በቤተ ክርስተያናችን የዘመን አቆጣጠር /አከፋፈል/ መሠረት ከኀዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ ፲፫ ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምህሮ ይባላል፡፡ መሀረ ማለት ይቅር አለ ማለት ሲሆን፤ ዘመነ አስተምህሮ ማለት ይቅርታ የመጠየቅ /የምልጃ/ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምዕመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ያሉት አምስት እሑዶችና በእነዚህ እሑዶች የሚጀምሩት ሳምንታት አስተምህሮ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ እና ደብረ ዘይት በመባል ይጠራሉ በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበውን ትምህርት በየጊዜው እናከብራለን የመጀመሪያውን ሳምንት /የአስተምህሮ/ ትምህርት እነሆ: -
ይህ ቃል የተወሰደው ጌታችን በደቀ መዛሙርቱ በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ /ዛሬም ላለን/ ክርስቲያኖች እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ካስተማረው ፀሎት ነው፤ በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን/ ማቴ.6. ፱-፲፬/ ይህ ጸሎት በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ሊቀውንት «የጌታ ጸሎት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የጸሎቱን የመጀመሪያ ሐረግ በመያዝ «አባታችን ሆይ» ወይም በግእዝ «አቡነ ዘበሰማያት» እንለዋለን፡፡ ይህ ጸሎት ጌታችን ራሱ ያስተማረው በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሌሎች ጸሎታት ሁሉ ማሰሪያ /ማሳረጊያ/ ሆኖም ያገለግላል፡፡ በውስጡም «አባታችን ሆይ» ከምትለው ከመጀመሪያዋ ሀረግ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እጅግ ጥልቅ የሆኑና ነፍስን የሚያጠግቡ ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጉ መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ መልእክቶችን ያዘለ ነው፡፡ ይህ የዘመነ አስተምህሮ የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ይቅርታ የሚሰበክበት ነውና በጸሎቱ ውስጥ ስለዚህ የሚናገረውን አንቀጽ መሠረት አድርገን እንማራለን፤ «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» ከዚህ ቃል በርካታ ነገሮችን እንማራለን፤
እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደሚወድ
አምላካችን ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ባይወድ ኖሮ ይቅርታን እንድንጠይቅ አይነግረንም ነበር፡፡ አዎ እኛ ከተመለስን ምንም ያህል በደለኛ ብንሆን ይቅር ሊለን፤ ምንም ያህል ብንቆሽሸ ሊያድነን ዝግጁ ነው፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራናል፤ «እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ»፡፡ ስለዚህ በዚሀ ጸሎትም ላይ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጠይቀው አስተማረን፤ ይቅር ይለን ዘንድ፡:
ይቅር ለመባል ምን ማድረግ እንዳለብን፤
ይቅር ሊለን ስለ ወደደም ይቅርታን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በዚሁ ቃል ነግሮናል፤ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው?
- ኀጢአታችንን ማወቅ፣ ማመን፣ ማስታወስ
- የበደሉንን ይቅር ማለት
- ይቅርታን መለመን
ኅጢአታችንን ማወቅ /ማመን/:- ጌታ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጸልይ ሲነግረን በመጀመሪያ ደረጃ በደለኛ እንደሆንን እያስታወስን /እንድናስታውስ እያደረገን/ ነው፡፡ ሁልጊዜም በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሆነውን ልባችንን /ኅሊናችንን/ እና ሰውነታችንን እናቆሽሻለን፤ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሞተለትን ማንነታችንን እናጎድፋለን፡፡ ይህም የሰው ልጆች በቅድስና እርሱን መስለን እንድንኖር በኋላም የተዘጋጀልንን የዘለዓለም መንግሥት እንድወርስ ብቻ ፈቃዱ የሆነውን እግዚአብሔርን ያሳዝናል፤ በአርአያውና በአምሳሉ ለክብር የፈጠረው ሰውነታችን መጉደፍ ያስቆጣዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ የሆነ እርሱ ኀጢአት አይስማማውምና፡፡ እንግዲህ ይቅር ለመባል በመጀመሪያ እንዲህ ኀጢአት እየሠራን መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ ዕውቀት ለመድረስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስህተት የሚታወቀው ያለውን ሁኔታ /ድርጊታችንን ንግግራችንን፣ ሀሳባችንን.. / መሆን ከነበረበት /ከትክክለኛው/ ጋር በማነጻጸር በሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው፡፡ የማነጻጻሪያ ሚዛኖቻችን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ሕግጋትና ትዕዛዛት ናቸው፡፡ እነዚህን ስናውቅ ጉድለቶቻችን፣ ድካሞቻችን ፍንተው ብሎ ይታዩናል፡፡ አሊያ ግን እየበደለን ያልበደልን ሊመስለን ይችላል፡፡
የበደሉንን ይቅር ማለት:- ጌታ በዚህ ጸሎት ይቅርታ እንድንጠይቀው በማስተማር ይቅር ሊለን እንደሚወድ ዝግጁም እንደሆነ ቢነግረንም ይቅር ለመባል ግን እኛ የበደሉንን ይቅር ማለታችን የግድ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦልናል፤ «በደላችንን ይቅር በለን» ከማለታችን በፊት «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል» እንድንል ያዘዘን እኛ ይቅርታ የምናገኘው ሌሎችን ይቅር ስንል ብቻ መሆኑን ለማመልከት ነው፡ ጌታችን ይህንን ጉዳይ በሌሎች የተለያዩ ቦታዎችም በተደጋጋሚ አስተምህሮናል፤ በዚሁ በተራራው ስብከት ይኸው ጉዳይ ሁለት ጊዜ በጌታችን ትምህርት ተሰጥቶበታል፡፡ «እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል፡፡ » /ማቴ.7-2/
በሌላ ቦታም እንዲህ ሲል ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ አስተምሯል፤ መንግስተ ሰማያት ባሮቹን ለመቆጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች መቆጣጠርም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ባለ እዳው ሰው የሚከፍለው ስላጣ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ንጉሡ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ባርያው ወድቆ ሰገደለትና ጌታ ሆይ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው፡፡ የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፡፡ ይህ ባርያ ግን ወጥቶ ከባልጀሮቹ /እንደርሱ ባርያ ከሆኑት/ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው፡፡ ባልንጀራው ባርያም ወድቆ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤ ብሎ ለመነው፡፡ እርሱ ግን ሊተወው አልወደደም፡፡ ዕዳውን እስኪከፍልም በወኅኒ አኖረው፡፡ ይህንን ያዩ ሰዎችም አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለንጉሡ ተናገሩ፡፡
«ከዚህ ወዲያ ንጉሡ ጠርቶ፣ አንተ ክፉ ባርያ ስለ ለመንከኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን የሆነውን ባርያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን አለው፡፡ ጌታውም ተቆጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚያሰቃዩት አሳልፎ ሰጠው፡፡» ጌታ ይህንን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የምሳሌውን ትርጉም እንዲህ ሲል ገልጦታል፤ ብሏል፤ «ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል»/ማቴ.18. 23- 35/
በአጠቃላይ ይቅር ለመባል ይቅር ማለት የግድ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚፈረድብን ፍርድ በእኛው እጅ ላይ ነው፡፡ ጌታችን በእነዚህ ትምህርቶች እንዲህ እያለን ነው «እኔ እናንተ ላይ የምፈርደው እናንተ በራሳችሁ ላይ በፈረዳችሁበት መንገድ /መልኩ ነው/»፡፡
ይቅርታ መጠየቅ
ኀጢአታችንን ካወቅንና ካመንን፣ የበደሉንንም ከልብ ይቅር ካልን በኋላ ይቅር እንድንባል መጠየቅ /መለመን/ አለብን ፡፡ «ይቅር በለን» ብላችሁ ጸልዩ ብሎ በማስተማሩ ይህንን እንረዳለን፡፡ ወደ ንስሐ አባት መሄድና ኀጢአትን ተናዞ ቀኖና መቀበል የሚገባው መጀመሪያ በዚህ መልኩ ስለ ኀጢአት ካለቀሱ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም ቀኖና ተቀብለን ስንፈጽምም ሆነ ከዚያ በኋላ ይኸው ስለ ኀጢአት ይቅርታ መጠየቁ ይቀጥላል፡፡ በእርግጥም ይቅርታ የምንጠይቀው አዳዲስ ስለ ሠራናቸውና ንስሐ ገና ስላልገባንባቸው ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይሆን ንስሐ ስለ ገባንባቸው ስለ ቀደሙት በደሎቻችንም ጭምር ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዳዊት «የቀደመ በደላችንን አታስብብን ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን» /መዝ.78-8/ እያልን ሰለ ቀደሙ በደሎቻችንንም እያሰብን በሕይወታችን ዘመን ሁሉ መጠየቅ አለብን፡፡ ይቅርታ የምንጠይቀው ስለምናውቃቸው /ስለምናስተውላቸው/ ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ማናስተውላቸውም መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ «ይቅር ብለን» ስንል እኛ ካስተዋልናቸው መንገዶች ውጪ በብዙ መልኩ እርሱን እንደምንበድል አስበን ተማጽኗችን ስለነዚህም መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችንና የጌታን ጸሎት ከመጸለያችን በፊት የበደሉንን ይቅር እንዳልን እርግጠኛ መሆን አለብን እኛ የበደሉንን ይቅር እንዳልን ልንል ነውና፡፡ «እኛንም በደላችንን ይቅር በለን» ስንልም ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ሁሉ እያሰብን፤ ይቅር ሊለን የወደደ አምላካችንንም እያመሰገንን መሆን አለበት፡፡
በእውነት ይህንን ጸሎት የምንጸልየው በዚህ መልኩ ነውን? ካልሆነ ልምምዱን ዛሬውኑ እንጀምረው፡፡ ይህንን ማድረግ እንችል ዘንደ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።