May 18, 2011

መጽሐፍ ቅዱስ (ክፍል አንድ)

በኢ/////ክን ስርአትና ደንብ ተዘጋጅቶ በቦሌ ////ማርያም /ክን ሰንበት /ቤት ስለመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱሳን መጻሕፍት ዙሪያ በትምህርት ክፍሉ ተዘጋጅቶ ከቀረበው ትምህርት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የቀረበውን ትምህርት በተከታታይ እናቀርባለን፡፡
መግቢያ
‹‹በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም አፊ አዝዟልና መንፈሱም ሰብስቧቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም ›› ኢሳ 34÷16 ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የነፍስ ምግቦች ናቸው፡፡ ሰዎች ለቁመተ ስጋ ምግብና ውኃ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ነፍሳችን ደግሞ እንዲሁ ምግበ ነፍስ ያስፈልጋታል፡፡ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ምድራዊ ሕይወታችንን ጭምር እንዴትና በምን አኳኋን ማራመድ እንደሚገባን የሚያስተምር የሚመክርና የሚገስፅ መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው ታላቅ የሕይወት መመሪያ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርት ለተግሣፅ ልብንም ለማቅናት በፅድቅም ለሰው ምክር የሚጠቅም ስለሆነ 2 ጢሞ 3÷16 ከመጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ትርጉም አንስቶ ተከታታይ ትምህርቶችን እንሰጣለን፡፡
1.1 መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ምን ማለት ነው
 መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ሐረግ ‹‹መጽሐፍ›› እና ቅዱስ ከሚለው ሁለት ቃላት የተገኘ ሐረግ ሲሆን መጽሐፍ የሚለው ቃል ተጠቃሎ በአንድ ጥራዝ ስር የተሰበሰበ ጽሑፍን ሲገልጥ ‹‹ቅዱስ›› የሚለው ቃል በእብራይስጥ ክዱስ በሱርስት ካዲሽ በግእዝና በአረብኛ ቅዱስ ካለው ቃል የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም የተለየ የተከበረ ማለት ነው፡፡
 1.2 መጽሐፍ ቅዱስ ስለምን ቅዱስ ተባለ
1.      አስገኝው እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ቅዱስ ተብሏል፡፡
የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ቅዱስ ስለሆነ፡፡ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፡፡›› ዘሌ 1÷92
‹‹የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡›› 1       ጴጥ 1÷15
2.      ሰውን ወደ ቅድስና የሚያደርስ ስለሆነ ቅዱስ ተብሏል፡፡
የከበሩ መጽሐፍትን አምኖ መቀበል የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ነው፡፡
‹‹የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው፡፡›› ራዕ 1÷27
3.      በእግዚአብሔር መንፈስ የተነሳሱ ቅዱሳን ሰዎች የፃፉት በመሆኑ ፡፡
‹‹በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ እራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ 2 ጴጥ 1÷1-11
4.      የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊት ያለውን ሁኔታ በእርግጠኝነት የሚናገር በመሆኑ፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ የተከወነ ሁኔታ ሲገለጽ በይሆናል ወይም በግምት ሳይሆን በእርግጠኝነት ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ›› እንዳለ ዘፍ1÷1
5.      ወደፊት ስለሚመጣው በእርግጠኝነት የሚናገር ስለሆነ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ያለፈውን በእርግጠኝነት እንደሚያስቀምጥ ሁሉ የሚመጣውንም ድርጊት ያለምንም ጥርጥር በእርግጠኝነት የሚናገር በመሆኑ ልዩ ነው፡፡ ሌሎች መጻሕፍት ወደፊት ስለሚመጣው ነገር በእርግጠኝነት ሣይሆን የራሣቸውን መላምት በጥናትና በምርምር ወይም በግምት እንዴት እንዲ ሊሆን ይችላል ቢሉ እንጂ እንዲህ ይደረጋል ብለው በእርግጠኝነት አይናገሩም፡፡ ለምሳሌ ነብዩ ልዑል ኢሣይያስ ‹‹እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› ኢሳ 7÷14 አለ እንጂ ትፀንስ ይሆናል አማኑኤል ሊባል ይችላል አላለም፡፡
6.       የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ስለሚባርክ፡፡
ሌሎች መጻሕፍትን በማንበብ ምክርና እውቀት ይገኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ እና ቃሉን በመስማት ግን ቡራኬም ይገኛል፡፡ ራዕ 1÷3
7.      ዘመን የማይሽረው በመሆኑ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የማያረጅ የዘመን ብዛት የማይገታው ዘላለማዊ ነው፡
‹‹የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ፀንታ ትኖራለች›› ኢሳ 40÷8
‹‹ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም›› ማቴ 24÷35
‹‹የጌታ ቃል ለዘለአለም ይኖራል›› 1 ጴጥ 1÷25
8.      ክብረ ቅዱሳንን የሚዘክር ስለሆነ፡፡
ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስለቅዱሳን መላእክት ስለቅዱሳን ፃድቃን እና ሠማእታት የሚናገር ነው፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅድስ የመንፈስ ምግብ ነው፡፡ ማቴ 4÷4 ኤር 15÷16 የመንገዳችን መብራት ነው መዝ 118÷105 በሁለት በኩል የተሣለ ሰይፍ ነው፡፡ ዕብ 4÷12 ያንፃል ዮሐ 15÷3 ያለመልማል መዝ 1÷፡፡
ይቆየን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።