Oct 5, 2011

ወርኃ ጽጌ

ወርኃ ክረምት አልፉል፡፡ነጎድጓዱም ጸጥ ብሏል፡፡አእዋፍ ከየተሸሸጉበት ጉድባና ከሸሹበት ሀገር መሰብሰብ ጀምረዋል፡፡ ተራራውና ሜዳውም በአበባ አጊጦ ስጋጃ የተነጠፈበት መስሏል፡፡ተፈጥሮ እንዲህ ውብ ሆና በምትታይበት ወቅትም ቤተክርስቲያን ትምህርቷን ከወቅቱ ጋር አሰላስላና ሰምና ወርቅ አድርጋ ታቀርባለች፡፡ለዚህም አብነት የሚሆን ወርኃ ጽጌ ነው፡፡ ከመስከረም ፳፮  እስከ ታህሳስ ፳፭ ያለው ጊዜ መጸው ወይም ጥቢ ይባላል፡፡ይህ ወቀት ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡እነርሱም ጽጌ፣አስተምሮ እና ስብከት ይባላሉ፡፡ እያንዳንዳቸውም የየራሳቸው የሆነ ሰፊ ትምህርት አላቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የወርኃ ጽጌን ብቻ እንደሚከተለው እናያለን፡፡ ‹‹ጸጌ›› የሚለው ቃል ‹‹ጸገየ›› ካለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም አበባ ማለት ነው፡፡ በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ያሉት አርባ ቀናት ‹‹ዘመነ ጽጌ›› ይባላሉ፡፡ በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ዘመኑን አስመልክቶ ማኅሌት ይቆማል፤መዝሙር ይዘመራል፡

በዘመነ ጽጌ ሜዳው ሸንተረሩ በአበባ ያጌጣል፡፡ በክረምቱ ዝናብ አረንጓዴ ለብሳ የነበረችው ምድር የተለያየ ኅብረ ቀለም ባላቸው አበቦች ትሸፈናለች፡፡ ጫካው ኮረብታው በአበቦች መዓዛ ይታወዳል፡፡ ዓይን በቀለማቸው አፍንጫ በመልካም ሽታቸው ይማረካሉ፡፡ የሰው ልጆች በሀሴት ተመልተው ከቅዱስ ያሬድ ጋር በጣዕመ ዜማ ‹‹አሰርገዋ ለሰማይ በከዋክብት ወምድር በሥነ ጽጌያት›› ‹‹ሰማይ በከዋክብት ምድርንም በአበቦች ሸለማት አስጌጣት›› በማለት እግዚአግሔርን ያመሰግናሉ፡፡ ይህ ወር ጨለማው ክረምት አልፎ ጅረቱ የሚጎልበት ዘመድ አዝማድ ‹‹እንኳን ዘመነ ክረምቱን በሰላም አስፈጸማችሁ›› እያለ የሚጠያየቅበት ታላቅ ተስፋ በየሰው ልቡና የሚያቆጠቁጥበት ወር ነው፡፡ የተዘራው በመብቀሉ የተተከለውም በመጽደቁ እጅግ ያስደስታል፡፡ በተለይም የክረምቱን ዝናብና ጭቃ ታግሶ ያሳለፈው ገበሬ በተስፋ ይመላል፡፡ የዚህን ወቅት አስደሳችነት ጥበበኛው ሰሎሞን ‹‹ሀገራችን አበባው ታየ ወይኑን ትርንጎውንም ቆርጠን የምንበላበት ጊዜ ደረሰ፡፡ የዋኖስ ቃልም በሀገራችን ተሰማ በለስም ቡቃያውን አወጣ ወይኖች አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡›› በማለት ገልጾታል /መኃ.ዘሰሎ ፲፩-፲፫/

በወርኃ ጽጌ የሚታሰበው ሌላው ዐብይ ነገር የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስደት ነው፡፡የጌታችን መወለድ በተስፋ ይጠባበቁ የነበሩ ‹‹ሰብአ ሰገል›› መወለዱን የሚያበስር ኮከብ በምስራቅ አይተው ሊሰግዱለት ወደ ቤተልሔም መጡ፡፡ በዚያም ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው›› እያሉ ጠየቁ፡፡ ይህ ዜና በንጉስ ሔሮድስ ዘንድ እንደተሰማ ከፍተኛ ፍርሃትን አሳደረበት፡፡ ‹‹ንጉስ ሳይገድል አይነግስም›› እንደሚባለው ገድሎት የሚነግስ የመንግስቱ ተቀናቃኝ የተነሳበት መስሎት ሕጻኑን ክርስቶስን የሚገድልበትን መንገድ መፈለግ ጀመረ፡፡ ንጉስ ሄሮድስ ይህን ያስብ እንጂ ሁሉን መደረጉ አስቀድሞ የሚያውቅ እግዚአግሔር መልአኩን ልኮ ለቅዱስ ዮሴፍ ‹‹ሔሮድስ ህጻኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሳ ህጻኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ፡፡ ብሎ በህልም ነገረው›› ማቲ -፲፫ በዚህም የተነሳ ሶስት ዓመት ከመንፈቅ በምድረ ግብጽ በረሀ ለበርሀ ተንከራተዋል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ ‹‹ ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች ከግንዱም አበባ፡፡›› ሲል ተንብዮ ነበር፡፡ ኢሳ ፲፩- ይህ ትንቢት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና እመቤታችንን የሚመለከት ነው፡፡ቅድስት ድንግል ማርያም ‹‹ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች›› ተብሎ የተነገረላት ከዳዊት ወገን የተወለደች ስትሆን ‹‹ ከግንዱም አበባ ይወጣል›› የተባለላት ደግሞ ከርሷ ያለዘርዐ ብእሲ በፍጹም ድግልና የተወለደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡የአበባ መዓዛ ለሚያሸተው ደስ እንዲያሰኝ ከእመቤታችን የተወለደ ጌታም ነገረ ወንጌሉ በጥቡዕ ልቡና በሚሰሙት ዘንድ ደስ ያሰኛል፡፡ አንድም አበባ እመቤታችን ናት፡፡ በአበባ ከተመሰለችው ከድንግል ማርያምም የተወለደው የማኅፀኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለሙ ሁሉ ምግበ ነፍስ ሆኖ ተሠጥቷል፡፡ለዚህም ነው አበው ስርዓት ሲሠሩ በዚህ ወር የእመቤታችንን ስደት እንድናስብ ያደረጉት፡፡

የእመቤታችን ስደት እንደ ውኃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ ሳይሆን ትንቢት የተነገረለት እና ምሳሌ የተመሰለለት ነው፡፡ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ነብዩ እሳይያስ ‹‹እግዝአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይወርዳል፡፡›› በማለት ትንቢት ተነግሮ ነበር ኢሳ ፲፩- ምሳሌውም ቀድሞ አባቶቹ እስራኤላውያን ወደ ግብጽ በተለያዩ ምክንያቶች ተሰደዋል፡፡ በተጨማሪም ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አኳያም ሲታይ ግብጽ ለኢየሩሳሌም ትቀርባለች፡፡ በዘመኑም ክህደት በነዚህ ጸንቶ ነበር፡፡ ግብፃውያን በአምሳለ ላህም ጣዖት ቀርፀው ያመልኩ ስለነበር ወደዚች ሀገር ገብቶ ጣዖታቱን በስልጣኑ ሰባብሯል ሀገሪቱም ሀገረ እግዚአብሔር እንድትሆን ባርኳታል፡፡መሰደዱም ሄሮድስን ፈርቶ ለመሸሽ ሳይሆን ከገነት ለተሰደደው አዳም እንደካሳ ለማጠየቅና በሃይማኖት ምክንያት ለሚሰደዱ ሰማዕታት ስደትን ለመባረክ ነው፡፡ በዚህ ስደት እመቤታችን ብዙ ችግሮችና ኃዘን ተፈራርቀውባታል፡፡የሌሊቱ ቁር የመዓልቱ ሐሩር የአሸዋው ግለት ጽጌረዳ የመሰለ መልኳን አጠውልጎታል፡፡ ይህንንም አባ ጽጌ ማርያም በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታቸው፡፡ ‹‹የሮማን ሽቱ የቀናንሞ አበባ የምትሆኝ ማርያም ሆይ በረሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪጠወልግ ድረስ በስደትና በልቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሰሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፡፡በዚህ ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር፡፡›› ብለዋል፡፡

የጻድቁ የአቡነ /ሃይማኖት ደቀመዝሙር የነበሩት አባ /ማርያም በስደቷ የደረሰባትን ሀዘን ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት ‹‹ሰቆቃወ ድንግል›› ድርሰታቸው የመከራው ጽናት ከሰው አልፎ ለግዑዛን ፍጥረታት እንኳን እደሚሰማቸው ሲገልፁ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ፀሃይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ከክፉ ዘንዶ ከሔሮድስ ልጅሽን ባሸሸሽ ጊዜ የደረሱብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋው ግለት እንዳጎበጎበ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር፡፡›› ብለዋል
ይህ ወር የእመቤታችንን ስደት አስበን በደረሰባት መከራ አዝነን የምናሳልፈው ብቻ አይደለም የራሳችንን ሕይወት የምንቃኝበት የጎበጠውንና የጎደለውን ምግባራችንን ለማቅናት የምንነቃቃበት እንጂ፡፡‹‹አምላኬ ተሰዳ ከወጣሁበት ገነት ባይመልሰኝ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነበርኩ›› በማለት የምናለቅስበትም ጭምር መሆን አለበት፡፡ ሄሮድስ እመቤታችንን ከምድረ ገሊላ ከነልጃ እንዳሳደዳት ዛሬም በኑፋቄ ብትእቢት በክፈት ተይዘው ከሕይወታቸውና በልቡናቸው አውጥተው የሚያሳድዳትም ሁሉ አጥብቀው ራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባቸዋል:: ሊቁ ‹‹ወደማልመለስበት ሩቅ ሀገር መሰደዴን ባሰብሁ ጊዜ ድንግል ሆይ የስደትሽ ልቅሶ መዝሙር ሆነኝ፡፡ ካንቺ በቀር ከልጅሽ  እንዲያማልደኝ የማውቀው የለምና በአፍሽ እና በሕሊናሽ የታሰብሁ በልብሽም ያደርሁ አድርጊን፡፡›› በማለት ማንነቱን በመገንዘብ ምክንያተ ድሒን የሆነችውን እመቤት ተማጽኗል፡፡እኛም እመብርሃንን በሕይወታችን ሁሉ እንዳትለየን እንማጸናት፡፡

በየቦታው ምድሩን ያስጌጠው አበባ እንዳማረበት እንዲሁ አይቀርም ይደርቃል ይረግፋል፡፡እኩሌታው ረግፎ ፍሬ ሲያፈራ የተቀረው ያለፍሬ ፍፎ ትቢያ ይሆናል፡፡ እኛም በተሰጠን ጊዜ በእምነት አብበን ፍሬ ምግባርን ልናፈራ ይገባል፡፡ ችግርን ሃዘንን ይታውቅ እመቤታችን በምልጃዋ እዳትለየንም እንደ አባ ህርያቆስ ‹‹ድንግል ሆይ ርሃቡንና ጥሙን ችግሩንና ሀዘኑን ደርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ፡፡›› ልንላት ይገባናል፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።