Mar 5, 2012

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የመመረቂያ ፅሁፍ


‹‹ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ (የአዳም የውርስ ሀጥያት) ጥላ ስር የተወለደች ናት››
የአቡነ ጳውሎስ የመመረቂያ ፅሁፍ ላይ ከሰፈረ
(አንድ አድርገን የካቲት 26 2004 .)- ለዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ እንድዳፈር ያበረታታኝ ‹‹እውነትና ንጋት›› የተባለው የካርዲናል አባ ሰረቀ መፅሀፍ ነው ፡፡ ይህ መፅሀፍ ባልጎለመሰው እውቀቴና በተራው እኔነቴ ልደፍረው ያላሻሁትንና ለእናንተ አእምሮ በመጨነቅ ልገልጸው ያልፈለኩትን ጉዳይ አድበስብሶና ለሌላ አላማ አድርጎ ወደ ህዝቡ አድርሶታል፡፡ ድፍረቱ ላይ ግልፅነትን አክላችሁ ሌሎች ተደብቀው የቆዩና ተሰውረው ያሉ የመንፈሳዊ መሪዎቻችንን ሃይማኖታዊ ጉዳዮች (የመንፈሳዊ መሪዎቻችንን እንጂ የቤተክርስትያናችንን አላልኩም ቅድስት ቤተክርስትያን ምንም አይነትት የተደበቀ የሃይማኖት ጉዳይ የላትም) የሚሳዩ መጻህፍት ታስነብቡኝ ዘንድ ፍላጎቴና ምኞቴ ነው፡፡
ፍላጎቴና ምኞቴ የሃይማኖት መሪዎቻችንን ሰብዓዊ ማንነት እና ግለሰባዊ ህይወታቸውን መግለፅና ማወቅ አይደለም እሱ የኔ ወይም የናንተ  ጉዳይ አይደለም ባውቅም ምንም አይጠቅመኝም፤  የእኔ የእናንተ እና የእነርሱ የጋራ ጉዳይ የሆነው ሐይማኖት ነው ፡፡ ከሃይማኖት ደብቀው እና ሳይገልፁት የቆዩትን ወይም አባት ሆነው እየመሩት ካሉት እምነት አንፃር እርስ በእርስ የሚጋጭ አስተምህሮና እሳቤ ሌሎችንም ነገሮች ማወቅ ነው የኔ ፍላጎት ፡፡ ለምን ስለ ድብቁ ሃይማኖታዊ እሳቤያቸው ማወቅ አሰፈለገክ ? ትሉኝ ይሆናል፡፡ መልሴ ለጠቅላላ እውቀት የሚል አይደለም መልሴ ስለ ሃይማኖቴ ይገደኛል ይመለከተኛል የሚል ነው በእምነቴ ዙሪያ የሚነሱ ይህን የመሰሉ ጉዳዮችም ሳይሆኑ ትናንሾቹንም ቢሆኑ ማለፍ ስለማልችልም ጭምር ነው፡፡

በእርግጥም ስለ እምነቴ እጨነቃለሁ ስለ ቤተክርስትያኔ አስባሁ፡፡ እምነቴ ውስጥ እኔ ቤተክርስትያኔ ውስጥ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ እና ደጋግ ሕዝቦቿ አሉ እናም ይገደኛል አውቀህስ ምን ታደርጋለህ ? ልትሉኝ ትችላላችሁ እኔ ደግሞ እቃወማለሁ እላችኋለሁ ልክ እንዳልሆኑ እየተናገርኩ እቃወማለሁ የተሳሳተውን ነገር በመግለፅ እቃወማለሁ   የቤተክርስትያናችን አስተምህሮ አይደለም እያልኩ እቃወማለሁ እምነቴን በህይወቴ እየመሰከርኩ እቃወማለሁ ስለ እውነት አጥብቄ እየጮህኩ እቃወማለሁ ……. ጩህት የት ሊደርስ ? ብትሉኝ መቼም ወደ ጎን ስለማልጮህ ወደ ላይ እንደመጮሄ  ጩህቴ ከሚደርስበት ይደርሳል ፡፡ አዎን በእነዚህ ነገሮች እቃወማለሁ ተቃውሞዩ ምን ለመፍጠር ወይም ምን ለማምጣት እንደሆነ ለእናንተ መንገር አይጠበቅብኝም ፡፡ ታውቁታላችሁና
እመቤታችን የአዳም የውርስ ሀጥያት(ጥንተ አብሶ) ነበረባት›› እና ‹‹ እመቤታችን ጥንተ አብሶ የአዳም የውርስ ሀጥያት የለባትም›› ሰሞኑን ቤተክህነት አካባቢ መነጋገሪያ የሆነ ርዕስ ነው ፡፡ ርዕስነቱ ‹‹አለባት›› ‹‹የሌባትም›› በሚል ሳይሆን የቤተክርስትያኒቱ ፓትርያርክ (/ አቡነ ጳውሎስ) እመቤታችን የአዳም የውርስ ሀጥያት ነበረባት ማለታቸውን የሚገልጥ መጽሀፍ (የሚገልፅ ከምለው የሚጠቁም ብለው ይሻላል) ምክንያቱም መፅሀፉ ‹‹እውነትና ንጋት ›› ላይ የአቡነ ጳውስ መፅሀፍም ይህን ሀሳብ ይደግፋል ብሎ ያቀረበው ፅሁፍ አሻሚ ስለነበረ ነው
(According to the eastern Orthodox church the blessed virgin is truly human , sharing the original sin which is part and parcel of humanity, and it’s in her it infirmity which ultimately expresses itself in natural death) ገፅ 61
(እንደ ምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አስተምህሮ ቅድስት ድንግል ማርያም ሰው እንደመሆኗ በሰው ዘር ላይ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ራሱንም በተፈትሯዊ ሞት የሚገልጸውን ጥንተ አብሶ ትጋራለች፡፡) ይህ የሚወራው ስለ ምስራቅ ኦርቶዶክስ  ቤተክርስትያን ስለሆነ አቡነ ጳውሎስ ሀሳቡን ይደግፉታ አያስብልም ነገር ግን አቡነ ጳወሎስ ሊደግፉት ይችላሉ የሚል ጥቆማ ሰጥቶን ያልፋል ምክንያቱም ‹‹የእውነትና ንጋት›› መጽሀፍ ጸሀፊም ሆኑ አብሯቸው ያሉ ሰዎች ከመሬት ተነስተው አቡነ ጳውሎስ ይህን ሀሳብ ይደግፉታል አይሉም፡፡ ( በቤተክርስትያኒቱ አባት ተጽፎ በጠቅላይ ቤተክርስትያን አዳራሽ ውስጥ መመረቁ አንዱ ነው)፡፡
ሰለምን እያወራሁ እንዳለ ተረድታችሁኛል ስማንስ እየጻፍኩ እንደሆነ ያቺ ገና ከማህፀን ሳትወጣ ጀምሮ ስሟን የሰማነው አነዚያ ቅዱሳን አባቶቻችን ስሟን ሲያወድሱ ውለው ቢያድሩ የማይጠግቧትን ለውሻ ራርታ በወርቅ ጫማዋ ውሃ ያጠጣችውን የሰማይና የምድር ጌታን ዘጠኝ ወር በማህጸኗ የተሸከመችውን ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ነው የማወራው ፡፡ አሷ ከሴቶች የተለየች ከፍጥረት ሁሉ የተለየች መሆኗ ተረስቶ እሷም እንደ እኔ እና እንደ እናንተ የአዳም የውርስ ሀጥያት ተካፋይ ናት ተባልን ይህን ማን እንዳለሁ እነግራችዋለሁ፡፡  የዛሬ 24 ዓመት በፊት አሜሪካ ፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ የያኔው 52 ዓመት የዶክትሬት ተማሪ  የአሁኑ 76 ዓመት ፓትርያርክ የያኔው ተማሪ የአሁኑ / የያኔው ስደተኛ የአሁኑ ፓትርያርክ ብጽዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ናቸው ይህን በመጽፋቸው ያሰፈሩት፡፡ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ በፍልስፍና ዶክትሬታቸውን ያገኙት ወይም ለዶክትሬታቸው ማሟያ የሆነው (Dissertation) የጻፉት ይህን በማለት ነው ፡፡ ይህን ሲሉም የግል አመለካከታቸው ወይም የእሳቸው ብቻ እሳቤ እንደሆነ አይደለም የገለፁት እናንተ እና እኔ ብሎም እነዚያ በህይወት ያለፉት ደጋግ ቅዱሳን አባቶቻችን የሚያምኑት እውነትና እምነት ብለው ነው የተናገሩት ፡፡
 “The author shows that Ethiopia Orthodox Trilogy sees the blessed virgin Mary, Mother of God on the one hand as honored by God above all other creatures is being chosen as the mother of God , the word incarnate, but on the other hand as a human being, born under the shadow of original sin “  (page Viii)
አጥኝው ማሳየት የፈለጉት ‹‹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ብፅእት ድንግል ማርያምን የአምላክ እናት አድርጋ ብትመለከትም በሌላ አገላለጽ አካላዊ ቃል በስጋ ለመውለድ የአምላክ እናት በመሆን ምርጫ ውስጥ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የተከበረች ብትሆንም ነገር ግን በሌላኛየሰው ዘር በጥንተ አብሶ (የአዳም የውርስ ሀጥያት) ጥላ ስር የተወለደች መሆኗን የኢትዮጵያው ገፅታ እንደማንኛውም  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የስነ መለኮት አስተምህሮ ይገልፃል…››
ይህን ጽሁፍ የምታገኙት በጥናቱ አስተዋፅኦ (ABSTRACT) ላይ ነው:: የጥናታቸው ርዕስ “ Filsata : the Feast of the Assumption of the virgin Mary and the Mariological  Tradition of the Ethiopia Orthodox Tewahedo Church” ይሰኛል ፡፡ “Princeton Theological Seminary” ጎግል ላይ ገብታችሁ “Order NO 8818495” እና “Yohannes Paulos” የሚለውን ስትጽፉ ጎግል ጎልጉሎ ያወጣላችኋል፡፡ ይህ አስተምህሮ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ይወክላልን? ቤተክርስትያናችን እንዲህስ ብላ አስተምራ ታውቃለችን? የቤተክርስትያኒቱ የእምነትና የሥርዓት መፅሀፍ ሆኖ 1988 . 22 ሊቃውንት ተጠንቶ በዘመነ አቡነ ጳውሎስ ጊዜ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነትና ስርዓተ አምልኮትና የውጭ ግንኑነት›› በሚል ርዕስ በአማርኛና በእንግሊዘኛ የታተመው መፅሀፍ ይህ ከላየ የተመለከታችሁት  የአቡነ ጳውሎስን ፅሁፍ እንዲህ በማለት ይቃወማል፡፡
‹‹አምላክን በድንግልና  ጸንሳ በድንግልና የወለደችው የእመቤታችን የድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጥያት(ጥንተ አብሶ) ያላገኛት መርገመ ስጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ህሊና ታስባ ትኖር የነበረች…››(ገጽ 49) ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ሀሳቦችን በአንድ ሰው በዶ/ አቡነ ጳውሎስ ሲዘነዘሩ አይተናል በመጀመሪያው ላይ ራሳቸው ቃል በቃል  ‹‹ በጥንተ አብሶ (በውርስ ሀጥያት) ጥላ ስር ነበረች›› ብለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ ሳይሆን ‹‹ነው›› በማለት ዶክትሬታቸውን አግኝተውበታል ፡፡ (ልብ ይበሉ የዶክትሬት ማግኛ ፅሁፋቸውን የተሰራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በማታምነውን እኛም በማናምነው ጉዳይ ነው  ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ይህን የገለጹት ለህዝብም በይፋ ያሳወቁት ካርዲናል አባ ሰረቀ መሆናቸው ነው፡፡ የቤተክርስትያን አባቶች ቅዱስ ሲኖዶስ ስራቸውን ሚዛን ላይ አስቀምጦ ከሀላፊነታቸው በጥቅምት ወር ያነሳቸው የአቡነ ጳውሎስ የቅርብ ወዳጅ በሆኑት ካርዲናል አባ ሰረቀ ነካክተው የተደበቀውን ነገር አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ጉዳዩ ጸሀይ እንዲሞቅ በአደባባይ አውጥተውታል ፡፡ ማንም ሰው በመንፈሳዊም ሆነ በአለማዊ ትምህርት ላይ የፈለገውን ሀሳብ አንስቶ ማራመድ ይችላል መብቱም ነው ሀሳቡን እንደፈለገው የማንሸራሸር መብት አለው፤ እግዚአብሔርም የለም ብሎ ማመን የእሱ ብቻ መብት ነው ፡፡ ነገር ግን አንድን እምነት ወክሎ የራሱን ሀሳብ የእምነቱ አድርጎ መናገርም ሆነ ማቅረብ ግን አይችልም፡፡
‹‹እውነትና ንጋት›› የተሰኝው መጽሀፍ ለህዝብ እስከሚደርስ አቡነ ጳውሎስ ያን የጥንቱን የአሜሪካውን ትምህርት ቤት እሳቤያቸውን በትምህርት ቆይታቸው ወይም ዶክትሬታቸውን እስኪይዙ ድረስ ብቻ አብሯቸው የቆየ ነው የመሰለኝ ፡፡ ምክንያቱን በዘመነ ፓትርያርክነታቸውም በእሳቸው መልካም ፍቃድ ይህን የተማሪ ቤት ቆይታቸው ወቅት ያንፀባረቁትን መጽሀፍ በማፃፋቸው ነው፡፡ 24 ዓመት በፊት ያሉትን ነገር ትተውታል ወይም በነገሩ ላይ የበሰለ እውቀት ሳይኖራቸው የፃፉት ነው ብዬ አስብ ነበር ፡፡ አሁንም ሊሆን ይችላል ፡፡ ግን የአባ ሰረቀ መጽሀፍት በቤተክህነት አዳራሽ ተመርቆ  ለህዝብ መቅረቡን አቡነ ጳውሎስ በነገሩ ላይ ዝም ማለታቸው ዳግም አስገርሞናል፡፡
እርግጥ ነው / አቡነ ጳውሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አምስተኛ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ቢሆንም እሳቸውም ሰው ናቸው አባትም ናቸው ስለሆኑም እኔ ሀጥያተኛ እና መሀይም ልጃቸው ነገሩ ቢያጠራጥረኝ ጉዳዩ ጥያቄ ቢፈጥርብኝ አይፈረድብኝም፡፡ ያነሳሁት ጉዳይ ቤታችንን ስለሚያምሱ አውርቶ አዳሪዎች እና ሴት ወይዛዝርቶች አይደለም፡፡ ለሰው ልጅ ድህነት ምክንያት የሆነችው ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ቀኑን ሙሉ ስሟን ሲጠራ ቢውል የማይረካን የእመቤት ማርያምን ጉዳይ ነው ያነሳሁት፡፡ ስለዚህ አትዘኑብኝ እሷ ከደሜ እና ከደማችሁ ተዋህዳለች እንግዲህ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህን ብያለሁ / አቡነ ጳውሎስ ‹‹የመመረቂያ ፅሁፍዎን›› ወይም ‹‹የቤተክርስትያኒቱን አስተምህሮ››  ከሁለት አንዱን ይምረጡ ብያለሁኝ፡፡ አበቃሁ። 
እግዚአብሔር አምላክ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታችንን ኢትዮጵያ ሃገራችንን ይጠብቅልን። አሜን።

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።