Sep 9, 2012

ዕንቁጣጣሽ

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ


ዘመነ ማቴዎስም፣ ዘመነ ማርቆስም፣ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ፤ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡

ኃይማኖታዊ መሠረት

ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍ «የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልእከተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጅ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ» ተብሎ በኢሳይያስ እንደ ተነገረ የነቢዩ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነሥቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ ለኃጢአት ሥርየት እየሰበከ መጣ ብሎ በዘመነ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ገልጾታል፡፡ /የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ ቁጥር ፵፤ ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ - /
የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተክርስቲያን አበው የበዓላቱን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በሚሆን መስከረም ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ አባቶች ደንግገዋል፡፡ / ድርሳነ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1 3/ ይህንንም በዓል አባቶቻችን በርእሰ ዓውደ ዓመት ማክበር እንደሚገባ አስበው ያደረጉት ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ሆኖ አይደለም፡፡ ለአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዓውደ ዓመት «ቅዱስ ዮሐንስ» ይባላል፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል ፲፪ ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡
ከዚህ በመቀጠል በዓሉ በተለያየ ስያሜ ስለመጠራቱና ትርጓሜያቸውን እንመለከታለን፡፡

ዘመን መለወጫ

አስቀድመን ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ማንነትና የዘመን መለወጫ መግቢያው ላይ በስሙ ስለመጠራቱ ተመልክተናል፡፡ ዘመን መለወጫ ደግሞ ለምን እንደተባለና ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ያትታሉ፡፡ ሲያትቱም ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱንም ጠንቀቀው ቢቆጥሩት ፫፻፷፬ ቀናት ይሆናል፡፡ ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትን ፈጠረ ይላልና /መጽሐፈ ሔኖክ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፵፱፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድረገው የአቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡/መጽሐፈ ኩፋሌ፡ ምዕ ቁጥር /
በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምትን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡

"ዕንቁጣጣሽ" አመጣጥ

ዓመታት ተፈጽመው አዲስ ዓመት ስንጀምር ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ዕንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱት ዕንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜው አመጣጥ ወይም ጥንተ ታሪክ በመጀመሪያ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪቃ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪቃ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኃ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡
ሁለተኛው የሀገራችን ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ዜና ጥበብ እየሰማች ስታደንቅ ትኖር ነበር፡፡ በጆሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ዓይታ ለመረዳት ስለፈለገች በግመሎች ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ በኢየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ ከንጉሡ ሰሎሞንም ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገጸ በረከት ከሰጠችው በኋላ ብዙ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ላይ ሰውሮ ሁሉንም ገለጸላት፡፡ ቤተ መንግሥቱንም፣ በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ ዕቃዎችን ሁሉ አስጎበኛት፡፡ ሲያበቃ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ አበረከተላት/ሰጣት/፡፡ ወሩም ወረኃ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው መጥቷል፡፡ አሁን ከሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት ደርሶ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሚከበረውም መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡
አንድም «ዕንቁ ዕፅ አወጣሸ» ብሎ የአበባውን መፈንዳትን ያስረዳናል፡፡

ባህል ነክ ስርዓቶች

የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸውና ከሚያዘክራቸው በዓላት አንዱና ተወዳጅ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። እንደ ዕፅዋት ሁሉ ሰው በመስከረም ላይ በተስፋ ስሜት ይለመልማል። ከቅዱስ ዮሐንስ ዋዜማ ጀምሮ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጐዘጐዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል። በተለይም ልጆች አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። በአመሻሽ ላይ ችቦ አቀጣጥለው "እዮሐ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፣ እዮሐ የበርበሬ ውኃ፣ በሸዋ በጐንደር በትግራይ በሐረር... ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ፣ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ። እንጉርጉሮ ገባሽ በያመቱ ያምጣሽ.." እያሉ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች (በተለይ በገጠር) ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ ያድራሉ።
የሚያበሩት ችቦና የሚያነዱት እሳት በግርማ ምሽት ሲንቀለቀል ውጋገኑ ካገር አገር ከሰፈር ሰፈር ከቦታ ቦታ... ይታያል። በዕንቁጣጣሽ መዓልት በተደመረው ሰፈርተኞች ከርቀትም ከቅርበትም ይሰበሰባሉ። አባቶች ይመርቃሉ። "ዝናሙን ዝናመ ምሕረት፣ እህሉን እህለ በረከት ያድርግልን፣ ሰላም ይስጠን፣ እህል ይታፈስ፣ ገበሬ ይረስ፣ አራሽ ገበሬውን፣ ሳቢ በሬውን ይባርክ፣ ቁንጫን፣ አንበጣን፣ ትልን... ያጥፋ፣ ምቀኛን ሸረኛን ያጥፋ፣ ወጡ ገቡ ሰቡ ረቡ የሚለውን ሁሉ እግሩን ቄጠማ ዓይኑን ጨለማ ያድርገው፣ ያርገው፣ ያርገው፣..." ይባባላሉ።
እናት አባት ዘመድ አዝማድ በልጆቻቸውና በወዳጅ ዘመዶቻቸው የተበረከተላቸውን የዕንግጫ ጉንጉን (የአበባ አክሊል) በራሳቸው፣ እንጀራ ማቡኪያቸው፣ በመሶባቸው፣ በወጋግራቸው... ላይ ያስራሉ። ከምሽት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በየቤቱ የተዘጋጀው ድግስ ይበላል፣ ይጠጣል።
በነጋታው የዕንቁጣጣሽ ዕለት ልጃገረዶች በሙሬ ወገባቸውን አስረው የሀገር ባህል ወይም ዘመናዊ ቀሚስ (ልብስ) ለብሰው አሽንክታብ ጨረቃ ጠልሰም፣ ብር ማርዳ (ዶቃ) ድሪ፣ መስቀል፣ የአበባ ጉንጉን በአንገታቸው ላይ አጥልቀው ዓይናቸውን ተኳኩለው፣ ፀጉራቸውን ጋሜ ቅርፅ ተሰርተው፣ ራሳቸውን በአደስና በአሪቲ የተቀመመ ለጋ ቅቤ ተቀብተው በራስ ማሰሪያ ሸብ አድርገው፣ የብር መስቀላቸው ላይ አሪቲ (ሪያ) ሰክተው፣ እጅና እግራቸውን እንሶስላ ሞቀው በክንዳቸው አምባር አስረው፣ ብርአልቦ በእግራቸው፣ ብር ቀለበት በጣታቸው አድርገው፣ ሎሚ በጉንፋቸው ይዘው አሥር አሥር በመሆን ክብ ይሰሩና በእጆቻቸው ጭንና ጭናቸውን መሬቱን እየተመተሙ ተንበርክከውና ቁጢጥ ብለው ድሪያ ይጫወታሉ።በከተማው የእንቁጣጣሽ ባህል ደግሞ አበባዬ ሆይ ባልንጀሮቼ.. እያሉ ገንዘብ ይለምናሉ፣ ሲቀበሉም ከብረው ይቆዩን... ይላሉ። ገጠሬዎች ግን ይጫወታሉ እንጂ አይለምኑም።
ምንጭ፦የቦሌ መንበረ ብርሃን ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት

መጪው አዲስ ዓመት የፍቅር፣  የሰላምና  የብልፅግና
ዘመን  እንዲሆንልን የቅዱስ እግዚአብሔር
ፈቃድ ይሁን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።