Mar 5, 2012

ምኩራብ (የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)


ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት «ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ» «ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ» እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ምኩራብ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡ የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 2112-13 ተጠቅሷል፡፡
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡
ትርጉም: ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው) ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።

ምንባባት መልዕክታት
(ቆላ. 2÷16-ፍጻ.) «እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፣ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፣ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል፡፡ ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ት ምህር ት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደሰው ሥርዓትና ት ምህር ት፡- አትያዝ አትቅመስ፣ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም ሁሉ እንደምትኖሩ ስለምን ትገዛላችሁ) እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና፡፡ ይህ እንደገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቈን ጥበብ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፡፡»
(ያዕ.5÷14) « ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል) እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን) ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል) እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡ በእግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡ አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን) አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን) እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን) መጽሐፍም አብርሃምም እግዚአብሔር አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን) ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡»
ግብረ ሐዋርያት
(የሐዋ.10÷1-8.) « በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፡፡ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፡- ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ ጌታ ሆይ ምንድር ነው) አለ፡፡ መልአኩም አለው፡- ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረገ፡፡ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ፡፡ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፣ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፣ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው፡፡ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፣ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ
ምስባክ
መዝ 689
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡
ትርጉም፦የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡
ወንጌል
ዮሐ. 2÷12-ፍጻ. «ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፡፡ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ፡፡ ስለዚህ አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክ ት ታሳየናለህ) አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን) አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡ በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡»
ቅዳሴ: - ቅዳሴ ዘእግዚእ 

እግዚአብሔር አምላክ በተዋሕዶ ሃይማኖታችን   በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችን ያጽናን፤ አሜን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።