ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ ቁጥር 2
የዕለተ ሰንበት ክብር
- በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ በዕለተ ሰንበት ከሥራው ሁሉ ዐርፎባታል፡፡ ዘፍ. 2፥3፤ ዘጸ. 20፥8
- በሐዲስ ኪዳን ጌታችን የተፀነሰባት፣ ትንሣኤውን የገለጠባት፣ ለሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የሰጠባት፣ ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣባት . . . ወዘተ በመሆኗ ነው፡፡ በአጠቃላይ ታላላቅ ሥራዎችን የሠራባት በመሆኗ ከሌሎች ቀናት ለይተን እናከብራታለን፡፡
- ሌሎች ቀናት ሲያልፉ ዕለተ ሰንበት ባለማለፏ ለዘላለም ጸንታ በመኖሯ ነው፡፡ ድርሳነ ሰንበት ምዕ. 18፥3-7 በዕለተ ምጽአት ከማያልፉ ነገሮች መካከል ቃሉ፣ ዕለተ ሰንበት፣ የሰው ልጅ ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ የኃጢአት ሥራ ሁሉ ቀን ተለይቶ የሚፈጸመው ዝሙቱ፣ ሴሰኝነቱ፣ መዳራቱ ወዘተ . . . በዚች ቅድስት ዕለት ሆኗል፡፡ ‹‹ይህን ኃጢአት ቅድስት በምትሆን በዕለተ ሰንበት፣ በሰሙነ ሕማማት የሚፈጽም ወዮለት›› ይላል /ፍትሐ ነገሥት/ የባልና የሚስት ሩካቤ ኃጢአት ባይሆንም በማይገባ ወቅት ይልቁንም በዕለተ ሰንበት፣ በሰሙነ ሕማማት፣ ረቡዕ እና ዓርብ ከተፈጸመ ኃጢአት ነው፡፡ ኢሳ. 58፥13-14 ‹‹ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን በሰንበት ብትመልስ የሰንበትም ደስታ እግዚአብሔር የቀደሰው ክቡር ብትለው የገዛ መንገድህን ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል በምድር ከፍታዎችም ላይ አወጣሃለው፡፡ የአባትህን የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ የእግዚኣብሔር አፍ ተናግሮአልና›› ሮሜ. 14፥6 ‹‹ቀንን የሚያከብር ለእግዚአብሔር ብሎ ያከብራል›› በማክበራችን ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ዘላለማዊ ዋጋ ክብር አለና፡፡ ባለ ማክበራችን ደግሞ ቅጣት ጉዳት አለውና ነው፡፡ ሰንበትን በሚገባ እንድናከብር ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።