May 28, 2014

ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን


ሙሴ አሮንንና ሖርምን ከተማዋን እንዲጠብቁ አድርጎ ኢያሱን አስከትሎ ወደ ደብረ ሲና ሔደ። ኢያሱን ከተራራው ግርጌ ትቶ ሙሴ ብቻውን ወደ ሲና ወጣ። በሲና ተራራም 40 ቀንና ለሊት ቆየ።
በዚህን ጊዜ እስራኤላዊያን ተስፋ ቆረጡና ማጉረምረም ዠመሩ።ፀሐይ ወጣች ገባች ሙሴ ግን ቀለጠአሉ። አመሌ አመሌ ሲል በደብረ ሲና ያያት እሳት አቃጠለችው እንዴ? ሐመልማሉንስ አላቃጠለች ሙሴን ፈጀችው እንዴ? ይህ ባይሆንም ወደኛ ሲመጣ ባሕረ ኤርትራን ሲሻገር ሰጠመ እንዴ? ብለው አጉረመረሙ
አንገተ ደንዳና የተባሉት እስራኤላዊያን በሬ አላርስ ሲል አንገቱን እንደሚያደነድን አንገታቸውን አደንድነው ካህኑ አሮንን ሙሴ ስለቀረ አምላክም ስለሌለ ጣኦት ስራልን ብለው ጮኹ። አሮን አሮን ግበር ለነ አማልክተ ዘይሐውሩ ቅድሜነ እያሉ ጣኦቱ ይሰራላቸው ዘንድ ካህኑ አሮንን አቻኮሉት አጣደፉትም። ይገርማል! እኛም አንዳንዴ ካህናቱን የማይገባ ሥራ ስሩ እንደምንላቸው ማለት ነው። ካህናቱን መነኮሳትን ጳጳሳትን ባሕታዊያንን ዓለማዊ ስራ ስሩ እንደምንላቸው እስራኤላዊያንም ካህኑን ጣዖት ስራ አሉት።
አሮን ልቡ ተከፈለ። ጣኦቱን ቢሰራ ከፈጣሪ ሊጣላ ባይሰራ እስራኤላዊያን በድንጋይ ሊወግሩት መኾኑን እያሰበ ልቡ ተከፈለ። በመጨረሻም ዘዴ መጣለት። አፍቃሬ ንዋይ ናቸውና ወርቃችሁን አምጡ ብላቸው ይሰስታሉ ብሎ አሰበ። ይኹን እንጂ በልባቸው ያደረው ሰይጣን እጃቸውን ፈቶ ወርቁን በአሮን እግር አስቀመጡ። ካህኑም መሬት ተቆፍሮ ቢቀበር ጣኦት ይኾናል አላቸው በዚያው ጠፍቶ የሚቀር መስሎት። ግና የተቀበረው ወርቅ በግብረ ሰይጣን አንገቱ ወርቅ ደረቱ ብር እግሩ ብረት የኾነ ጥጃ ኾኖ ወጣ።
እስራኤላዊያንም አምላካችን እያሉ መጮኽ ዠመሩ። ቀን ሲደርስ አንባ ይፈርስ እንዲሉ ሙሴ ከሲና ተራራ የሚወርድበት ቀን ደረሰ። ጽላቱን ከእግዚአብሔር ተቀብሎ 40 ቀን ሙሉ ከሲና ተራራ ግርጌ የነበረውን ትዕግስተኛ ኢያሱን አስከትሎ ወደ ሕዝበ እስራኤል መጣ። ነቢዩ ሙሴ ከሲና ተራራ ላይ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዞ ሲወርድ እስራኤላዊያን ጣኦትን ያመልኩ ነበር፤
ሙሴ ከሲና ተራራ መውረዱ .... ጌታችን ከሰማየ ሰማያት የመውረዱ ምሳሌ ነው።    
ታቦቱ ከሙሴ እጅ ወድቆ ጣዖታቱን ሰባበረ ...... ይህም ጌታችን የዲያቢሎስን እራስ እራሱን የመቀጥቀጡ ምሳሌ ነው።
ጌታ ስለ ኃጢአታችን በፈቃዱ ሞቶ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣበክብርም ዐረገይህም ታቦቱ ከእንደገና በእግዚአብሔር ጣት ተጽፎ ለሙሴ የመሰጠቱ ምሳሌ ነው!!!  ዘፀአት ምዕ. 31-34
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ጌታችን የዐረገው ማታ ማታ እየወጣ የሚያድርባት፣ ሐሙስ ሌሊት በይሁዳ በኩል ለአይሁድ ተላልፎ የተሰጠባት፣ ሐዋርያት ስለ ነገረ ምጽአት ጠይቀው ተረዱባት ተራራ ደብረ ዘይት ነው በዚህች ተራራ ላይ ብዙ የወይራ ተክል ስለሚገኝ ተራራው ደብረዘይት ተብሏል።
ጌታችን ከትንሳኤእስከ ዕርገቱ 40 ቀናትለሐዋርያቱ እየተገለጸ ያስተምራቸው ነበር። [ሐዋ. 1:3] ነገር ግን ምን እንዳስተማራቸው አልተጻፈም; በመፅሐፈ ኪዳን ላይ ግን ተፅፏል። ቤተክርስቲያናችን አዋልድ መጽሐፍትን የምትጠቀመው በእንዲህ ሁኔታ ነው ማለት ነው።
ዐርገ የሚለው የግዕዝ ግስ ዐረገ፣ ወጣ በሚሉት የአማርኛ ቃላት የሚፈታ ሲሆን ዕርገት የሚለው ስምም ማረግን፣ መውጣትን፣ አወጣጥን ያመለክታል።/.. ./ አስቀድሞ ክቡር ዳዊት እንደተናገረው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱ እያዩት ወደ ሰማይ ዐርጓል። "ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን" እንዲል መዝ. 465 ጌታችን በእውነት እንዳረገ ይኽም ሊታመን የማይችል እንዳልሆነ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያስረዳል። ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሄደ፡ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፤ሥጋው አልተለወጠምና። /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐ.አፈ.ክፍል 13 ቁጥር 15/

አንቃዕድዎተ ዐይን

ወዘንተ እንዘ ይብሎሙ ተለዐለ ወነሥአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ እንዘ እሙንቱ ይኔጽሩ ኀቤሁ ወተሠወረ እምአዕይንቲሆሙ። የሐዋ. 19 አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ የወጣው በርህቀት(በመራቅ) እንጂ በርቀት (-ጠብቆ ይነበብ፤ ረቂቅ በመሆን) አይደለም።ይኽም ማለት አስቀድሞ የተዋሐደውን ሥጋ አርቅቆ፣ ግዙፍነቱን አጥፍቶ ሳይሆን ከመለኮቱ ጋር በተዋሕዶ አንድ የሆነው ግዙፍ ሥጋ ግዝፈቱን ሳይለቅ ከዐይን በመራቅ፣ ከፍ ከፍ በማለት፣ ወደ ሰማይ በመውጣት ነው።
በትምህርቱ የተጽናኑ፣ በተአምራቱ የተማረኩ፣ ትዳራቸውን፣ ወላጆቻቸውን፣ ሃብታቸውን፣  ሥልጣናቸውን፣የተዉለት ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር አብሮአቸው የቆየ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ሲለያቸው በናፍቆት ተይዘው ወደ ሰማይ ሲወጣ ትኩር ብለው ተመለከቱት። ያሳያቸውን ፍቅር፣ ሑሩ ወመሃሩ በማለት ያዘዛቸውን አገልግሎት እንዴት እንደሚወጡት እያሰቡ ትኩር ብለው ተመለከቱት።

ነቢር በየማነ አብ

ነቢር በየማን (በቀኝ መቀመጥ) በመጽሐፍ ቅዱስ አገባብ መሠረት ዕሪናን (በሥልጣን አንድ መሆንን) ያመለክታል። በመለኮቱ የእግዚአብሔር አብ ልጅ፣ በትስብእቱ (ሥጋን በመዋሐዱ) የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአብ ቀኝ ተቀመጠ። ማር.1619
ይኽ ስለ መለኮት የተነገረ አይደለም፤ በመለኮቱስ ከአብ ሥልጣን ዝቅ ያለበት የዐይን ጥቅሻ ያህል ጊዜ የለምና። ነገር ግን ከተዋሕዶ በፊት ደካማ፣ በደለኛ እና ውርደት ይስማማው የነበረው የእኛ ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ ጸጋን የሚያድል፣ እውነተኛ ፍርድን የሚያደርግ፣ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን ያለው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ለመግለጽ ነው።

ዕርገተ ልቡና

ሲጸልዩም ሆነ ሲናገሩ፣ ሲጾሙም ሆነ ሲመገቡ፣ ሲሠሩም ሆነ ሲያርፉ የአምላክዎን ውለታ በማሰብ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ለምን ያህል ደቂቃዎች ያርጋሉ(ይመሰጣሉ)? ሐዋርያት ጌታችን በአካለ ሥጋ አብሮአቸው እያለ ያዘዛቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ በመታመን አደራቸውን እንደተገበሩ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ያለን ምዕመናንም ጌታችን በበረት በመወለድ፣ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ የሰጠንን የትሕትናን አደራ፤ወደ ግብፅ በመሰደድ፣ በመስቀል በመቸንከር ያሳየንን መከራን የመቀበል አደራ፤ አልአዛርን ከሙታን በማንሣት፣ ራሱም በገዛ ሥልጣኑ ከሙታን በመነሣት የነገረንን ትንሣኤ ዘጉባኤን ተስፋ የማድረግ አደራ በሐሳባችን እያረግን ልባችንን ከፍ ከፍ እያደረግን ክርስቲያናዊ ምግባራትን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረን በመያዝ ልንጠብቀው ይገባል።
በዕርገቱ ዕርገተ ልቡናን ያድለን።

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።