በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በዓል አደረሳችሁ አያልን ከ ዲ /ን መላኩ አዘዘው ጡመራ መድረክ ሰለበአዓሉ ያገኝነውን ፅሁፍ ከዚህ በታች አስፍረነዋል፡፡
ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በተረዳኢነቱና በአማላጅነቱ በክርስቲያኖች ዘንድ ይወደዳል፡፡ ምክንያቱም ያዘኑትን ለማጽናናት የምሥራች ለመንገር ከእግዚአብሔር ወደ ምእመናን ይላካልና፡፡ ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስል ጌታና አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱሳን ሰማእታት ገድላቸውን እንዲፈጽሙ እሳቱንና ስለቱን ተሳቀው ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ይረዳቸዋል፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የቅዱሳን መላእክትን ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላቸውን በፀሎትና በምሥጋና ታከበራለች፤ በተለይ ታህሣሥ 19 ቀን የሚከበርበት ምክንያት ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሠለሥቱ ደቁቅን ከዕቶነ እሳት ( ከነደደ እሳት ) ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡
በጣዖት ፍቅር እጅግ ከመጠን በላይ ልቡ ተቃጥሎ የነበረው የባቢሎን መሪ ናቡከደነጾር ቁመቱ ስድሳ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቅ ምስል አሰርቶ መኳንንቱን ሰብስቦ ሕዝቡ በሙሉ ለጣኦት እንዲሰግድ አዋጅ አወጀ፡፡ ያ ዘመን ለእግዚአብሔር ወዳጆች የፈተና ዘመን ነበር፡፡ አስመሳዮች ለጣኦት ሰገዱ ተረበረቡ፡፡
እውነተኛው አማኞች ግን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እምነት ንጉሥ የወደደው ጊዜ የወለደው በሚል አስተሳሰብ አይለወጥም፡፡
የነደደ እሳት ውስጥ ገብቶ ከመውጣት ባልተናነሰ መከራ ውስጥ ገብተው በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት ከሞተ ሥጋ ነፍስ ድነው እውነተኛ ምሥክርነታቸውን የሚሰጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በመልአኩ ሥም በፈለቀው ጠበል ተጠምቀው ደዌ የራቀላቸው እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በየዓመቱ በቁልቢና በቅዱስ ገብርኤል ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰበሰበው ምዕመናን ሥዕለቱ የሰመረለት ልመናው የተሰማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ገብርኤል የተሰጠውን ጸጋ ተረድተን የመልአኩን አማላጅነት በመጠቀም ልናከብረው ይገባል፡፡
የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ረድኤት እና በረከት አይለየን - አሜን
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።