅ በመራራ ሥር፣ በሐሞትና በእሬት የተመሰለውን ኃጢአት ከሕይወቱ ካላራቀ መራራ ገሀነመ ዕሳት እጣ ፈንታው ይሆናል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ሐሳቦች በሙሉ መራራ ሥር የተባለው ኃጢአት መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም እስኪ በሕይወታችን ውስጥ ሊነቀሉ የሚገባቸው ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለዩንን መራራ ሥሮች በዝርዝር እንመልከት፡፡
፩፦
ዝሙት
ዝሙት አእምሮን የሚያጐድል፣ ሰላምን የሚነሣ፣ ጤንነትን የሚያሳጣ፣ ሕይወትን የሚያበላሽ፣ ጸጋ እግዚአብሔርን የሚያሳጣ /የሚገፍፍ/ በሰው ልቦና ውስጥ የሚበቅልና መነቀል ያለበት መራራ ሥር ነው፡፡ ብዙ ታላላቅ አባቶች ክብራቸውን ያጡት በዝሙት እንደሆነ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ፡- እስራኤላዊያን ከሞአብ ልጆች ጋር በማመንዘራቸው ብኤልፌጐር የሚባል ጣዖት እንዲያመልኩ አደረጓቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔርን በማስቆጣታቸው 24 ሺሕ ሕዝብ በአንድ ቀን ተቀስፏል፡፡ /ዘፍ.2237 ዘኁ.271/ «ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል» እንደተባለው፡፡ /ምሳ.221/
ዝሙት፣ ሴሰኝነትና አመንዝራነት ቅድስናን ከሚያሳጡ ታላላቅ ኃጢአቶች ውስጥ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ በእነዚህ ኃጢአቶች እንዳይወድቅ እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን አዋቂ ነውና አንድ ለአንድ በመወሰን ጸንቶ እንዲኖር ጋብቻን ባርኮ ቀድሶ ሰጥቶታል፡፡ «መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፣ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡» እንዲል፡፡ /ዕብ.134 1ቆሮ.71/ ዝሙት ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለይ መራራ ሥር ነው የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሶምሶንም ጸጋውን እንዲገፈፍ ያደረገው ይህው በውስጡ የበቀለው መራራ ሥር ነው፡፡ /መሳ.171/ ይህ ታላቅ ሰው ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ቢሆንም አንድ ናዝራዊ ማድረግ የሌለበትን የዝሙትን ተግባር ፈጽሞ በመገኘቱ ከክብሩ ተዋርዷል ኀይሉ ተነፍጎታል፡፡ /ዘኁ.61/ ዛሬም ትእዛዛተ እግዚአብሔርን በመጣስና ዝሙት በመሥራት ከክብር እየተዋረድን ያለን ሰዎች ራሳችንን ልንመረምርና መራራውን ሥር በንስሐ በጣጥሰን በመጣል ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ ይገባል፡፡ ለሶምሶን እግዚአብሔር አምላክ ታላላቅ ውለታዎችን ቢውልለትም፤ እሱን ያስጨነቀው አምላክ ያደረገለት ውለታ ሳይሆን ከደሊላ በዝሙት የመውደቅ መንፈስ አእምሮውን አሳጥቶት ነበር፡፡ /መሳ.1617/ ይህች ሴት ቃሏን አጣፍጣ የዚህን የተመረጠ ሰው ሕይወት እንዳጠመደችው ዛሬም የብዙዎቹን ሕይወት በዝሙት የሚያጠምዱ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸው መራራ ሥር የበቀለባቸው እንዳሉ ማስተዋል ይገባል፡፡
ከክብራችን እንዳንዋረድ የቅዱሳን አባቶቻችንን ፈለግ በመከተል ሥጋችንን ለነፍሳችን አስገዝተን መኖር ያስፈልጋል፡፡ ዓይኖቻችን ወደ ቅዱስ ሥጋውና ወደ ቅዱስ ደሙ የሚመለከቱ መሆን አለባቸው፡፡ «ልጄ ሆይ ወደ ጋለሞታ ሴት ልብህ አይባዝን በጐዳናዋ አትሳት፡፡ ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፡፡» /ምሳ.724/ በዝሙት ተወግተው ከወደቁት ወገኖች እንዳንደመር በየትኛውም ቦታ ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡
፪፦ ትዕቢት
ሳጥናኤልን ያህል ታላቅ መልአክ ከክብሩ ያዋረደው ሌላው መራራ ሥር ትዕቢት ነው፡፡ ትዕቢት በመራራ ሥር የተመሰለውም ከኔ በላይ ማን አለ በማለት የማይገባውን ይገባኛል እያሰኘ ሌላውን የመናቅ፤ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ መራራ መንፈስ ስለሚያበቅል ነው፡፡ «አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ አንተ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፣ ዙፋኔንም ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ አልህ፡፡ ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጉድጓድም ጥልቅ ትወርዳለህ፡፡» /ኢሳ.1412-16/ ብሎ የተናገረለት ሳጥናኤል በትዕቢቱ ምክንያት ነው፡፡ «ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም፡፡» /መዝ.35/ ተብለ የተነገረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልናስብ ይገባል፡፡
ይሁን እንጂ ትናንት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ቅዱስ ሥጋውንና ቅዱስ ደሙን እየበላና እየጠጣ አድጎ በትዕቢት ምክንያት የበላበትን ወጭት ሰባሪ የሆነ ብዙ ነው፡፡ ክርስቲያን ነኝ እያለ በሀብቱ በጉልበቱ በእውቀቱ፣ በወገኑ የሚኩራራና የሚታበይም አለ፡፡ ይሁን እንጂ ሀብታሙ በደሃው ላይ፣ የተማረው ባልተማረውላይ አሠሪ በሠራተኛው ላይ የሚታበይ ከሆነ ክርስቲያን ነው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ፤ ያለው የሌለውን መርዳት፣ የተማረውም ላልተማረው ደሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ማለት፣ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲባል ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የማገልገል ጸጋ ቢሰጠንም በቸርነቱ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል እንጂ ልንታበይ አይገባም፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናገለግል ሁሉ የምናቀርበው የአገልግሎት መስዋዕት በእግዚአብሔር ቸርነት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ልክ «... የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ፡፡» እንደተባለ፡፡ /ሉቃ.171/
ስለዚህ ፈሪሃ እግዚአብሔር ሊኖረን እንጂ ልንታበይ አይገባም፡፡ «እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው፡፡» /ምሳ.224/ እንዳለ ጠቢቡ በምሳሌው፡፡
 ፫፦ ማስመሰል
መመሳሰልና መስሎ መታየት፣ ለመመሳሰል መጣር የብዙዎች ችግር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳች ፍሬ ባገኝባት ብሎ ወደ አንዲት ዛፍ ሲጠጋ ፍሬ ያፈራች መስላ እንጂ አፍርታ ባለመገኘቷ ምክንያት ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ ወዲያውም ደረቀች፡፡ /ማቴ.2118/
ከዚህ ኀይለ ቃልም የምንረዳው በመስሎ መኖርና ሆኖ አለመገኘት የሚያመጣውን ርግማን ነው፡፡ ማስመሰል መራራ ሥር ነውና ሊነቀል ይገባዋል፡፡ ዛሬም ብዙ ሰው በአፉ የሃይማኖት ሰው ይመስላል፣ እውነታው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያን የሚሔዱ ጾም የሚጾሙ፣ ነገር ግን ከኃጢያት ያልተለዩ፣ በንስሐ መመለስን ችላ የሚሉ፣ ታቦት ሲነግሥ እልል ስለተባለ ብቻ እልል የሚሉ ከዚያ ሲወጡ ግን ኃጢአት ለመሥራት የሚጣደፉና በልባቸው የሸፈቱ ሰዎች የማስመሰሉን መራራ ሥር ከውስጣቸው በንስሐ ነቅለው መጣል አለባቸው፡፡ ሆኖ መገኘት እንጂ መስሎ መታየት አያድንምና፡፡ «ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከኔ በጣም የራቀ ነው፡፡ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል፡፡» /ኢሳ.2913 ማቴ.58/ እንደተባለው ዛሬም የብዙ ሰው አምልኮ የዚህ ትንቢት መፈጸሚያ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ጥዋት ቤተ ክርስቲያን፤ ከሰዓት ቤተ ጣኦት በመሔድ ጊዜን በከንቱ ከማሳለፍ መቆጠብ ያሻል፡፡ ክርስቲያን ነኝ እያለ ጨሌውን፣ የዐውደ ነገሥቱን ጥንቆላ ማመን፣ መናፍስትን መጥራትና የመሳሰሉትን እየፈጸሙ መገኘት በልብ መሸፈት ነውና ልንመለስ ይገባል፡፡ «በሰማያት ያለው የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ የሚሉኝ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡ አይደሉም፡፡» /ማቴ.721/ ተብሏልና፡፡
 መስለው ለመኖር የሞከሩ ብዙ ሰዎች ሲጎዱ እንጂ ሲጠቀሙ አላይንም፡፡ ግያዝ ከኤልሳዕ ጋር መስሎ ሲኖር ልቡ ግን ወደ ገንዘብ ሸፍቶ ስለነበር በለምጽ ተመታ፡፡ /2 ነገ.52/ የይሁዳንም ታሪክ ስንመለከት ከሐዋርያት ጋር ተመሳስሎ እየኖረ ልቡናው በፍቅረ ንዋይ ተነድፎ እንደነበር ነው፡፡ እናም እነዚህንና የመሳሰሉትን የፍቅረ ንዋይ፣ የስስት፣ የእምነት ጎደሎነት ወዘተ መራራ ሥሮች በቶሎ በንስሐ መነቃቀል ያስፈልጋል፡፡
 ካህኑም፣ ዲያቆኑም፣ ሰባኪውም፣ ዘማሪውም በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነኝ የሚል ሁሉም አገልግሎቱ ዋጋ የሚያገኘው ከእግዚአብሔር መሆኑን ከልብ በማጤንና ራሱን በመመርመር የጐደለውን ሊያስተካክል ይገባል፡፡ እያንዳንዷ ሥራችን የምትበጠርበት ጊዜ ይመጣልና፡፡ «መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፡፡ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደሥራቸው መጠን ተከፈሉ፡፡ ... እያንዳንዱ እንደሥራው መጠን ተከፈለ፡፡» እንዲል፡፡ /ራእ.2ዐ፡12/
 ስለዚህ መልካም ዋጋ ለማግኘት መልካም ሥራ ለመሥራት መጣር ይገባል፡፡ «አምላካችሁ እግዚአብሔርን ተከተሉ እርሱንም ፍሩ ትእዛዙንም ጠብቁ ቃሉንም ስሙ እርሱንም አምልኩ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ» /ዘዳ.134/ ስለተባልን ለመልካም ሥራ እሺ እንድንል ያስፈልጋል፡፡ «እሺ ብትሉ፣ ለእኔም ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምጹ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህንን ተናግሯል» ተብሏልና፡፡ /ኢሳ.119/
፬፦ ዓላማ ቢስነት
ዓላማ የሌለው ሰው ከየት ተነሥቶ ወዴት መሔድ እንዳለበት የማያውቅ፣ ካሰበበት የማይደርስ ነው፡፡ ማንም ወደነዳው የሚነዳ፣ በጭፍን የሚጓዝ ሰው ዓላማ ቢስ ሊባል ይችላል፡፡ ዓላማ የሌለው ሰው በጀመረውና በተሠማራበት ተግባር ላይ ጸንቶ አይቆይም፡፡ በተለይ ክርስቲያን ዓላማ ከሌለው በትንሽ ነገር የሚፈተን፣ ሥጋዊ ፍላጐቱ ካልተሟላለት የማያገለግል፣ የሚያማርር፣ በሆነ ባልሆነው የሚያኰርፍ፣ መንፈሳዊነትን ያዝ፣ ለቀቅ የሚያደርግ የጸሎቱ፣ የጾሙ ዋጋ ዛሬውኑ እንዲከፈለው የሚፈልግ ይሆናል፡፡ የሚያገለግልበትንም ዓላማ ያልተገነዘበ ሰው በየደቂቃው እንዲመሰገን ይፈልጋል፡፡ ሰዎች ዓላማቸውን እንዲስቱ በልባቸው ውስጥ የማዘናጋትን ተግባር የሚፈጽም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ቅዱሳን አባቶች በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፉም ዓላማን የመሳት መራራ ሥር በውስጣቸው አልበቀለም፡፡ በሁሉም ጸንተው በመቆማቸው ለክብር አክሊል በቅተዋል፡፡
ሙሴ እስራኤልን በምድረ በዳ ይመራ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ከዓላማው አልተዘናጋም፡፡ ይልቁንም ያህዌህ ንሲ /እግዚአብሔር ዓላማዬ ነው አለ እንጂ፡፡ /ዘዳ. 1215/ ዮሴፍ ጽኑ ዓላማ ስለነበረው የተዘጋጀለትን የዝሙት ግብዣ እምቢ አለ፡፡ /ዘፍ. 39/ ሶስና ልትሸከመው የማትችል የሚመስል ፈተና ቢያጋጥማት ንጽሕናዋን ክብሯን ጠብቃ፣ ለአምላኳ ታምና መኖርን ዓላማዋ ስላደረገች የመጣባትን ፈተና በጽናት፣ በታማኝነት፣ በንጽሕና በቅድስና ልታልፍ ችላለች፡፡ /መጽሐፈ ሶስና/
ኢዮብ ዓላማው እግዚአብሔር ስለነበር ይፈራረቅበት የነበረውን መከራ፣ ሥቃይና ችግር ሊያልፍ ችሏል፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ ተፈትኖ፣ ነጥሮ ታላቅነቱን አስመስክሯል፡፡ /ኢዮ.210/ በአንጻሩ ደግሞ ዓላማቸውን የሚያስት መራራ ሥር በውስጣቸው በመብቀሉ ምክንያት የተጐዱ ከክብራቸው ያነሡ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ሳኦልን ብንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ከሕዝበ እስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ቢሾመውም የቅንዓት መንፈስ በውስጡ ስለበቀለ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር ሲሠራ እናያለን፡፡ /1ኛሳሙ. 1191535/
ዛሬም ትናንት የቤተ ክርስቲያን ልጆች የነበርን፣ እግዚአብሔር ከፍ ስላደረገን፣ ስለሾመን ዓላማችንን የዘነጋን አንታጣምና ራሳችንን ልንመረምር ይገባል፡፡ ከዓላማችን እንድንስት የሚያዘናጉ ነገሮች በርካቶች ናቸው፡፡ ሰው ለገንዘብ፣ ለሥልጣን፣ ለሓላፊ ጠፊ ሀብት ብሎ ዓላማውን ይስታል፡፡ ይሁዳ ምንም እንኳን ከሐዋርያት አንዱ ሆኖ ቢቆጠርም ዓላማው መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ሳይሆን ገንዘብን ማሳደድ ስለነበረ አምላኩን እስከ መሸጥ ደረሰ፡፡ «እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ፡፡» ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመበት፡፡ /መዝ.4ዐ፡9/ ይሄው ዛሬ የነፍሰ ገዳዮችና የክፉዎች ተምሳሌት ሆኖ ይነገራል፡፡ ስለዚህ «ከመልካም ሽቱ መልካም ስም ይሻላል፡፡» እንደተባለ ስማችን በክፉ እንዳይጠራ በዓላማችን እንጽና፡፡ /መክ. 71/ ዓላማችን መንግሥቱን ለመውረስ፣ ስሙን ለመቀደስ ይሁን፡፡ እንደ ዴማስ ወደ ዓለም የሚመለስ መራራ ሐሳብ በውስጣችን እንዳይበቅል ጥንቃቄ እናድርግ፡፡ /2ኛጢሞ. 49/
፭ ፦የጥርጥር መንፈስ
«የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባህርን ማዕበል ይመስላል፡፡ ሁለት ሐሳብ ላለው፣ በመንገድም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች የሚያገኝ አይምስለው፡፡» /ያዕ. 16/ በማለት እንደተነገረው ተጠራጣሪ ሰው ከጌታ አንዳች ነገር አያገኝም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከጽናታችን እንድንናወጥ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የተጠራበትን ዓላማ ጠንቅቆ የማያውቅ ክርስቲያን በጥርጥር ነፋስ ተነቅሎ ይገነደሳል፡፡ ስለዚህ ጊዜው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻው በመሆኑ በማስተዋል መራመድ ያስፈልጋል፡፡
 ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ይመጣ ዘንድ ስላለው ክህደትና ሐሳዊ መሲህ «... የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየተሳቡ የሚያጠፉ ኑፋቄን አሾልከው ያገባሉ፤ ... በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል፡፡» /2ጴጥ.21/ በማለት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የክርስቶስን አምላክነት የሚጠራጠርና የሚያጠራጥር፣ በቅዱሳን ላይ አፉን የሚከፍት ሐሳዊ መሲህ ቢነሣ የሚያስደንቅ መሆን የለበትም፡፡ ለምን ቢሉ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውና፡፡ ዮሐንስም ስለዚህ ነገር «አውሬው ታላቅ ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው ... እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም፣ በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ፡፡» ብሎ ጽፏል፡፡ /ራእ.13/
ስለዚህ በልባችን የሚበቅለውን የጥርጥር መንፈስ ከውስጣችን ነቅለን ልንጥል ያስፈልጋል፡፡ «ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፡፡ /2ጴጥ.317/ እንደተባልነው ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ መራራ ሥር ኃጢአትና ክርስቲያናዊ ምግባር በአንድ ሰውነት ላይ ሊበቅሉ የማይገባቸው እንክርዳድና ፍሬ ናቸው፡፡ በመሆኑም በንስሐ መከር መለየት ይኖርብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም የመራራ ሥራ ፍሬዎችን የሥጋ ሥራ በማለት ገልጿቸዋል፡፡ «አስቀድሜ እንዳልኩ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ብሏል፡፡ ገላ. 521» ስለዚህ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲያብብ የክፋት ሥራ የሆኑ ኃጢአቶችን በንስሐ እና በተጋድሎ በተለይም ዝሙት፣ ትዕቢት፣ ማስመሰል፣ ዓላማ ቢስነትና የጥርጥር መንፈስ የመሰሉ መራራ ስሮች በጥንቃቄ መንቀልና ማራቅ ያስፈልገናል፡፡ መራራ ሥሮችን ነቅለን የመንፈስ ፍሬያትን በሰውነታችን እናበቅል ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።