Nov 14, 2012

ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዴት እናንብባቸው?


ምንጭየያሬድ ቤት

፩፦ተራ ጠብቆ ማንበብ

ቅዱሳት መጻሕፍት ስመ ሥላሴን ጠርተው ከሚጀምሩበት የመጀመሪያ ምዕራፍ አንሥቶ እስከ ፍጻሜያቸው የሐሳብ የታሪክ ቅደም ተከተል አላቸው፡፡የሚያነባቸው ሰው ሊረዳቸው የሚችለው ይህንን ቅደም ተከተል ጠብቆ ሲጓዝ ነው፡፡አንዳንድ ጊዜ በመካከል  ለየት ያሉ ታሪኮች ሲገጥሙን እንኳን ለጊዜው ተያያዥነታቸውን ባንረዳውም የኋላ ኋላ ግን እየተረዳነው እንሔዳለን፡፡የተጻፈበት ዓላማ ግልጽ እየሆነልን የሚመጣበት ጊዜ አለ፡፡ከዚህ አንጻር ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ የሚጀምረው ሰው በዘፈቀደ በተገኘው ሥፍራ ገልጦ ከማንበብ ይልቅ መስመሩን ጠብቆ የማንበብ ልማድ ሊኖረው ይገባል፡፡

የቅዱሳን መላእክትን ተአምራት የሚናገሩ ድርሳናትን ስናነብ ከመጀመሪያው አንሥቶ እያንዳንዱ ምዕራፍ የሚያስተላልፈው መልእክት አለ፡፡የመልአኩን የስም ትርጉም፣ነገዱን፣የተሰጠውን የአገልግሎት ጸጋ፣ከብሉያት በሐዲሳት የሠራውን ተአምራት በየተራ እየነገረን ይሔድና ከዚያ በኋላ ከሐዋርያት ዘመን በኋላ እስካለንበት ዘመን ድረስ የተደረጉትን ተአምራት በየተራ ይዘረዝርልናል፡፡ ለቅዱሳን መላእክት የተሰጠን ጸጋ እግዚአብሔር ተረድተን በአማላጅነታቸው ለእኛም ተአምራት እንዲደረግልን እምነታችንን ያጎለምስልናል፡፡
የቅዱሳን አባቶችን ገድል ስናነብ ደግሞ ከቅዱሱ አባት የዘር ሐረግ ጀምሮ ከዚያ የእናትና አባታቸውን የተቀደሰ አኗኗር፣ ቅዱሳት ከመወለዳቸው በፊት የተነገሩ ትንቢታትን እየዘረዘረ ይተርክልናል፡፡ከዚያም ቅዱሳን ሲወለዱ የነበረውን ሁኔታ አስተዳደጋቸውን ካደጉ በኋላ በተጋድሎ መጽናታቸውን በጥሩ ሁኔታ ይተርክልናል፡፡በመጨረሻም ስለተጋድሎአቸው በዘመናቸው ፍጻሜ ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ቃል ኪዳን ሲሰጣቸው ያስነብበናል፡፡ገድላቱን ስናነባቸው የቅዱሳንን የተጋድሎ ሕይወት አስነብበው እኛም ፍኖታቸውን እንድንከተል መንፈሳዊ ቅናት እንዲያድርብን ሲያደርጉ በተጨማሪም የቅዱሳንን ቃል ኪዳን አንብበን ተጠቃሚ ለመሆን ራሳችንን እንድናዘጋጅ ያነሣሡናል፡፡
አንድ ሰው ድርሳናትን ወይም ገድላትን ሲያነብ ከመካከል ከጀመረ ወይም ፍጻሜያቸው ላይ ከተነሣ የቅዱሳት መጻሕፍቱን ሐሳብ ለመረዳት፣ታሪካቸውም ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ለማወቅ ይከብደዋል፡፡ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍትም ሲነበቡ እንዲሁ ተራቸውን ጠብቆ ቢነበቡ መልካም ነው፡፡አንዳንድ ወጣቶች ብዙ መጻሕፍትን እንዳነበቡ እየነገሯችሁ ነገር ግን ያነበቡትን መጽሐፍ ታሪክ ስትጠይቋቸው ሲጀመር አልያ ሲፈጸም ያለውን ብቻ ያስትውሳሉ፡፡ይህ አሟልቶ ባለማንበብ የሚፈጠር ችግር ነው፡፡ሌሎችም ከአራትና አምስት ምዕራፍ በላይ ሳያነቡ ይህን መጽሐፍ አንብቤዋለሁ ሲሉ የሚሰሙበት ጊዜ አለ፡፡ይህ አንባቢ ለመባል ያህል እንጂ መጻሕፍቱን ለማወቅና ለመረዳት አይመስልም፡፡

፪፦ ማስታወሻ መያዝ

ቅዱሳት መጻሕፍት በውስጣቸው የያዙት ምስጢር ተዝቆ የማያልቅ ነው፡፡በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ምስጢር ሁልጊዜም አዲስ ነው፡፡ ስናነባቸው ባጠገባችን ማስታወሻ ይዘን ከሆነ የምናገኘውን ምስጢር እየመዘገብን ለማኖር ይረዳናል፡ ታሪክ ሲሆን የተረዳነውን በአጭሩ ጽፈን ብናኖር፣ምስጢር ሲሆን ደግሞ እንዲገባን አድርገን ማስታወሻ ብንይዝ፣አንብበን ከፈጸምን በኋላ ስለዚያ መጽሐፍ ተመልሰን ለመከለስ ይረዳናል፡፡አንዳንድ ሰው ብዙ መጻሕፍትን እንዳነበበ እየተናገረ ምን እንዳነበበ  ግን በፍጹም የማያስታውስ አለ፡፡ይህ የሚሆነው ማስታወሻ ካለመያዝ ነው፡፡ለጊዜው ደስ ደስ እያለን አንብበን ማስታወሻ ካልያዝን ወዲያውኑ እንዘነገዋለን፡፡ይልቁንም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አዕዋፍ የተባሉ አጋንንት ከልቦናችን እርሻ ላይ ስለሚለቅሙት ፈጥነን ልንዘነጋው እንችላለን /ማቴ፲፫-/፡፡
ማስታወሻ እየያዝን ስናነብ መጻሕፍቱ የሚሉትን ብቻ ለመጻፍ መሞከር አለብን፡፡አሳጥረን የምንጽፈው ታሪክ ሲኖረንም ሐሳቡን እንዳይለቅ መጠንቀቅ አለብን፡፡የራሳችንን ሐሳብ ቀላቅለን ደባልቀን ከጻፍን ያንን እያነበብን ለስሕተት እንዳረጋለን፡፡ስለዚህ እንዳናሳስት ሁልጊዜም ቅዱሳት መጻሕፍት የሚሉትን እርሱን ብቻ ሳንቀንስ ሳንጨምር ለማስፈር መሞከር አለብን፡፡የአበው የአነጋገር ዘይቤ በራሱ የመጻሕፍት ውበት ነው፡፡ይህንን በራሳችን አባባል እንተካው ብለን ለዛውን ምስጢሩን እንዳናጠፋው መጠንቀቀ አለብን፡፡
ወጣቱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጥበቅ እያንዳንዱን ቁም ነገር በማስታወሻ በመከተብ ቢጓዝ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ያበለጽጋል፡፡መሠረታዊ የሆነ መንፈሳዊ ዕውቀት እንዲኖረው የማንበብ ብቻ ሳይሆን በጥሩ መልኩ ማስታወሻ የመያዝና ከመምህራን እየጠየቀ ትርጉሙን የመረዳት ልማድ ሊኖረው ይገባል፡፡የቀደሙ አበው በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሆነው ያዩትን የሰሙትን ባይጽፉልን ኖሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ እድል አይኖረንም ነበር፡፡እነርሱ ጽፈው በማስቀመጣቸው ግን ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ አብረናቸው ያለን ያህል እያንዳንዱን ታሪክ በንባብ እንከታተላለን፡ እንደዚሁ ለትውልድ ባይተርፍ እንኳን ለራሱና እንዲሁም ለቤተሰቡ ለጓደኞቹ እንዲሆን ወጣቱ ማስታወሻ  እየያዘ ማንበብ አለበት፡፡ያነበባቸውን ምክሮች፣ትምህርታዊ ጽሑፎች፣ታሪኮች በማስታወሻ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡

፫፦ ያልተረዱትን መጠየቅ

የንግሥት የህንደኬ ባለሟል /የቃቤት በጅሮወንዷ/ የሚሆን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ከኢየሩሳሌም እጅ ነስቶ ሲመለስ ትንቢተ ኢሳይያስን ያነብ ነበር፡፡መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያው ፊሊጶስን ይኽን ባለ ሠረገላ ተከተለው አለው፡፡ፊሊጶስም ተከተለው፡፡በአጠገቡ በደረሰ ጊዜ ትንቢተ ኢሳይያስን ሲያነብ አገኘው፡፡ሐዋርያው የምታነበውን ታስተዉለዋለህን? ብሎ ጠየቀው፡፡ጃንደረባውም መለሰለት የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል»አለው/ሐዋ -/ ፡፡በቅዱሳት መጻሕፍት ያለን መንፈሳዊ ምስጢር ማንም እንደገዛ ፈቃዱ እንዲተረጉም አልተፈቀደልም ተርጓሚ/ምስጢሩን አብራርቶ የሚያስረዳ መምህር/ከሌለ መረዳት ማወቅ አይቻልም፡፡አበው በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉት በመሆኑ ተርጓሚ ያስፈልገዋል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ ነገር ሲጽፍ ‹‹ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደለትም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ››፪ጴጥ -/ብሏል፡፡ሐዋርያው እንዳለው በመንፈሳዊ ቅኔ የተሞሉ፡፡አላፊያትን መፂያትን በአንድነት የያዙ የፈጣሬን የዘመናት ድንቅ ሥራ የሚተርኩ ቅድሳት መጻሕፍትን ለመረዳት በመጻሕፍት እውቀት የበሰለ መምህር ተርጓሚ አመስጣሪ ያስፈልጋል፡፡
ማርቲን ሉተር ባመጣው ፍልስፍና የተወሰዱ መናፍቃን ሁሉ አንደፈቀደው አንዲያነብ እንዳሰበው እንደተረጉም ያስተምራሉ፡፡ይህ አካሔድ ከጌታችን ከሐዋርያት አስተምህሮ የተለየ ነው፡፡እነርሱ ሁሉን እንዳሻህ ተርጉም የሚሉት በየትኛውም መንገድ ተጉዞ ቢሳሳት ከመንገዱ ቢወጣ ስለማያሳስባቸው ግድ ስለማይላቸው ነው፡፡ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን የቀደመው የአበው ትምህርት ሳይበረዝ ሳይከለስ ለትውልድ እንዲተላለፍ ትሻለች።ልጆቿ መስመሩን ጠብቀው በሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ትሻለች፡፡ስለዚህ ሁልጊዜም በራስ ፈቃድ ከማንበብና ከመተርጎም ይልቅ ከአበው ከመምህራን እንድንጠይቅ ትመክረናለች፡፡
ወጣቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን የማንበብ ልምዱን እያዳበረ ከዚህ ጋር ወደ መምህራን ቀርቦ ያልተረዳውን መጠየቅንም ተግባሩ ማድረግ አለበት፡፡ቅዱስ ጳውሎስ‹‹በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ አደንቃለሁ፡፡እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም የሚያናውጣችሁ የክርስቶስን ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ››/ገላ -/ይለናል፡፡ሐዋርያዉ እንዳለው መጻሕፍትን አጣመው የሚተረጉሙ መናፍቃን ሊገጥሙት ስለሚችሉ ትክክለኛውን ትርጉም መረዳት ወጣቱን ከጥፋት ይጠብቀዋል፡፡ሰለዚህም ከጥሩ ምንጭ እየተቀዳ የሚቀርበውን የአባቶች ትምህርት ለማግኘት መምህራንን መፈለግ ተገቢ ነዉ፡፡
 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።