Oct 2, 2011

የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። (፩ኛ ቆሮ ፩፡ ፩)


                                                                                    
ምንጭ ፦ ዘመድኩን (ዋርካ ጡመራ መድረክ)
. . . . የሁሉ መጀመሪያ ፫፻፳፮  . . . . .
" መስከረም ባበባው ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃልይላሉ አበው። ክረምቱ አልፎ ሜዳና ተራራው በአበባ ሲሸፈን፣አዝመራው ሲያሸት አንድም መስከረም ርዕሰ ዓውደ ዓመት፣ የዘመን መለወጫ በመሆኑ ወርኃ አደይ ወወርኃ ጽጌ ተብሏል። እናም ኢትዮጵያውያን በርዕሰ በዓልነት ታላቅ ማዕዘን ላይ ያስቀመጡት ወርኃ መስከረም፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል። ከነዚህም ውስጥ ከዕንቁጣጣሽ በዓል ቀጥሎ በሠፊው የሚታወቀው በዓለ መስቀል ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑና ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ  ፫፻ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ / ኖረ፡፡


ጉዞ ወደ ኢየሩሳሌም
 ፫፻፳፮ . . የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች፡፡ እዚያም ደርሳ . . . ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቀድ ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን የተጣለበትን አካባቢ ለማወቅ አንቺም በከንቱ አትድከሚ ስውንም አታድክሚ እንጨትአሰብስበሽ እጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪውበዚህ ምልክት ታገኚዋለሽአላት እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። ዕንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡ ይህ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪርያኮስ ተብሏል፡፡

በዚህም መሠረት ከመስከረም ፲፯ ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት ፲ ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት ፲ ቀን ፫፻፳፮  . . ነበር፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶን እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ፡፡ ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት፡፡ በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ተቀምጦ ለመሰቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ተመርቆ የገባው (ቅዳሴ ቤቱ ) የተከበረው መስከረም ፲፯ ቀን ፫፻፳፮  . . ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም ፲፯ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት ፲ ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረው መስከረም ፲፯ በመሆኑ ነው፡፡

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም
‘’መስቀሌን በመስቀልያ ሥፍራ አስቀምጠው
ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ የሚያሻግረው ብቸኛው መንገድ
 ፲፭ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአገራችን በተደጋጋሚ ያስቸገረውን ረኀብ እና በሽታ ለማስወገድ በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ ኢየሱስ ክርስቶሰ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መቀመጡ ነው።ይህም የሆነው መስከረም ፲ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ መስቀል መምጣት የቤተክርስቲያኗ ጸሐፍት በተለያዩ ሠነዶቻቸው የተረኩ ሲሆን፣ ንጉሡ አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን አስመጥተው በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር፣ ሊያሳርፉበት ያልሞከሩበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸገረ። በመጨረሻ ግንአንብር መስቀልዬ በዲበ መስቀል። (መስቀሌን በመስቀልያ ሥፍራ አስቀምጠው )” የሚል መለኮታዊ ምሪት ስለደረሳቸው፣ አሁን ግሼ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም ፳፩ ቀን ፲፻፬፻፵፮  / ደብረ ከርቤ እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ሥፍራ መስቀልያ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው ነው።

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም፡ - በአሁኑ ወሎ ክፍለ ሃገር፣ አምባሰል ወረዳ ውስጥ ግሸን ተራራ አናት ላይ የምትገኝ /ክርስቲያንናት። ለዚች /ክርስቲያን መግቢያ አንድ መንገድ ብቻ ነው። እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይህችቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያየ ስያሜን አግኝታለች።
ከአጼ ድልናአድ ዘመን (፰፻፷፮  . ) እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ (ደብረ ከርቤ ) ትታወቅ ነበር።
 ፲፩ ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔር አብ የተሰኘ /ክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሰሩ ደብረ እግዚአብሔር በሚል ስም ታወቀች። ብዙ ሳይቆይ ግን ደብረ ነገስት ተባለች።
 ፲፻፬፻፵፮ አጼ ዘርአ የዕቆብ ግማደ መስቀሉን በዚህ ስፍራ ሲያርፍ ደብረ ነገስት መባሏ ቀርቶ ደብረ ከርቤ ተባለች። በዚህጊዜ የነበረው የቤ /ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መምህረ እስራኤል ደብረ ከርቤ ይባል ነበር።
አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ "ገሰ " ወይም በአማርኛው "ገሰገሰ " የሚለው ቃልለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተዛወረ። አካባቢው በዚህ ስም ታወቀ።

የግማደ መስቀሉ ታሪካዊ አመጣጥ
ዐፄ ዳዊት ግብፆች እጅ መንሻ ብዙ ወቄት ወርቅ ቢሰጡአቸውም አልፈልግም ብለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ዕፀ መስቀል እንዲሰጧቸው አጥብቀው ጠየቋቸው፡፡ የዓለም ድኅነት የተገኘበት ክቡር የሆነው መስቀል እንደሚበልጥ እግዚአብሔር አመልክቷቸው ነበርና፡፡ በትግል ክቡር መስቀሉን እንደተቀበሉ ድንገተኛ ራእይ ታያቸው «መስቀልየ ይነብር በዲበ መስቀል፤ መስቀሌ በመስቀል ላይ ይቀመጣል» የሚል፡፡ ንጉሡም ይህንን ትዕዛዝ በልባቸው ይዘው መስቀሉን ለአገራቸው ኢትዮጵያ በረከት እንዲሆንላቸው በደስታ ላይ እንዳሉ መናገሻ ከተማቸው ሳይደርሱ በጠረፍ አካባቢ በድንገት ዐረፋ፡፡
አበው «የአባቱን ሱሪ የማይታጠቅ ልጅ አይወለድ» እንዲሉ ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ የአባታቸውን በትረ መንግሥት እንደጨበጡ በአደራ የቆየውን ክቡር መስቀሉን ተረከቡ፡፡ «አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀል ላይ አስቀምጥ» የሚል ትእዛዛዊ ራእይ ስለታያቸው እንደሰንሰለት በተያያዙ በኢትዮጵያ ተራሮች በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አምባ ክቡር መሰቀሉን አስገብተዋል፡፡ 
የእግዚአብሔር አብ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀው በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን መሠረት ውስጥ በተዘጋጀ ልዩ ቦታ መስቀሉን አስቀምጠው ቅዳሴ ቤቱን ነሐሴ 13 ቀን የመስቀሉን ክብረ በዓል ደግሞ መስከረም ፳፩ ቀን፣ ፲፻፬፻፵፮ ዓ.ም. በድምቀት እንዲከበር ሲያደርጉ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ጥር ፳፩ ቀን ፲፻፱፻፵፱ ዓ.ም.  ተከበረ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የመስቀሉና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀንና ጥር ፳፩ ቀን ብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ምእመናን በሚገኙበት በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡
                                           የእመቤታችን አማላጅነት የመስቀሉ በረከት ከእኛ ጋር ይሁን አሜን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።