በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩት ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ደብረ ታቦር ነው፡፡ በዓሉ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ ታቦር ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ ደቡብ በኩል 10ኪ.ሜ ርቆ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ይህ ተራራ ከባሕር ጠለል 572 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ «ባርቅ የተባለው ጦረኛ ሕዝበ እስራኤልን ይዞ በመዝመት ሲራ የተባለውን የሕዝብ ጠላት በታቦር ድል ነስቶ አሸንፏል» (መሳፍንት.4፡6-14)፡፡
የታቦር ተራራ ደቡባዊ እይታ (Jezreel Valley, Galilee, Northern Israel)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ረጅም ተራራ የወጣው ብርሃነ መለኮቱን ክብሩን ለመግለጽ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ተነጋግሮአል፡፡ እነዚህም ሁለት ታላላቅ ሰዎች በበብሉይ ኪዳን ጊዜ ስለ ክርስቶስ ትንቢት የተናገሩ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያስተማሩ ቅዱሳን ነቢያት ነበሩ፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፡፡ ክንድህ ከኃይል ጋር ነው ሲል በመዝሙር 88፡12 ስለ ታቦር ተራራ ዘምሯል፡፡ የታቦር ተራራ በገሊላ ከሚገኙ ተራራዎች አንደኛው ሲሆን በዛብሎን ክፍል ውስጥ ለሚኖሩ ልጆች የተሰጠ ቦታ ነው፡፡ 1ኛ ዜና.6፡77 ሐዲስ ኪዳን ግን ረጅም ተራራ ከማለት በስተቀር ታቦር ብሎ ስሙን አይጠራውም፡፡ ሆኖም ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ክብሩን እንደገለጠና የዚህም ተራራ ስም ታቦር መሆኑን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ገልጠዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ረጅም ተራራ ደብረ ታቦር እያለ በድጓው አስፋፍቶ ጽፏል፡፡
ከነቢያት መካከል ሁለቱ ቅዱሳን ነቢያት እንዲገኙ ያደረገውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሣርያ ተገኝቶ «ደቀ መዛሙርቱን ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል) ሲል ጠየቃቸው ከእነሱም አንዳንዶቹ ኤልያስ፣ አንዳንዶቹም ሙሴ፣ ነው ይሉሃል አሉት፡፡ እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ) ቢላቸው አብዛኛዎቹ ኅብረተሰቡ ከሚለው ጋር ሲተባበሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ሲል መሰከረ፤ ኢየሱስም መልሶ ይህን በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ አለው» ማቴ.16፡13-18፡፡
በዚህ አኳኋን ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ይዞ ወጥቶ ራሱ ኤልያስ ወይም ሙሴ አለመሆኑን ገለጠላቸው፡፡ ከሞተ ብዙ ዘመን የሆነውን ሙሴን ከመቃብር አስነስቶ ቀጥሎም በእሳት ሠረገላ ያረገውንና በተድላ ገነት የሚኖረውን ኤልያስን በተራራው እንዲገኝ አድርጐ አብረውት የነበሩት ደቀ መዛሙርት ሙሴ ነው ወይም ኤልያስ ነው በማለት ሲጠራጠሩ እንዳይኖሩ ትምህርት ለመስጠት ነው፡፡
ማቴ.17፡2 «በፊታቸው ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ» ይላል፡፡ የክርስቶስ ፊቱ እንደ ፀሐይ የበራው የብርሃኑም ኃይል ያንፀባረቀው የብሉይ ኪዳን መሪ እንደነበረው እንደ ሙሴ ፊት ብርሃን አይደለም፡፡ «ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ የፊቱ ቆዳ አንፀባረቀ አሮንና እስራኤልም ይህንን ስላዩ ወደ እሱ ይቀርቡ ዘንድ ፈኸ ተሸፈንም እያሉ ጮኹ «ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ለእነሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ» ይላል፡፡ ኦሪት ዘፀ.34፡29-30፡፡ የሙሴ የጸጋ ነው የክርስቶስ ግን የባሕርይ ነው፡፡ «ብሩህ ደመና ጋረዳቸው» ይላል ይህ በሲና እንደታየው ያለ አይደለም፡፡ በታቦር የታየው ግን ብሩህ ነበር፡፡ በደብረ ሲና የተገለጠ የፍጡር የሙሴ ክብር ነበር፤ በደብረ ታቦር ግን የሕያው ባሕርይ የክርስቶስ ክብር ተገልጦአል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ማኅበረ ቅዱሳን
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።