ጾመ ፍልሰታ ሐዋርያትን
አብነት አድርገው ሐዋርያት
የተቀበሉትን በረከት ለማግኘት
ኦርቶዶክሳዊያን የሚጾሙት ጾም
ነው። ፍልሰታ የግዕዝ ቃል
ሆኖ ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ
ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም
ተለየ፣ ሄደ፣ ከአንድ
ቦታ ወደ ሌላ መሄድን
ያመለክታል።
እመቤታችን እንደ ሰው
ልማድ ሞትን ትቀምስ ዘንድ
ግድ ስለሆነ ጻዕርና ሕማም
በሌለበት አሟሟት በተወለደች
በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን
48 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም
በሞተ ሥጋ አርፋለች። ሐዋርያትም
እንደምታርፍ በመንፈስ ቅዱስ
ስለተገለጸላቸው ከያሉበት ወደ
መኖሪያ ቤቷ (የዮሐንስ
ቤት) መጥተው ነበር።
ነፍሷ ከሥጋዋ እንደተለየች አስከሬኗን
ገንዘውና ከፍነው ወስደው
ለመቅበር ወደ ጌቴሴማኒ
ሲሄዱ አይሁድ ሰምተው መጡና
ሐዋርያትን ከበቧቸው። የአይሁድ
ተንኮል አስከሬኗን ከሐዋርያት
እጅ ቀምተው በእሳት ለማቃጠል
ነበር፤ ይህንም ማድረግ
የፈለጉት የሐዋርያት ትምህርት
የጌታችን ከሞተ መነሳትና
ለፍርድ ተመልሶ መምጣት
ከአይሁድ አልፎ ዓለም
ሁሉ እያመነበት ስለመጣ እመቤታችንም
ተነሥታ ዐርጋለች እያሉ
ሐዋርያት ያስተምራሉ በሚል
ስጋት ነበር። የፈሩት ይነግሣል
የጠሉት ይወርሳል እንዲሉ
የእመቤታችን ትንሣዔም ሆነ
ዕርገት አይቀሬ ሆኗል።
ሐዋርያትም ለእመቤታችን ካላቸው
ክብርና ፍቅር የተነሳ
ለምን አልቀበርናትም? ለምንስ የሥጋዋ
ምሥጢር ይደበቅብናል? በማለት
እያዘኑና እየለመኑ ለስድስት
ወራት ከአሥር ቀናት ቆይተዋል።
ከዚህ በኋላም ከነሐሴ 1 ቀን
ጀምረው ሱባዔ ይዘው
ለ14 ቀናት እግዚአብሔርን በጾምና
በጸሎት ጠየቁት። በመጨረሻም
የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን
የማይነሳ ልጇ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ነሐሴ 14 ቀን ሥጋዋን አምጥቶ
ስለሰጣቸው ሳይውሉ ሳያድሩ
በዕለቱ በጌቴሴማኒ በታላቅ
ክብርና ዝማሬ ቀበሯት።
በተቀበረችም በ3ኛው
ቀን በነሐሴ 16 ከተቀበረችበት መቃብር
ተነሥታ ወዲያውኑ በታላቅ
ክብር በመላእክት አጃቢነት ወደ
ሰማይ ዐርጋለች።
ጥበበኛው ሰሎሞንም “ውዴ እንዲህ ይለኛል
ሙሽራዬ ውዴ ሆይ!
ተነሺ የእኔ ውብ ሆይ
ነዪ አብረን እንሂድ” በማለት
አመሣጥሮ የተናገረው በጥበበ
እግዚአብሔር ተመርቶ እንደ
ክርስቶስ ሆኖ ውዴ
ያላት እመቤታችን መሆኗንና ልጇ
ተነሥቶ እንደ ዐረገ
እሷም መነሣቷንና ማረጓን እንረዳለን።
/መሓ ፪፥፲/። እመቤታችን
ባረገችበት ጊዜ ቶማስ
በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ
በደመና ተጭኖ ከሀገረ
ስብከቱ (ሕንድ) ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ
እመቤታችን በመላእክት ታጅባ
ወደ ሰማይ ስታርግ ተገናኙ።
በዚህ ጊዜ ቶማስ ቀድሞ
የልጇን ትንሣኤ ሳላይ
አሁንም ደግሞ እርሷን
ሳልቀብራት ከትንሣኤዋም ሳልደርስ
ቀረሁ ብሎ አዘነ፤ ሆኖም
እመቤታችን ዕርገቷን ከእርሱ
በስተቀር ሌሎች አለማየታቸውን ገልጻ አረጋጋችው፤ ዕርገቷንም
ለሐዋርያት እንዲነግርና ምልክትና
ማስረጃ እንዲሆነው ተገንዛበት
የነበረውን ሰበኗን /የከፈን ጨርቅ/ ሰጥታ
አሰናበተችው።
ቶማስም መሬት ለይ
ወርዶ መቀበሯን፣ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን
ያላወቀ መስሎ ሐዋርያትን
ስለ እመቤታችን ሥጋ ጉዳይ
ጠየቃቸው፤ እነርሱም ሱባዔ
ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት
መጠየቃቸውን፣ ከሱባዔያቸው በኋላ
የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ
ሥጋዋን መላእክት አምጥተው
እንደሰጧቸውና እንደቀበሯት አስረዱት።
እርሱ ግን ሞት በጥር
በነሐሴ መቃብር እንዴት
ሊሆን ይችላል? ሲል ተከራከራቸው። ሐዋርያትም ቶማስን ለማሳመን
መቃብሯን ለማሳየት ወሰዱት
ሆኖም መቃብሯ ባዶ ሆኖ
አገኙትና ተደናገጡ፤ በዚህ
ጊዜ ቶማስ የሆነውን ሁሉ
ገልጾ ለምልክትና ለማረጋገጫ የሰጠችውን
ሰበኗን /ተገንዛበት የነበረውን
ጨርቅ/ የራሱን ድርሻ
አስቀርቶ አከፋፍሎ ሰጣቸው
ዛሬም ካህናቱ ከእጅ መስቀላቸው
ጋር መሐረብ የሚይዙበት ምክንያት
ሐዋርያት የተከፋፈሉት የእመቤታችን
ሰበን ምሳሌ ነው።
ሐዋርያትም የዕርገቷን ምሥጢር
ካመኑ በኋላ ዕርገቷን ለማየት
በዓመቱ በተመሳሳይ ሁኔታ
እንደገና ከነሐሴ 1 ቀን
ጀምረው ለሁለተኛ ጊዜ
ለሁለት ሱባዔ ገቡ፣
እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ
በነሐሴ ወር በ16ኛው
ቀን ጌታችን ሐዋርያትን ወደ
ሰማይ አውጥቷቸው እመቤታችንን አግኝተዋት
ከሷ ተባርከው በታላቅ ደስታ
ወደ ደብረዘይት ተመልሰዋል።
በአጠቃላይ የእመቤታችን ለሐዋርያት
በተለያዩ ጊዜያት መታየት፣
የሥጋዋና የነፍሷ ከቦታ
ቦታ መንቀሳቀስ ፍልሰት ሲባል
ከዚህ የተነሣ የነሐሴ ጾም
በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት
ሐዋርያት ያገኙን በረከት
ለማግኘት ጾመ ፍልሰታን
እንጾማለን።
በዶ/ር ሙሉጌታ ማርቆስ
ምንጭ፦ማ/ቅዱሳን ፤ አሜሪካ ማዕከል
አምላካችን ጾሙን የተባረከ ያድርግልን።
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።