Sep 7, 2012

የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል መታሰቢያ

ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡ ዕብ. 13.1-2

ርኅወተ ሰማይ በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ ታላላቅ በአላት መካከል አንዱ ሲሆን የሚውለውም ጳጉሜ 3 በየዓመቱ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ቀን ነው፡፡ ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት እንደማለት ሲሆን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ ሁሉ ፀሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ከአምላክም የሚወርድበት አለት ነው፡፡ በዚህች እለት ቅዱሳን መላእክት የምእመናንን ልመና መስዋእቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካችንን ምህረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት እለት በዚህች ቀን በሚዝንመው ዝናምም በእግዚአብሔር ቸርነት ብዙ ድውያን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስን ያገኛሉ መካኖች ከማየ ፀሎቱ ጠጥተውም ማህፀናቸው ይከፈታል ሌሎች ብዙ ተዓምራትም ይደረግባታል፡፡
ጳጉሜ 3 የሊቃነ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል  መታሰቢያ ነው ፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን (የራጉኤልን ልጅ) ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡

"የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡" መጽ. ጦቢት::
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላአባባ የነገርከኝን ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እፈጽማለሁ ግን ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? ሀገሩን አላውቀውምአለው፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሩ አሳሳቢ ሆኖ ስላገኘው ጦቢት ልጁ ጦብያንአብሮህ የሚሄድ ሰው እስቲ ፈልግ ምናልባት አብሮ የሚሄድ ጓደኛ ታገኝ ይሆናል ደመወዝም ሰጥተን ቢሆን ካንተ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ ያስፈልግሃልና ሂድ ሰው ፈልግአለው፡፡
አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ቢሄድ አንድ መልካም ጐበዝ አገኘ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ጦብያ ግን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጦብያ መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘውየሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን የድካምህን ዋጋ የጠየቅኸውን ያህል እሰጥሃለሁሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልምእሺ ካንተ ጋር ለመሄድ ፈቃኛ ነኝ መንገዱንም ሆነ ሀገሩን በሚገባ አውቀዋለሁ ከገባኤል ቤት ብዙ ጊዜ ኑሬአለሁናአለው፡፡
ከዚህ በኋላ ጦብያ በል ከአባቴ ጋር ላስተዋውቅህ ብሎ ወደ አባቱ ወስዶ አስተዋወቀው ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው በማለት ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም የታላቅ ወንድምህ ወገን ከመሆንም ሌላ ስሜም አዛርያስ ይባላል አለው፡፡ ጦቢ. 5.12 ፡፡ ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላአንተስ ወንድሜ ነህ በል የልጄ የጦብያን ነገር አደራ ከሀገር ወጥቶ አያውቅምና እንዳይደነግጥ ደኅና አድርገህ እንድትይዝልኝብሎ ስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤልመራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡ እነርሱ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው  ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው ዓሣውን እንዳትለቀው አለው ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው ፡፡ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡  ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡
ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፣ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው አደረጉት፡፡ ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን እንደሚያገለግል ለመረዳትይህን ያዘው ያልከኝ ለምንድን ነው?› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ጋኔን ያደረበት ሰው ሲገኝ ይህንን ከዕጣን ጋር ቢያጤሱበት ጋኔኑ ይለቃል ሲል መለሰለት፣፡
በዚህ ሁኔታ አንድ ባንድ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያንዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱ ዘመድህ ነው፡፡ የእርሱም ልጅ ሣራ የምትባል ቆንጆ ልጅ አለችው፡፡ እሷን ለሚስትነት ይሰጥህ ዘንድ ለራጉኤል እነግርልሃለሁአለው፡፡ ጦብያምያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ እንደሚያድሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁአለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን  ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን መሰለህ ያዘው ያልኩህ ? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር  ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለንአለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳለው ሚስቱ አድናንይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላልአላት ከዚያም ጋር አያይዞልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነሱምከነነዌ ሀገር ነው የመጣንአሉት፡፡ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለትእናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝአለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤልየወንድሜ ልጅ ነህን?› ብለ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
ራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ  ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያንልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግአላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነመልአከ ከብካብይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን 14 ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡ 14 ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡
በመጨረሻም ከጦብያ ጋር ሄዶ የነበረው  መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት ጠሩት እርሱ ግን ጦቢትንና ጦብያንፈጣሪያችሁን አመስግኑ እናንተ እስከ ዛሬ ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ /መጽ. ጦቢት/፡፡  
የጳጉሜ ወር  ዳግም ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡ አምላካችን ዳግም ሲመጣ በመንግስቱ እንዲያስበን ተግተን ልንፀልይ ሁሉን በስርአት እንድናደርግ  ይገባል፡፡
 ጦቢትን በሥራው  ሁሉ የረዳ  በችግሩም ያፅናናው ሊቀ መላእክት ሩፋኤል እኛንም ከመከራ ስጋ ከመከራ ነፍስ እንላቀቅ ዘንድ ይራዳን ያማልደን በረከቱ ሁሌም አይለየን አሜን፡፡
አዲሱ አመትም የሰላም የፍቅር የመከባበር አመት እንዲሆንልን አምላክ ይርዳን ፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።