May 8, 2014

«መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው» /መዝ. ፹፮፥፩/


እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል አደረሳችሁ!!
«መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው» /መዝ. ፹፮፥፩/

የዛሬ 2020 ዓመታት ወደኋላ ዘወር ብለን ስንመለከት ታሪክን የሚለውጥ አንድ ድንቅ ክስተት መፈጸሙን እናገኛለን። ይህም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ነው። ልበ አምላክ የተባለ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው» ያላትም እርሷን ነው። /መዝ. ፹፮፥፩/ የተቀደሱ ተራሮች የተባሉ የእመቤታችን ወላጆችና ቅድመ አያቶች ሲሆኑ እኒህም እነ ኖኅ እና አብርሃም ናቸው። እነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ናቸውና። ኢያቄምና ሐናም ከተቀደሱት ተራሮች መካከል ሲሆኑ የእመቤታችን አባትና እናትም ናቸው። ሁለቱም በተቀደሰ ጋብቻ ጸንተው ቢኖሩም መካን በመሆናቸው ያዝኑ ነበር። ይሁንና በስተእርጅና እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ብፅዓት ገቡ። ብፅዓቱም «ወንድ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ነግዶ አትርፎ ይርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር ጠባቂ አገልጋይ ይሁን እንጂ፣ ሴትም ብንወልድ እንጨት ሰብራ እንጀራ ጋግራ ውሃ ቀድታ ወፍጮ ፈጭታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር ውሃ ቀድታ መሶበ ወርቅ ሰፍታ ትኑር እንጂ» የሚል ነው። እግዚአብሔርም የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትንም የማይነሳ ቸር አምላክ ነውና ብፅዓታቸውን ፈጸመላቸው። በተቀደስ ጋብቻ ንጽሕት ቅድስት ልጅ አገኙ። ይህንንም የልደቷን ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በደስታ ታከብረዋለች።

ስለእመቤታችን ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ?

ወላዲተ አምላክ ናት

«በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፤ ወደ ምንጣፌ አልጋ አልወጣም፤ ለጉንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፣ ለእግዚአብሔር ሥፍራ፣ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስከአገኝ ድረስ» /መዝ. ፻፴፩፥፫-/ ዳዊት ይህን ሲናገር ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት የሚለውን ረስቶ አይደለም። ልበ አምላክ ነውና። /ኢሳ. ፷፥፩/ ነገር ግን የያዕቆብ አምላክ ማደሪያ የእግዚአብሔር ሥፍራ የተባለች እመቤታችን ናት። ወልደ እግዚአብሔር ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን
አድሯልና። ስለዚህም ነው ነቢዩ ኢሳይያስ የእግዚአብሔር ከተማ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል ያለው። /ኢሳ. ፷፥፲፬/ ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። /መዝ. ፻፴፩፥፲፬/
«በውስጧም ሰው ተወለደ» /መዝ. ፹፮፥፭/ ማኅፀኗን ዓለም ያደረገው እግዚአብሔር ሰው ሆነ። «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል» /ኢሳ. ፱፥፮/ የተወለደው ሕፃን ኃያል አምላክ ስለሆነ እናቱም ወላዲተ አምላክ ትባላለች። «… ስለዚህም ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል» /ሉቃ. ፩፥፴፭/ «የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?» /ሉቃ. ፩፥፵፫/ ኪሩቤል መንበሩን ለመሸከም የሚርዱለትን /የሚፈሩትን/ እርሷ ፀንሳዋለች፣ አዝላዋለች፣ ጡቷንም አጥብታዋለችና ከኪሩቤልም የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ አላት አባ ኤፍሬም።

የዘላለም ድንግል ናት

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሀልዮም በገቢርም /በሀሳቧም በሥራዋም/ ድንግል ናት። «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደአለው ወደመቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፤ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፣ ሰውም አይገባበትም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል» /ሕዝ. ፵፬፥፩-/ ምሥራቅ የተባለች እመቤታችን ናት። በርም የተባለ ድንግልናዋ ነው። በተዘጋው በር /በድንግልና/ የገባው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተባለ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። «እኅቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት፣ የተዘጋ ምንጭ የታተመ ፈሳሽ ናት» /መኃ. ፬፥፲፪/ የተቆለፈ ገነት አላት በተከፈተ ገነት ቅዱሳን ጻድቃን ገብተው እንደሚኖሩበት በተቆለፈ ገነት ግን /ድንግልና/ መግባት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ለማጠየቅ የተዘጋም ምንጭ አላት ምንም ብትዘጋም /በድንግልና/ የሕይወት ውኃ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳዋለችና።

ስግደት ይገባታል

«የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ» /ኢሳ. ፷፥፲፬/ «ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኗ ውስጥ ዘለለ» /ሉቃ. ፩፥፵፩/ የእመቤታችን አክስት በማኅፀኗ የነበረው ፅንስ ለእመቤታችን የጸጋ፣ በማኅፀኗ ለነበረው ለጌታችን ደግሞ የአምልኮት ስግደት ሰግዷል። «ነገሥታትም
አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ። እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፣ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፣ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ።» /ኢሳ. ፵፱፥፳፫/

አማላጃችን ናት

«የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ» /መዝ. ፵፬፥፲፪/ «ይማለላሉ» ማለቱ ድንግል ሆይ በፊቱ ሞገስ አግኝተሻልና ከአምላካችን ከአምላክሽ ምሕረትን /ይቅርታን/ ለምኝልን እያሉ ይማፀናሉ ለማለት ነው። «በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ /ሞገስ/ አግኝተሻልና አትፍሪ።» /ሉቃ. ፩፥፴/ እግዚአብሔር ለእመቤታችን ከሰጣት ጸጋዎች መካከል አንዱ በፊቱ ቆማ ማማለድ መሆኑን እንገነዘባለን። ይህንንም ቃል የተናገረው ከእግዚአብሔር የተላከው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው።
«የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም» /ዮሐ. ፪፥፫/ ከዚህ ጥቅስም ወረድ ብሎ ያለውን አባባል መነሻ በማድረግ «ከአንቺ ጋር ምን አለኝ» ብሏታልና አታማልድም አይባልም። ጌታ ይህን የተናገረው አታማልጅም ለማለት ቢሆን ኖሮ የለመነችውን ባላደረገላት ነበር። ቋንቋውም የእናትና የልጅ በመሆኑ ተግባብተውበታል። እንዲህ ማለቱም አንቺ ለምነሽኝ እንዳላደርግልሽ የሚያግደኝ ምን ጠብ አለኝ ለማለት ነው። አነጋገሩም ከእስራኤል ወገን ተወልዷልና የእነርሱን ዘይቤ የተከተለ ነው።
ለምሳሌ «የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝይህንን ቃል የተናገረው ርኩስ መንፈስ /ጋኔን/ ቢሆንም ከአንተ ጋር ምን አለኝ ማለቱ መሳደቡ አይደለም። እንዲህ ብሎ ሰይጣን እግዚአብሔርን አይሳደብምና። ትርጉሙም ወዳዘዝኸኝ እሄዳለሁ ብቻ አታሰቃየኝ ማለቱ ነው። /ማር. ፭፥፯/ «እርሷም ኤልያስን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? … አለችው» /፩ኛ ነገ. ፲፯፥፲፰/ እንዲህ ማለቷ መሳድቧ አልነበረም። ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ ለማለት እንጂ። ልጇን እንዲያድንላት እየፈለገች አትሳደብምና። እንግዲህ ከእነዚህ አባባሎች የምንረዳው የእስራኤላውያን አዎንታዊ ንግግር መሆኑን ነው። ጌታችንም ለእመቤታችን ከዚህ የተለየ አልተናገረም።

የእመቤታችን ክብሯ

መትሕተ ፈጣሪ መልእልተ ፍጡራን /ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ/ ናት። «ለአንቺ የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል» /ኢሳ. ፷፥፲፪/ «በምድር ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚአቸዋለሽ» /መዝ. ፵፬፥፲፮/ ከእነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው እመቤታችንን የማያከብር፣ አማላጅነቷን የማያምን፣ የማይሰግድላትም ከእግዚአብሔር መንግሥት ዕድል ፈንታ ያጣል ማለትን ነው።

ስለነቃፊዎቿ

«ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ» /ኢሳ. ፵፱፥፳፭/ እመቤታችንን የማያከብሩ ሁሉ አማላጅነቷንም የማያምኑ የሚጣሉት ከእርሷ ጋር አይደለም። ይልቁንም ከኃያላን ኃያል ከእግዚአብሔርም ጋር እንጂ።

ምስጋና ይገባታል

«መልአኩም ወደእርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፣ አንቺ ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ አላት።» /ሉቃ. ፩፥፳፰/ «በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት በታላቅ ድምጽም ጮኻ እንዲህ አለች፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።» /ሉቃ. ፩፥፵፩-፵፪/ እንደ ኤልሳቤጥ እመቤታችንን ማመስገን የሚችለው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ብቻ ነው። «እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል።» /ሉቃ. ፩፥፵፱/

እናታችን ናት

«ሰው እናታችን ጽዮን ይላል» /መዝ. ፹፮፥፭/ የሕያዋን ሁሉ እናት ተብላ የተጠራችው ሔዋን በአጠፋችው ጥፋት የሰው ዘር እናታችን ብሎ ለመጥራት የሚደሰትባትን እናት በማግኘቱ እናትነቷን ያመነባት ሁሉ ይናገረዋል። የእርሷ እናትነት ጽድቅን ለተራቡት ምግብ የሚሆነውን ለተጠሙትም መጠጥ የሚሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘች በመሆኗ ከሴቶች ሁሉ የተለየ እናትነት ነው።
እናት ለልጇ ወጥታ ወርዳ የሚበላውን እንድትሰጠው እመቤታችንም የአዳም ተስፋው እስኪሞላለት ድረስ ከመስቀሉ እግር አልተለየችም። እኛም እናትነቷን እስከመጨረሻው ሕቅታ ልናጸና ይገባል። በእናታችን በሔዋን የተነሣ እናቶች ምክንያተ ስሕተት መባላቸው ቀርቶ በእመቤታችን ምክንያት ደግሞ ምክንያተ ድኅነት ሆኑ። የቀደመችው ሔዋን ሞትን ቆርጣ ሰጠችን፣ ዳግማዊቱ ሔዋን እመቤታችን ግን ሕይወትን ወልዳ ሰጠችን፣ በሔዋን የተነሣ ከገነት ተባረርን፣ በድንግል ማርያም የተነሳ ግን ወደ ገነት ተመለስን፣ በሔዋን ስሕተት የሰው ልጅ በመበደሉ መላእክት ገነትን ዘግተው አስወጡን፣ እመቤታችን ጌታችንን ብትወልድ ግን ወደ እኛ መጥተው አብረውን ዘመሩ።
ስለዚህም ነው እመቤታችንን ከጌታ የማዳን ሥራ ነጥለን አናያትም የምንለው። ከቤተልሔም እስከቀራንዮ አብራው ነበረችና።  እመቤታችን የጸጋ እናታችን ናት። ሰዎች ጸጋን ወጥተው ወርድው፣ ነግደው አትርፈው የሚያመጡት ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሚያስፈልገን አውቆ በነጻ የሚሰጠን በረከት ነው። የሥላሴ ልጅነት ጸጋ ነው። እኛ አላመጣነውም ነገር ግን ተሰጠን። መንግሥተ ሰማያት ጸጋ ናት እኛ አልከፈትናትም ከፍቶ ሰጠን እንጂ። ሰው ሆኖ መፈጠር ጸጋ ነው ታግለን አላገኘነውም፤ ተሰጠን እንጂ። ሥጋና ደሙ ጸጋ ነው እኛ አልተጋደልንበትም። ራሱ እንደሚያስፈልገን አውቆ ያለ እርሱም ሕይወት ስለሌለን ሰጠን እንጂ። እመቤታችንም እንዲሁ የተሰጠችን የጸጋ እናታችን ናት። «እነኋት እናትህ» ብሎ በዮሐንስ አማካኝነት ሰጥቶናልና። /ዮሐ. ፲፱፥፳፯/
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የእመቤታችንን ስሟን የምትጠራው በዓላቷን የምትዘክረው እርሷንም የምታከብረው ይህን በመረዳት ነው። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!!

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።