ምንጭ፦ ቤተ ደጀኔ
መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው
የሶርያ ንጉሥ ሁለተኛው ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰብስቦ በፈረስ በሰረገላ የሰማርያን ከተማ በከበባት ጊዜ
እጅግ የሚያስጨንቅ ረሀብ ሆኖ ነበር። ምክንያቱም የከተማይቱ ሕዝብ የሚመገበው የእህል ምርት የሚገባው ከአስዴራም
ምድረ በዳ ነበርና ነው። በሰማርያ ተራራ ዙሪያ ያለውን ሸለቆ በማረስ እህል ወይን እና የወይራ ዘይት በማምረት ለሕዝቡ እንደፍላጐቱ ያቀርቡ ነበር። በተከበበች ጊዜ ግን
ይህ ሁሉ በረከት በመቆሙ፦የአህያ ራስ በሃምሣ ብር፥ የጎሞር ስምንተኛ የሚሆን የርግብ ኩስ ደግሞ በአምስት ብር ተሸጠ። ይህንንም ገዝተው የሚመገቡት አቅሙ ያላቸው ብቻ ነበሩ።
ረሀብ፦ ማንኛውም ሰው ያገኘውን ሁሉ እንዲበላ ያስገድደዋል። በማቴዎስ ወንጌል ፦በዚያም ወራት ጌታችን ኢየሱስ በሰንበት (በቀዳሚት ሰንበት)በእርሻ መካከል ሄደ።ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ነበርና እሸት እየቆረጡ ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው፥«እነሆ ደቀመዛሙርትህ በሰንበት ሊደረግ የማይገባውን ሲያደርጉ እይ፥ አሉት። እርሱ ግን ፦«ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ እርሱ ያደረገውን ፥ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደገባ ፥ካህናት ብቻ እንጂ፥እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኀብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን?»አላቸው፤ የሚል ተጽፋል። ማቴ፲፪፥፩-፬፣ ፩ኛሳሙ ፩--፮። ረሀብ ከተቀደሰ ስፍራም ይለያል። ከነዓን ለያዕቆብና ለልጆቹ የተቀደሰች የቃል ኪዳን ምድር ነበረች።ይህቺውም ፦ «ወተትና ማር የምታፈስስ ሀገር፤»ተብሎ
በእግዚአብሔር የተነገረላት ሀገር ናት። ዘዳ፫፥፰። ነገር ግን በረሀብ ምክንያት ከተቀደሰችው ከአባቶቻቸው ርስት ተነቅለው ወደ ግብፅ ተሰድደዋል።«በምድር ሁሉ ረሀብ እጅግ ጸንቶ ነበርና ያዕቆብም በግብፅ እህል እንዳለ ሰማ፥ ያዕቆብም ልጆቹን ፦ለምን እርስ በርሳችሁ ትተያያላችሁ? አላቸው።እንዲህም አለ፦እነሆ ስንዴ በግብፅ እንዲገኝ ሰምቻለሁ፤ ወደዚያ ውረዱ ፥ እንድንድንና እንዳንሞትም ከዚያ ሸምቱልን። . . . ራብም በምድር ጸና።ከግብፅም ያመጡትን እህል በልተው ከፈጸሙ በኋላ አባታቸው፦ እንደገና ሂዱ፤ጥቂት እህል ሸምቱልን አላቸው። . . . በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፥ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ፤» ይላል።ዘፍ ፵፩፥፵፯፣፵፪፥፩፣፵፫፥፩፣፵፯፥፲፫።
የሰማርያው ረሀብ ግን ከሁሉም ለየት ይላል፤ በጠላት በመከበባቸው የሚሄዱበት ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። በመሆኑም ሁለት የሰማርያ ሴቶች ለማሰብ እንኳ የሚዘገንን ተግባር አከናወኑ። የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥር ላይ ሲመላለስ አንዲት ሴት ፦«ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ርዳኝ ፤»ብላ ወደ እርሱ ጮኸች። እርሱ ግን «እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት እረዳሻለሁ? ከአውድማው ወይስ ከመጥመቂያው ነውን?»አላት። የንጉሡ አነጋገር ምንም የሚቀመስና የሚላስ ነገር እንደሌለና መፍትሔውም ከእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን የሚያጠይቅ ነበር። ቀጥሎም፦ «ምን ሆነሻል?» አላት። ይኸውም ከረሀቡ በላይ የጎዳት ሌላ ነገር እንዳለ ከሁኔታዋ (ከጩኸቷ፥ ከእንባዋ፥ ከከሰለው ፊትዋ) ተረድቶ ነው። ምክንያቱም የልብ(የውስጥ) ሐዘን ከፊት ላይ ይነበባልና ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሐና እመ ሳሙኤልን፦ «እርሷም በልብዋ አዝና አለቀሰች፤» ይላታል። ፩ኛሳሙ ፩፥፲ ። የሐናን ሐዘን የሚያነብላት አላገኘችም፥ የሰማርያዋ ሴት ግን ንጉሡ ትርጓሜው ባይገለጥለትም ሐዘኗን አንብቦላታል። እርስዋም፦ «ይህች ሴት፦ ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ። ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግስቱም፦ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኋት፤ ልጇንም ሸሸገችው፤»ብላ መለሰችለት። የእስራኤልም ንጉሥ የሴቲቱን ቃል ሰምቶ ልብሱን ቀደደ፤ ይኸውም፦ እስራኤል ፈጽመው ሲያዝኑ ልብሳቸውን ለሁለት ይቀዳሉና ነው። በቅጥርም ይመላለስ ነበር፤ ሕዝቡም በስተውስጥ በሥጋው ላይ ለብሶት የነበረውን ማቅ አዩ። በመከራ ጊዜ ማቅ መልበስ ዐመድ ላይ መተኛት የተለመደ ነው።
ይህ ታሪክ ለማሰብ ከአእምሮ፥ለመናገርም ከአንደበት በላይ ነው።ንጉሡ፦በረሀብ ምክንያት የሆነውን ሰምቶ ወደራሱ ከመመልከት (ኃጢአቱን በደሉን ከማሰብ) ይልቅ የችግሩን ምክንያት ወደሌላ ሲገፋ ፥በሌላ ሲያሳብብ እናገኘዋለን ። ለዚህም ነው፥ «የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በላዩ ያደረ እንደሆነ (አንገቱን ሳልቆርጠው ያደርኩ እንደሆነ) እግዚአብሔር እንዲህ ያድርገኝ፥ እንዲህም ይግደለኝ፤» ያለው። የእግዚአብሔር ነቢያት «ጸልዩልን፥ አማልዱን፤» የሚባሉ እንጂ የሚገደሉ አይደሉም፤ በመጽሐፈ ነገሥት እንደተጻፈው፥ ከነቢያት ወገን ሚስቶች፥ ባሏ የሞተባት ሴት፥ በማሰሮ የነበራት እንጥፍጣፊ ዘይት፥ እንደ ምንጭ ሆኖ የበረከተላት በነቢዩ በኤልሳዕ ጸሎት ነው። ፪ኛነገ ፬፥፩። የሰራፕታዋ ሴት ዱቄቷና ዘይቷ ተባርኮላት የረሀቡ ዘመን እስኪያልቅ ድረስ የተመገበችው በነቢዩ በኤልያስ ጸሎት ነው።ንጉሡ አካዝያስ ከሃምሣ ወታደሮች ጋር ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ነቢዩ ወደ
ኤልያስ የላከው የሃምሣ አለቃ፦ በጉልበቱ ተንበርክኮ፥ «የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ፥ሰውነቴና የእነዚህ የሃምሣው ባሪያዎችህ ሰውነት በፊትህ የከበረች ትሁን። እነሆ ከሰማይ ወርዳ ሁለቱን የሃምሣ አለቆችና ሃምሣ ሃምሣውን ሰዎቻቸውን በላች፤(አቃጥላ ገደለቻቸው)፤ አሁን ግን ነፍሴ (ሰውነቴ) በፊትህ የከበረች ትሁን።»በማለቱ ራሱንና ተከታዮቹን አትርፏል።የተላከው የእግዚአብሔርን ነቢይ እንዲገድል ነበር።፪ኛነገ፩፥፲፫-፲፬። የዚህ ዓለም ሥጋውያን ሹማምንት የሚመስሉት አካዝያስንና የሰማርያውን ንጉሥ ነው። እግዚአብሔርን ትተው የተጓዙበት መንገድ አላዋጣ ብሎ ማጣፊያው ሲያጥራቸው ፥ ወደራሳቸው መመልከት ትተው፥ ችግሩን ወደቤተክርስቲያን ይገፋሉ፤ ሕዝቡ የሚራበው በዓላት ስለበዙ ነው ይላሉ፤ «በዓላትን በማያውቁና በማያከብሩ አካባቢዎችስ ለምን ጥጋብ አልሆነም?» ሲባሉ ግን መልስ የላቸውም። ወደላይ አባቶቻቸውን ይሰድባሉ። የቤቴልን አርባ ሁለት ወጣቶች ሁለት አራዊት ሰባብረው የገደሏቸው አባታቸውን ኤልሳዕን በመስደባቸው የወደቀባቸው እርግማን ነበር። ፪ኛ ነገ ፪፥፳፭።
ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው ለመግደል በሚዝትበትና ከባለሟሎቹም አንዱን በሚልክበት ጊዜ፥ ነቢዩ ኤልሳዕ ከቤቱ ሆኖ ይሰማው ይመለከተው ነበር። የእግዚአብሔር ሰዎች የቦታ ርቀት አይከለክላቸውም፥ የሚያገለግሉት አምላክ እግዚአብሔር የራቀውን አቅርቦ፥ የረቀቀውን አጉልቶ ያሳያቸዋል። ነቢዩ ኤልሳዕ እንኳን በእርሱ ላይ የሚዶለተውን፥ በእሥራኤል ንጉሥ ላይ፥ በሶሪያ ቤተ መንግሥት የሚመከረውን በዶታይን ተቀመጦ ያውቅ ነበር። ንጉሡንም፦ «ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ሥፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ፤» እያለ ብዙ ጊዜ ከሞት አትርፎታል። ፪ኛ ነገ ፮፥፰-፲። ነቢዩ ኤልሳዕ ይኽንን የመሰለ ታላቅ መንፈሳዊ ጸጋ ስለነበረው፥ መልእክተኛው ገና ሳይደርስ፥ አብረውት ለነበሩት ሽማግሌዎች ፦ «ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቆርጥ ዘንድ እንደላከ እዩ፤ መልእክተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ክልክሉት፤ በደጅም ይቆም ዘንድ ተዉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው፤» አላቸው ። ከእነርሱ ጋር ሲነጋገር እነሆ፥ መልእክተኛው ወደእርሱ ደረሰ፤ እርሱም፥ «እነሆ፥ ይህ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፥ እግዚአብሔርን ገና እጠብቅ ዘንድ ምንድነኝ?» አለ። ከንግግሩ የምንረዳው ትዕግሥቱ መሟጠጡን፥ ተስፋ መቁረጡን ነው። ተስፋ ያስቆረጠው በጆሮ የሰማው አሰቃቂ ነገር ነው። «ልጄን ቀቅለን በላነው፤» የሚለው ድምጽ ከልቡም ከጆሮውም አልጠፋ ብሎታል። ቢሆንም በእግዚአብሔር ቸርነት እና በነቢዩ በኤልሳዕ አማላጅነት እስከ መጨረሻው መታመን ነበረበት። የእግዚአብሔር ነቢይ እንኳን በሕይወት እያለ ቢሞት እንኳ፦ በስሙ፥ በቃል ኪዳኑ፥ በአጽሙ መማጸን ይገባው ነበር። የዚህ ዓለም ሹማምንት በችግር ውስጥም ሆነው ልባቸው አይሰበርም። ያንን ሕዝብ የሚመግቡት በስልጣናቸው፥ በጥበባቸው ይመስላቸው ነበር። ረሀብ በመጣ ጊዜ ግን ያንን ሕዝብ ልጁን ቀቅሎ ከመብላት አላዳኑትም። ከሁሉም የሚገርመው ነቢዩን ኤልሳዕን በመግደል መፍትሔ ይመጣል ብለው ማሰባቸው ነው። ፪ኛ ነገ ፮፥፴፪-፴፫። በዚህ ዓይነት በራሳቸው ስሕተት በመጣ ችግር ስንቱን አሰሩት? ስንቱንስ ገደሉት፥ ስንቱንስ አሳደዱት? ብለን ብንጠይቅ ከቁጥር በላይ ነው። እኛም ባለሥልጣኖች ብንሆን እንዲሁ ነን።
፩፥፪፦ «እነሆ፥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያ ግን አትቀምስም፤»
ነቢዩ ኤልሳዕ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ፥የንጉሡን መልእክተኛ፥ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር፥ ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄትም በአንድ ሰቅል ይሸመታል፤»አለው። ይህ መልእክተኛ ለንጉሡ በጣም የቅርብ ሰው ነው፥ ንጉሡ በሚቆምበት ጊዜ እንደ ምርኲዝ የሚደገፈው ሰው ነው። ማንኛውም ሰው ለምድራውያን ባለሥልጣኖች በቀረበ ቁጥር፥ በእነርሱ እየተመካና እየተመጻደቀ ስለሚሄድ መንፈሳዊነቱ እየጠፋ፥እምነቱ እየላላ ፥ልቡ በጥርጥር እየተመላ ይሄዳል። ለዚህም ነው፥ «እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ የእህል ሿሿቴ ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? »ያለው። ይኽንን የተናገረው የሰማርያው ንጉሥ ቢሆን ኖሮ በአድር ባይ ልቡና አምኖ ይቀበል ነበር። የንጉሡ ቃል እውነት ነው፤» እያለ፦ እንደ በቀቀን ይደጋግም፥ እንደ ገደል ማሚቶም ያስተጋባ ነበር። ዛሬም ነገረ እግዚአብሔርን ትተው ነገረ ነገሥታተ ምድርን ወደማስተጋባት የተንሸራተቱ ሰዎች አሉ። ኤልሳዕም ፥«እነሆ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያ ግን አትቀምስም፤» አለው።ምክንያቱም፦ የሰማውን የእግዚአብ ሔር ቃል እንደተጠራጠረ ፥ የሚያየውንም የእግዚአብሔር በረከት ስለሚጠራጠር ነው። እስራኤል ዘሥጋ በምድረ በዳ የእግዚአብሔርን በረከት እየተመገቡ ፥ ተጠራጠሩ እንጂ አላመኑበትም። ይኸንንም ነቢዩ ዳዊት፥ «ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤ውኆችን እንደ ረዋት ውኃ አቆመ። ቀን በደመና መራቸው፥ሌሊቱንም ሙሉ በእሳት ብርሃን ። ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ከብዙ ጥልቅ እንደሚገኝ ያህል አጠጣቸው። ውኃንም እንደወንዞች አፈሰሰ።ውኃንም ከዓለት አፈለቀ፥ነገር ግን እርሱን መበደልን እንደገና ደገሙ፥ልዑልንም በምድረ በዳ አስመረሩት። እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት። እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት፦እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ፥ ዓለቱን ይመታ ዘንድ ፥ውኃንም ያፈስ ዘንድ ይችላልን? እንጀራን መስጠትና ለሕዝቡስ ማዕድን መሥራት ይችላልን? አሉ፤» በማለት ጠቅሶታል።መዝ፸፯፥፲፫-፳።
ይህ ሰው፥ ቢያንስ በረከቱን እንደሚያይ ተነግሮለታል። እኛ ግን በረከተ ሥጋንም በረከተ ነፍስንም ለማየት ያልታደልን ሰዎች ሆነናል። ሁሉ ነገር እንደ ሰማይ ርቆናል። ሰማይ እንኳ ቢርቅም ይታያል፥ የእኛ ነገር ግን በዓይነ ሥጋም በዓይነ ነፍስም የማይታይ ሆኖብናል። ተስፋ ባንቆርጥም አዝነናል። ብቻ ማዘናችን በሥጋ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን።
፩፥፫፦ አራቱ ለምጻሞች፤
በከተማዋ በር አራት ለምጻሞች ሰዎች ነበሩ፤ በኦሪቱ የሰው ርኲሰቱ በለምጽ ይገለጥ ነበር ። በዚህም ምክንያት በለምጻሞች ላይ የተሠራ ሥርዓት ነበር። በመሆኑም ለምጻሞች እስኪነጹ ከሕዝብ ተለይተው፥ ከከተማ ወጥተው፥ ለብቻቸው መኖር ግዴታቸው ነበር።«የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፤ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኲስ ይባላል።ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኲስ ይሆናል፤ እርሱ ርኲስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር ውጪ ይሆናል፤ » ይላል። ዘሌ፲፫፥፵፭-፵፮ ። ከለምጽ በሚፈወሱበትም ጊዜ ልዩ ሥርዓትና መሥዋዕት ይደረግ ነበር። ዘሌ፲፬፥፩-፴፪። አራቱ ለምጻሞች ሥርዓት ጠብቀው እዚያው እንዳይሰነብቱ በረሀብ ሊሞቱ ሆነ፥ ሥርዓት አፍርሰው ወደ ከተማይቱ እንዳይገቡ የሚጠብቃቸው በረሀብ መሞት ነው፥ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንዳይሄዱም ያው ሞት ነው። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ የጨነቀና የጠበበ ነገር ያጋጥማል። እኛ ብንሆን ከሶስቱ ዓይነት ሞት የምንመርጠው የትኛውን ዓይነት ሞት ነው? ወይስ በእምነት እንድናለን ብለን ሕይወትን እንመርጣለን? በሞት መካከል ሆኖ ሕይወትን መምረጥ ታላቅ እምነት ነው። ቅዱስ ዳዊት፦«በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። » ያለው ለዚህ ነው። መዝ፳፪፥፬።ለሰው ከሆነ ግን አንዱን ወይም ሦስቱንም ልንመርጥለት እንችላለን። በመንፈሳዊ ሕይወት ፥ ፈቃደ ነፍስ ሕገ ወንጌል ቀጭን መንገድና ጠባብ ደጅ ነው። «በጠባቢቱ በር ግቡ ፤ ወደ ጥፋት የምትወስድ ሰፊ በር ፥ሰፊ መንገድም አለችና፤ወደ እርስዋ የሚገቡ ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የምትወስደው በር እጅግ ጠባብ፥ መንገድዋም ቀጭን ናትና፤ የሚገቡትም ጥቂቶች ናቸውና፤» ይላል። ማቴ ፯፥፲፫።
የእኛ ለምፅ ኃጢአት በደላችን ነው፥ በመሆኑም ከሰው ተለይተን (ከሥጋዊ ከደማዊ አስተሳሰብ ርቀን ) ከከተማይቱ (ከኃጢአት መንደር ) ልንወጣ ይገባናል። አፋችንን ልንሸፍን (ክፉ ከመናገር ልንቆጠብ ፥ቅዱሱ የእግዚአብሔር ስም በረከሰው በእኛ አንደበት ሊጠራ አይገባውም፤ ልንል)፥ ልብሳችንን ለሁለት ልንቀድ (ስለኃጢአታችን ፈፅመን ልናዝን ) ያስፈልገናል።ለምፃሞቹ እስኪነፁ ድረስ ከከተማ ውጭ እንደሚቆዩ እኛም ቀኖናችንን እስክንጨርስ ከዓለማዊ ስፍራ ወጥተን በገዳም ልንሰነብት ይገባናል።
፩፥፬፦«እግዚአብሔር፦ለሶርያውያን የሰረገላ፥ የፈረስና የብዙ ጭፍራ ድምፅ አሰማቸው።»
አራቱ ለምጻሞች ከሦስቱ ዓይነት ሞት አንዱን መረጡ ። እርስ በርሳቸውም ፥ «እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን? ወደ ከተማ ብንገባ ራብ በከተማ አለና እንሞታለን። በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን፤»ተባባሉ። በረሀብ ከመሞት በጦር መሞትን ወሰኑ። በጨለማም ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ። ወደ ሰፈሩበት ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ግን ማንም ሰው በዚያ አልነበረም። እግዚአብሔር ለሶርያውያን የሰረገላ፥ የፈረስና የብዙ ጭፍራ ድምፅ አሰምቶአቸው፥ እርስ በርሳቸው፥ «እነሆ የእስራኤል ንጉሥ ይከቡን ዘንድ የኬጤዎናውያንንና የግብፃውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል፤» ይባባሉ ነበር። ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን ፥ አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ። እግዚአብሔር ሲያሸንፍ እንዲህ ነው፥ለሰው የከበደውን እርሱ በቅጽበት እንደ ትቢያ ይበትነዋል። እስራኤል ዘሥጋ፦ «እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ስሙ እግዚአብሔር ነው፤»እያሉ የዘመሩት ለዚህ ነበር። ዘዳ፲፭፥፫።እነዚያም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ፤ ጠጡም ፤ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፤ ሄደውም ሸሸጉት ፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፥ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ። እግዚአብሔር ቀድሞ የሚደርሰው እንዲህ ላሉትና ለተናቁት ነው። እነዚህ ሰዎች ከሰው ተለይተው ከመንደር ወጥተው የሚኖሩት ኃጢአታቸውን አምነው ነበር። እኛስ ኃጢአታችንን አምነን የንስሐ ኑሮ መኖር የምንጀምረው መቼ ነው። የራሳችንን ግመል የሚያህል ኃጢአት ሸፍነን የባልንጀራችንን ግን ትንኝ የምታህለውን እያጠራን የምንኖረው እስከመቼ ነው። በዚህስ መንፈስ እግዚአብሔር ለሀገራችንም ለቤተክርስቲያናችንም እንዴት ይደርስላታል?
፩፥፭፦ «መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም የምሥራች ቀን ነው፤»
ብዙ ሰዎች ለራሳችን ከተመቸን ማንም ቢሆን ትዝ አይለንም፥ትዝ ቢለንም ግድ የለንም። የምናየው የእኛን ከችግር ማምለጥ እንጂ በችግር የተያዙትን ወገኖቻችንን አይደለም። በተለይም በዚህ ዘመን በረሀብተኞች ስም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ ስለሚቻል፥ መነገጃ ልናደርጋቸውም እንችላለን። ወይም «ሲያጋንኑ ነው እንጂ ረሀብም ችግርም የለም፤» እንል ይሆናል። ወይም ብሶብን እንደ ንጉሥ ሰሎሞን «ረሀብ ደግሞ ምንድን ነው?» እንል ይሆናል። እርሱ ቢል ያምርበታል፥ ምክንያቱም ረሀብን አይቶ ስለማያውቅ ነበር። በኋላ ግን እግዚአብሔር በጥበብ ረሀብን አሳይቶት ለረሀብተኛ የሚያዝን ሆኗል። የሚያሳዝነው የእኛ ነው፥ ምክንያቱም በረሀብ መካከል አልፈን ረሀብን ረስተናል፥ ሕዝቡ በረሀብ እንደቅጠል ቢረግፍ የማይሰማን ሰዎች ሆነናል። ወላጆች ልጆቻቸውን በረሀብ ሲነጠቁ፥ ልጆችም ወላጆቻቸውን በረሀብ ሲቀሙ እያየን ግድ የለንም። አጥንታቸው አግጦ፥ ቆዳቸው ተሸብሽቦ፥ ዓይናቸው ጎድጉዶ፥ ቅስማቸው ተሰብሮ እያየን፥ እኛ እንደቁም ነገር የያዝነው ያለንን፥ ቀን የሰጠንን ወርቅና ብር ደብቀን ሸሽገን ማከማቸት ነው። መስሎን ነው እንጂ ወይ ሳንበላው እንሞታለን፥ ወይ ቀን የሰጠንን ቀን ይወስድብናል።
አራቱ ለምጻሞች በሰው ዘንድ የተናቁና የተዋረዱ ቢሆኑም የሚያስከብር ሥራ ሠርተዋል።በስግብግብነት ያገኘነውን ሁሉ ለራሳችን ብቻ እናከማች ሳይሉ በረሀብ አለንጋ የተገረፉትን ወገኖቻቸውን አስታውሰዋል። የተራቡ ወገኖቻቸውን ለማስታወስ አንድ ቀን አልፈጀባቸውም። ለዚህ ነው፥ «መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የምሥራች ቀን ነው፤ እኛም ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተሰብም እንናገር፤» የተባባሉት።ገብተውም በከተማው በር ጮኹ፤ «ወደ ሶርያውያን ሰፈ ር ገባን፤ እነሆም ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖቹም ተተክለው ነበር እንጂ ያገኘነው አልነበረም፤ የሰውም ድምፅ አልነበ ረም።» ብለው ያዩትን ተናገሩ። የደጁም ጠባቂዎች ለንጉሡ ይነግሩ ዘንድ ወደ ውስጥ ገቡ፤ ለንጉሡም ቤት አወሩ። ንጉሡ ግን ተጠራጠረ፥ የሰማውን ነገር ማመን አልቻለም። በሌሊት ተነሥቶ ብላቴኖቹን፥ «ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል፤» አላቸው። ከብላቴኖቹ አንዱ ግን አስተዋይ ስለነበር «ንጉሥ ሆይ፥ ይኸንን ነገር ሄደን እናጣራ፤» ብሎ ከንጉሡ ፈቃድ አገኘ። ሁለት ፈረሰኞችን ወስደው አስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከትለዋቸው ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ አገኙ። ተመልሰውም ለእስራኤል ንጉሥ ነገሩት። ንጉሡም ከሕዝቡ ጋር አብሮ ተርቧል። ዛሬ ዛሬ ግን በዓለም የሚታየው እንዲህ አይደለም፤ከታች ጀምሮ እስከላይ ድረስ ያሉ የሥልጣን ሰዎች ጠግበው ያድራሉ፥ እንዲያውም ተርፏቸው ያከማቻሉ።ተርታው ሕዝብ ግን በረሀብ ይረግፋል፥ በሰው ዘንድ ያለውም ተስፋ ጨልሟል። ለዚህ ሕዝብ እንደ አራቱ ለምጻሞች መልካሙን የምሥራች ማን ይንገረው? «መልካም አላደረግንም፤» ብለው የሚጸጸቱስ እነማናቸው?
፩፥፮፦ ነቢዩ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ተፈጸመ፤
ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ፥ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ተሸመተ።ይህ ሁሉ የሆነው ንጉሡ ሊገድለው በዛተበት በነቢዩ በኤልሳዕ ጸሎትና አማላጅነት ነው። ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን ብላቴና በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም እርስ በርሱ ሲገፋፋ ወድቆ ተረጋገጠ። መልእክተኛው ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደተናገረበት ሞተ። ኤልሳዕም ለንጉሡ ፥«ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈርያ ገብስ በአንድ ሰቅል ፥ይሸመታል፤ » ብሎ እንደተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ። ያም ሎሌ ለኤልሳዕ መልሶ፥«እነሆ እግዚአብሔር በሰማይ የእህል ሿሿቴ ቢያወርድ ይህ ነገር ይሆናልን?»ብሎ ነበር፤ ኤልሳዕም ፥«እነሆ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ከዚያም አትቀምስም፤ ብሎት ነበር።
«ለእኛስ ፥የቅዱሳን ጸሎት ደርሶልን ፥የእግዚአብሔር ቸርነት የሚፈጸምልን መቼ ይሆን?የዕለት ጉርስ ፥የዓመት ልብስ ያለጭንቀት የምናገኘው መቼ ይሆን?»ልንል ይገባል ። ባንራብም ፥በተራቡት ወገኖቻችን ሕይወት ተገብተን ፥በራሳችን ላይ እንደደረስ አድርገን ልንቆጥረው ያስፈልጋል።
፪፦ ምን እናድርግ?
በፍርድ ቀን ፥ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ ፥«ተርቤ አላበላችሁኝምና፤ ተጠምቼም አላጠጣችሁኝምና ፤ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፤ ታርዤም አላለበሳችሁኝምና፤ ታምሜም አልጎበኛችሁኝምና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ አልጠየ ቃችሁኝምና፤» ብሎ የሚወቅሰን ከታናናሾቹ ለአንዳቸው (ለተቸገሩ ወገኖቻችን) ባለማድረጋችን አንደሆነ በግልጥ
ነግሮናል። ማቴ ፳፭፥፵፪። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም፥ «ወንድሞቻችን ሆይ፥ እምነት አለኝ ፤ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር፥ ምን ይጠቅ መዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን፥ ወይም ከእኀቶቻችን፥ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ፥ ከእናንተም አንዱ፥ በሰላም ሂዱ፥ እሳት ሙቁ ፥ ትጠግባለችሁም ቢላቸው፥ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም
ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው፤» ብሎናል። ያዕ፪፥፲፩-፲፯። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም በበኲሉ፦ «የዚህ ዓለም ንብረት ያለው ወንድሙንም ተቸግሮ አይቶ ምጽዋትን የሚከለክለው የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? ልጆቼ ሆይ፥ በምግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንፋቀር።»በማለት አስገንዝቦናል። ፩ኛዮሐ ፫፥፲፯-፲፰።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፥ ከዚህ አለፍ ብሎ፥ የጌታን ቃል መሠረት በማድረግ «ጠላትህ ቢራብ አብላው ፤ቢጠማም አጠጣው ፤ይህን ብታደርግ የእሳት ፍሕም በራሱ ላይ ትከምራለህ።ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው፤» ብሏል። ሮሜ፲፪፥፳፣ ምሳ፳፭፥፳፩፣ ማቴ፭፥፵፬ ይህም በጸጸት እሳት እንዲቃጠል፥ አንገቱን እንዲደፋ፥ ራሱን ዝቅ እንዲያደርግ፥ ንስሐ እንዲገባ ታደርገዋለህ፥ ማለት ነው። ስለ ክፉ ሥራው ካልተጸጸተና በትዕቢቱ ከገፉበት ደግሞ በገሃነመ እሳት ታስፈርድበታለህ፥ ማለት ነው። ስለዚህ በተለይም በውጪው ዓለም ያለን ምእመናን ፥ለቤተሰቦቻችን እንደምናስብ ሁሉ ለተራቡት ወገኖቻችንም ልናስብ ይገባል። እግዚአብሔርም ወገኖቻችንም ከእኛ የሚጠብቁት ይኽንን ነው። በመሆኑም፥ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን፥ ተጨማሪ ገንዘብ በቤተሰቦቻችን በኲል አየላክን ፥ ዘመድ ባዕድ ሳይሉ፥ ዘር ፖለቲካ ሳይለዩ የተቸገሩትን ሁሉ እንዲጎበኙ ማድረግ አለብን። ምክንያቱም፦ በዚህ የኑሮ ውድነት ከጣራ በላይ በሆነበት፥ ገንዘብ የመግዛት ኃይሉን ባጣበት፥ አብዛኛው ከድህነት ወለል በታች ወድቆ ራስንም ቤተሰብንም በቀን አንድ ጊዜ እንኳ መመገብ ባልቻለበት ዘመን
ከእኛ ብዙ ይጠበቃል። «ብዙ ከሰጡት ብዙ ይፈልጉበታልና፥ ጥቂት ከሰጡትም ጥቂት ይፈልጉበታልና፤ »ሉቃ፲፪፥፵፰።
በመንፈሳዊውም ረገድ ፥ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች በረሀብ ምክንያት እንዳይፈቱ ፦ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ዛሬውኑ ማድረግ ይጠበቅብናል። ይኽንን በተመለከተ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ማኅበር፥ ማኅበረ ቅዱሳን ፥ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ፥ በተጠናና በተቀናጀ መልኩ፥ የታመነና የተመሰከረ እጅግ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ በመኾኑ፥ አንዳንድ የተጠኑ ፕሮጀክቶችን በኃላፊነት በመውሰድ፥ በታሪክ የሚታወስ፥ በምድርም በሰማይም የሚያስመሰግን፥ ዋጋም የሚያሰጥ፥ ሃይማኖታዊ ሥራ መሥራት ይቻላል። ጥንት መናፍቃኑ፥ ርሃብን ምክንያት በማድረግ፥ በዕርዳታ ስም፥ ምዕመናንን ከሃይማኖታቸው ያፈልሱ ነበር። ዛሬ ዛሬ ደግሞ፥ ያለፈው እንደተጠበቀ ሆኖ፥ በዕርዳታ ስም፥ ወደ ገዳማትና የአብነት ት/ ቤቶች በመቅረብ፥ ምንጩን ለማድረቅ ከምንጊዜውም በላይ እየሠሩ ነው። ይህ ሁሉ የሆነው፥ እኛ ልንሠራው የሚገባንን የቤት ሥራ በትክክል ባለመሥራታችን ነው። ስለዚህ ወደድንም ጠላንም ችግሩ አፍጥጦ ወጥቶ፥ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር በመሆኑ፥ ነገ እንዳይጸጽተን ዛሬ በእምነት ታጥቀን ልንነሣ ይገባናል። በአዋጅ ከሚጾሙት አጽዋማት በተጨማሪ ጾም ጸሎት እየያዝን፥ እንደ ነህምያ፥ በፍጹም እምነትና ተስፋ፥ «የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ንጹሓን ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢያሩሳሌም (ኢየሩሳሌም በምትባል በቤተ ክርስቲያን፥ አንድም ዛቲ ይዕቲ ኢየሩሳሌም በምትባል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ፥ አንድም ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በምትባል በመንግስተ ሰማያት) ዕድል ፈንታና መብት፥ መታሰቢያ የላችሁም፤ » ልንል ይገባል። ነህ ፪፥፳።
ስብከተ ወንጌልንም በተመለከተ፥ ይህን ሕዝብ፥ ትምህርተ ተዋሕዶን እያስራቡት፥ ትምህርተ መናፍቃንን እየመገቡት ስለሆነ፥ መነሻ መድረሻችን፥ መሠረት ጉልላታችን፥ ትምህርተ ወንጌል መሆን ይገባዋል። ዓፄ ምኒሊክ «ዓመልህን በጉያህ » በማለት በሀገር ጉዳይ ሕዝብን አንድ አድርገው ለሰማዕትነት እንዳዘጋጁት፥ እኛም እንደየመልካችን የሚለያየውን የግል ዓመላችንን ሲቻል አስወግደን ካልተቻለም በጉያችን አድርገን፥ በቤተክርስቲያን ጉዳይ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን፥ በእምነት የምንነሣበትና ለሰማዕትነት የምንዘጋጅበት ጊዜው አሁን ነው።
ያቺ ሴት በጓደኛዋ አሳሳችነት፥ መልሳ ላታገኘው ልጅዋን ቀቅላ እንደበላች፥ ይህም ትውልድ በመናፍቃን ሴራ፥ ሃይማኖቱን ፥ ሥርዓቱን፥ ትውፊቱን፥ ታሪኩን፥ ቅርሱን፥ ቀቅሎ ከበላ (ካጠፋ) በኋላ ባዶውን እንዳይቀር፥ ተከታታይና የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይገባል። የውስጥ መናፍቃን ነገር፥ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የእውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ጉዳይ ለመሆን የበቃው ያላሰለሰ ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በመሠራቱ ነው። መቼም ቢሆን በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አትወድቅም። ከላይ እሰከ ታች ያለነው እኛ፥ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ትዝብት ላይ እንወድቃለን እንጂ፥ እርሷን የቅዱሳኑ አፅም ይጠብቃታል፥ በአጸደ ነፍስ ያሉ የእነርሱ አማላጅነት ይጋርዳታል። ይህም የእግዚአብሔር ቸርነት መገለጫው
ነው። ያቺ ሴት ጓደኛዋ « ለዛሬ ልጅሽን ቀቅለን እንብላ፤ » ስትላት ፥ «ረሃቡ ይግደለኝ እንጂ ልጅ አይበላም፤» ብላ ቢሆን ኖሮ በጸጸት አለንጋ አትገረፍም ነበር። በእግዚአብሔር ቸርነት፥ በነቢዩ በኤልሳዕ ጸሎት ከበረከቱ ዕለት ትደርስ ነበር። ዛሬ እናታቸውን ቤተ ክርስቲያንን ቀቅለው ለመብላት እሳት ላይ የጣዷት ሁሉ የነገ ትርፋቸው ጸጸት ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን፥ እንኳን ይህንን ዘመን፥ የዮዲትን (የጉዲትን) እና የግራኝ መሐመድን ዘመን፥ እንዲሁም የአምስቱን ዓመት የጣሊያን ወረራ (የካቶሊኮችን ዘመቻ) ዘመንንም አልፋለች። ምክንያቱም፦ ቤተክርስቲያንን የሲኦል ደጆች (የሲኦል ደጅ ጠባቂዎች አጋንንት) አይችሏትምና ነው። ማቴ ፲፮፥፲፰። እንግዲህ ይኽንን ሁሉ በማስተዋል፥ በረሀበ ሥጋ በረሀበ ነፍስም ለተያዙ ወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባል። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፥ አሜን።
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።