Nov 21, 2011

ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም። ዳን ፲፥፳፩


ምንጭ፦ ደቂቀ ናቡቴ

 ቅዱስ ማለት ልዩ፥ ክቡር ማለት ነው፤ ሚካኤል ማለት ደግሞ «መኑ ከመ አምላክ፥ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነውማለት ነው። ሚካኤል የሚለው ስም ቃሉ የዕብራይስጥ ነው፤ - የሚለው «መኑ» ማለት ነው፥ - የሚለው «ከመ» ማለት ሲሆን፥ ኤል - ማለት ደግሞ «አምላክ» ማለት ነው። ይህን ማለትም የቅዱስ ሚካኤልን ስም በጠራን ቊጥር የምንመሰክረው ስለ እግዚአብሔር ነው፤ በመሆኑም እግዚአብሔርን በባሕርይ የሚመስለው፥ በሥልጣንም የሚተካከለው፥ በምድርም በሰማይም እንደሌለ የሚናገር ልዩ፥ ክቡር ስም ነው። የነቢያት አለቃ ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን ያሻገረለትንና ፈርዖንን ከነሠራዊቱ ያሰጠመለትን አምላክ እግዚአብሔርን በመዝሙር ሲያመሰግን፥ «አቤቱ በአማልክት መካከል (በስም አማልክት ከሚባሉ፥ በስመ አማልክት ከሚጠሩ፥ አንድም አማልክት ዘበጸጋ ከተባሉ ከነቢያት ከካህናት መካከል) አንተን የሚመስል ማነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማነውብሏል። ዘጸ ፲፭፥፲፩። ቅዱስ ዳዊትም፦ «አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፤» ብሏል። መዝ ፹፭፥፰።

በህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት  ታከብረዋለች ፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ህዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው ፡፡እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡(ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ እንደሆነ አክሲማሮስ በሚባለው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡)

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን ፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ ? አለው ፡፡ እርሱምእኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ”(ኢያ.፲፫) ይለናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር ፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስ ይዋጋው በጸሎትም ይራዳቸው ነበር ፡፡ ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡንበፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት”(ዘጸ.2321)ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር ፡፡ ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን ያስረዳናል ፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ አያረጋግጥም የሚል ካለመልአክየተባለው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ ገልጦልን እናገኛለን፡ሰይጣን ሠራዊቱን አሰማርቶ በአሕዛብ ነገሥታት እያደረ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባሉ እስራኤልን ዘወትር በጦርነት ያስጨንቃቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ሲወድቁ ሲነሡ፥ ሲነቀሉ ሲተከሉ፥ ሲፈርሱ ሲገነቡ፥ ሲበተኑ ሲሰበሰቡ፥ ሲሰበሩ ሲጠገኑ ኖረዋል። በዚያ ዘመን መጋቤ ብሉይ ተብሎ የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነው። እርሱም ዘወትር ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ሆኖ ሕዝቡን ይረዳቸው ነበርና። ይኽንንም «ወደ አንተ የመጣሁት ለምን እንደሆነ ታውቃለህን? አሁንም የፋርስን አለቃ እዋጋው ዘንድ እመለሳለሁ፥ እኔም ስወጣ እነሆ የግሪኮች አለቃ ይመጣል። (ሰይጣን በግሪክ ንጉሥ አድሮ ሌላ ጦርነት ይጀምራል) ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፥ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ (ከመላእክት አለቃ) ከሚካኤል በቀር የሚያጸናኝ የለም።» ዳን ፲፥፳፩ በማለት ቅዱስ ገብርኤል ለነቢዩ ለዳንኤል ነግሮታል። ቅዱስ ገብርኤል እንዲህ ካለ እኛስ ምን እንበል?

የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን አሜን።

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።