Feb 25, 2014

ዐቢይ ጾም ፣ ጾመ ሁዳዴ

በቅዱሳን ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ባሕልና ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመጀመሪያዎቹ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ስለሆነች የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፡፡ እነዚህም ሰባት የጾም ወራት ናቸው፡፡ ከእነዚህም ዓበይት አጽዋማት ዐቢይ ጾምን እንመለከታለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾመው ለአብነት፣ ለማስተማር፣ ለአርአያ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ጾም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ፣ ከሰው የሥጋ ጠባይ የሚመጣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ድል የተነሱበት ነው፡፡ እኛም ይህን እያሰብን በተለያየ መንገድ የሚመጣብንን ፈተና ለማራቅ ከዚህ ታላቅ ጾም በረከት እንድናገኝ እንጾማለን፡፡ ጸልዮ ጸልዩ፣ ጾሞ ጹሙ ብሎናል፡፡ ማቴ.6-16፡፡ ስለዚህም ትእዛዙን ለማክበር እንጾማለን፡፡ የዚህ ታላቅ ጾም ስያሜዎች፡-

  •  ዐቢይ ጾም

የባሕርይ አምላክ በሆነዉ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተ በመሆኑ ዐቢይ ወይም ታላቅ ጾም ይባላል
  •  ጾመ ሁዳዴ

በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለ ርስት የሚያርሱት መሬት ሁዳዴ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እኛም ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰብን የምንጾመው በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡
  • የካሳ ጾም

አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ለውርደት ሞት ለሲዖል ባርነት የበቁት በመብል ምክንያት ነው፡፡ በመብል ምክንያት የሞተውን የሰው ልጅ ጌታችን በፈቃዱ በፈጸመው ጾም ከሰው፤ መንፈሳዊ ረሃብን በረሃቡ ካሰለት፡፡ ስለዚህም የካሳ ጾም ተባለ
  •  የድል ጾም

አርዕስተ ኃጣውእ /ማቴ. 4/ ድል የተነሱበት በመሆኑ የድል ጾም ተብሏል፡፡
  •  የመሸጋገሪያ ጾም

ጌታችን ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል ሊያሸጋግረን የጾመው ጾም በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሏል፡፡
  •  ጾመ አስተምህሮ

ጌታችን የጾመው ለትምህርት ነው፡፡ እርሱ መጾም ያለበት ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ጾም ጾመ አስተምህሮ ይባላል፡፡
  •  የቀድሶተ ገዳም ጾም

ጌታችን ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በመጾም ከከተማ ርቆ ከሰው ተለይቶ በብሕትውና መኖርን ቀድሶ የሰጠበት፣ የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልያስን ገዳማዊነት የባረከበት በመሆኑ የቀድሶተ ገዳም ጾም ተብሏል፡፡
  • የመዘጋጃ ጾም

ሕዝበ እሥራኤል የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም ትንሣኤን ከማክበራችን፣ ሥጋና ደሙን ከመቀበላችን በፊት በጾምና በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበት በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል፡፡ ዓቢይ ጾም ስምንት ሳምንት ማለትም 55 ቀናት አሉት ከእነዚህም ቀናት ውሰጥ ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሐዶች ይገኛሉ አሥራ አምስት ቀናት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ከጥሉላት እንጂ ከእህለ ውኃ ስለማይጾሙ የሙሉ ቀናት ጾም አርባ ቀናት ብቻ ናቸዉ፡፡ በሌላ መልኩ የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል የመጨረሻው ሳምንት ደግሞ ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ሕርቃል 614 . የቢዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበትም ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ ምእመናን «ተዋግተህ አስመልስልን»አሉት፡፡እርሱም «ሐዋርያት ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይኽንን የዕድሜ ልክ ጾም ፈርቼ እንጂ ደስ ይለኛል» ሲል መለሰላቸው፡፡ እነርሱም «የአንድ ሰው ዕድሜ ቢኖር ሰባ ሰማኒያ ዘመን ነው፡፡ እኛ ተካፍለን እንጾምልሃለን» ስላሉት ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነዚያ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡ መታሰቢያም እንዲሆን ይህን የጾም ሳምንት በቀኖና ውስጥ አስገቡት፡፡ ጾሙም ጾመ ሕርቃል ይባላለ፡፡ ታሪኩ የመስቀል ፍቅር የተገለጠበት ታሪክ ነው፡፡ 

በሰላም፣ በፍቅር፣ በትሕትና ጾመን ለበዓለ ትንሣኤው በሰላም እንድንደርስ  ጾመን ለማበርከት እንዲያበቃን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቀን አሜን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።