May 18, 2011

ቅዱስ ያሬድ


በግንቦት 11 ዕለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማህሌታይ ቅዱስ ያሬድ አረፈ::ይህ ቅዱስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነጹት አብያተ ክርስቲያናት ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው: እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተከበበ እና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት ::
የዚህ ቅዱስ አባት አዳም የእናቱም ስም ታውክሊያ ሲባሉ:: 512 በአክሱም ከተማ ተወለደ:: እናት እና አባቱም ልጃቸውን ለማስተማር ወደ ዘመዳቸው አባ ጌዴዎን ልከው እንዲማር አደረጉት : ይህም አባት አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊያስተምረው በጀመረ ግዜ መቀበልም ማጥናትም ተሳነው እስከ ብዙ ዘመንም መዝሙረ ዳዊትን ሲማር ኖረ ነገር ግን ከልቡ ማጥናትን እምቢ አለው:መምህሩም አብዝቶ ደበደበው ባሳመመውም ግዜ መታገስ ተሳነው ከአባቶቹ ቤትም ወቶ ዕብነ ሃኪም ወደተቀበረበት ገዳም ሄደ:: በውስጡም የወርቅ የብር የልብስ መቀመጫዎች የተመሉ ናቸው: ከአንዲትም ዛፍ አጠገብ ደረሰ ከዚያም አረፈ ትልም ወደ ዛፏ ሲወጣ አየ :ወደ ዛፊቱም እኩሌታ ደርሶ ወደ ምድር ይወድቃል :ሁለተኛም ተመልሶ ወደ ላይ ይወጣል መጀመርያ ወደ ደረሰበት ሲደርስ ይወድቃል:ሲወጣ ሲወድቅ ብዙ ግዜ ያደርጋል : ወደ ሌላ ቦታም አይሄድም ::
ከዚህም በኋላ በብዙ ጥረት በብዙ ትጋት በብዙ ድካም በዚያ ከዛፏ ላይ ወጣ:ከዚያችም ከዛፏ ላይ ተቀምጦ በላ :ቅዱስ ያሬድም ወደዚያ ዛፍ ላይ ይወጣ ዘንድ እንደሚተጋ ብዙ ግዜም ከላይ ሳይደርስ ከመካከል እንደሚወድቅ ከዚያም በኋላ በጭንቅ ወደ አሰበው እንደደረሰ የፈለገውንም እንዳገኘ የትሉን ትጋት ባየ ግዜ ሰውነቱን ግርፋቱን እንደምን አትታገሺም ህማሙንስ እንደምን አትችይም አላት መታገስንስ አብዝተሽ ኖሮ ቢሆን እግዚአብሄር በገለጠልሽ ነበር ይንንም ብሎ አለቀሰ ወደ መምህሩ ወደ ጌዲዮን ተመለሰ አባት ሆይ ይቅር በለን እንደቀድሞ ንገረኝ አስተምረኝም አለው:መምህሩ ጌዲዮንም እንዳልከው ይሁን አለው 150ውን መዝሙረ ዳዊት:መሃልየ ነብያትን :መሃልየ መሃልይን :የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ምስጋና ነገረው:81 መጻህፍትን ትርጓሜ የሌሎች መጽሃፍትን ቁትር እና የመሳሰሉትን መጽሃፍተ ሊቃውንት ሁሉ በአንድ ቀን አጥንቶ ፈጸመ::
ከዚህ በኋላ በብዙ ለቅሶ ወደ እግዚአብሄር በለመነ ግዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ግዜ የብሉይ እና የሃዲስ መጽሃፍትን ተምሮ ፈጸመና ዲቁና ተሾመ:በዚያም ወራት እንደዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማህሌት የለም ነበር በትሁት እንጂ :: እግዚአብሄርም መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ግዜ ከኤዶም ገነት 3 አእዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ እየሩሳሌም ሰማያዊት ከእነሱ ጋር አወጡት በዚያም 24 ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማህሌት ተማረ::
ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ግዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን 3 ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ:ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ :የፅዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም እንዴት እንደሚሰራት የድንኳንን አሰራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ:: ይህቺም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት:የቃሉንም ድምጽ በሰሙ ግዜ ንጉሱም ንግስቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋር የመንግስት ታላላቆች እና ህዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ሮጡ:ሲሰሙትም ዋሉ ከዚህም በኋላ ከአመት እስከ አመት በየክፍለ ዘመኑ በክረምት እና በበጋ:በመጸው እና በጸደይ:በአጽዋማት እና በባእላት :በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በአል በነብያት እና በሃዋርያት በጻድቃን እና በሰማእታት በደናግልም በአል የሚሆን አድርጎ በሶስቱ ዜማው ሰራ :ይህውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው::
የሰው ንግግር የአእዋፍ የእንሥሳትና የአራዊት ጩሀት ከነዚህ ከሶስቱ ዜማ አይወጣም :በአንዲት እለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉስ ገበረመስቀል እግር በታች ቆሞ ሲዘምር ንጉሱም የያሬድን ድምጽ እያዳመጠ ልቡ ተመስጦ የብረት ዘንጉን ወይም መቋምያውን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውሃ ፈሰሰ ያሬድም መሃሌቱን እስከሚፈጽም አልተሰማውም ነበር ንጉሱም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለከውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው ንጉስም በማለለት ግዜ ወደ ገዳም ሄጄ እመነኩስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሱም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሃላውን አሰበ እያዘነም አሰናበተው ከዚ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ በተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበርሽ እና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍ ያልሽ የብርሃን መውጫ የህይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና (አንቀጸ ብርሃን) እስከመጨረሻ በተናገረ ግዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ::
ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን ሃገር ሄዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ስጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ እግዚአብሄር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚ በኋላ ግንቦት 11 ቀን በሰሜን ተራራ አሁን ቅዱስ ያሬድ ገዳም ባለበት ቦታ ተሰወረ::
የአባታችን የአምሳለ ሱራፌል የሊቁ ማህሌታይ የቅዱስ ያሬድ ጸሎቱ በረከቱ ረድኤቱ በኛ በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ በሃገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም በእውነት ይደርብን::አሜን::

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።