ምንጭ፦ መምህር ደምለው ይነሱ
(በኖርዌይ የቅዱስ ገብርኤል እና የአቡነ ተክለሃማኖት ቤተ ክርስቲያን)
“ነቢያት ሰበክዎ ሰማዕተ ኮንዎ ፈኑ እዴከ ለወላዲ ይብልዎ” (ድጓ ዘአስተምህሮ ገጽ ፻፷ /፻፷/) ነቢያት ሰበኩት፤ ምስክርም ሆኑት፤ የባህርይ አባቱን አብንም ቀኝ እጅህን ላክልን አሉት።
ይህ የያዝነው ጾም ጾመ ነቢያት ይባላል።በዚህ ጾም ነቢያት ስለ ክርስቶስ መምጣት የተናገሩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባኤ እናስብበታለን። ጾሙ ሁልጊዜ በህዳር አጋማሽ ተጀምሮ ከልደት
በዓል አንድ ቀን በፊት ያልቃል። ጾመ ነቢያትን የምናስታውሰው እግዚአብሔር አምላክ በልዩ ጥበቡ ሰውን በአርአያውና በምሳሌው ፈጥሮ በተድላ በደስታ ፈጣሪውን እያመሰገነ በገነት እንዲኖር ወስኖ የእግዚአብሔር ፈጣሪነቱ የሰውም ታዛዥነቱ ይለይበት ዘንድ በገነት ካሉ የሚበሉ እፀዋት መካከል ዕፀ በለስን እንዳይበላ ፤ቢበላ ሞትን እንደሚሞት (ዘፍ.፫፡፪-፬፣፲፩-፲፪) አስረድቶ ነጻ ፈቃዱን ሳይጋፋ ምርጫን ሰጥቶ ትዕዛዝን ሠራለት። ነግር ግን የሰው ልጅ በመሠሪ ምክረ ሰይጣን ተታልሎ አታድርግ የተባለውን ዕፀ በለስ በላና ከገነት ተባረረ (ዘፍ.፫፡፳፫-፳፬)፤ የሞት ሞትንም ሞተ።እግዚአብሔር አምላክ የእጁ ሥራ ሲጠፋ አይጬክንምና ለወደቀው የሰው ልጅ “እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ” አድንህ ዘንድ ከልጅ ልጅህ ሰው ሆኜ እወለዳለሁ እንደ ሰው ሕግም ቀስ በቀስ አድጋለሁ፤ እንደ ሕጻናት ጡትን እጠባለሁ፣ አድሃለሁም ሲል የተስፋ ቃልን ሰጥቶት ነበር።
- ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል፤ በውስጥዋም ሰው ተወለደ፤ እርሱም ራሱ መሠረታት (መዝ.86፡5
- እግዚአብሔር ከቴማን፣ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል (ትን.እንባቆም 3፡3)
- አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል (ትን.ሚክያስ 5፡2-3)
- ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ህፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል (ትን. ኢሳይያስ 7፡14-16)።
በቤተ ክርስቲያናችን የምሥጢር መፈልፈያ ወይም መፍለቂያ በሆነው ቅኔ ትምህርት ቤት ነቢያት እና አበው ስለ ወልድ እና ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምሳሌ የተገለጠላቸውን ወይም የተናገሩትን በመውሰድ ደቀ መዛሙርት ቅኔ ይቆጥሩበታል፤ምሥጢር ይፈለፍሉበታል። በተለይም ነቢያት ምልክትን ሲያደርጉ ወይም ወደ እግዚአብሔር ልመናን አቅርበው በእውን ወይም በራዕይ አለዚያም በህልም የጸሎታቸውን ወይም የልመናቸውን ውጤት ያዩበት ለእመቤታችንና ለጌታ በምሳሌነት ይመሣጠራል። በቀጣዩ ሠንጠረዥ እመቤታችንና ጌታ ከተመሰሉባቸው ምሳሌዎች ጥቂቶችን ይመለከቷል።
እመቤታችን
|
ጌታ
|
ደመና [ኤልያስ በሰው እጅ አምሳል ያያት]
|
ዝናም
|
መሶብ [ኤልያስን መልአኩ የመገበባት]
|
መና
|
ፀምር/የበግ ጠጉር ባዘቶ/ [ጌዴዎን በምልክትነት ያያት]
|
ጠል
|
ዕፀ ጳጦስ ዘሲና [ሙሴ በደብረ ሲና ያያት]
|
ነበልባል/እሳት
|
ቀርነ ቅብዕ /የዘይት ቀንድ [ሳሙኤል ዳዊትን ለንጉሥነት በቀባ ጊዜ ዘይቱን የያዘባት]
|
ቅብዐ መንግሥት
|
መሰንቆ/በገና [ዳዊት በሳዖል ፊት የዘመረባት]
|
የበገናው ድምፀ ቃና
|
ማሰሮ [ኤልሳእ የኢያሪኮን መራራ ውሃ ያጠፈጠባት]
|
ጨው
|
በትር [በቤተ መቅደስ ለምልማ አብባ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር]
|
ጽጌ/አበባ/ልምላሜ፣ ፍሬ
|
ኆኅተ ምሥራቅ [ሕዝቅኤል በምሥራቅ ያያት የተዘጋች በር/ደጃፍ]
|
ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት የወጣው
|
በእንዲህ ዓይነት መንገድ ነበር
የጌታ መወለድ ለነቢያት የታያቸው። ይህን ዓይነት የምሥጢር ፍስሰት ተከተለው ነው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት በዚህ በጾመ ነቢያት ጊዜ ቅኔውን እንደ ውሃ የሚያፈስሱት እንደ ጠጅ የሚያንቆረቁሩት።
ጾመ ነቢያት ሲነሳ ከጾሙ አጋማሽ በኋላ ከልደት በፊት ስለሚገኙት ተከታታይ ሶስት እሁዶች ስያሜ ማንሳት ተገቢ ይሆናል።ብሉይን ከሐዲስ
Aስተባብራና በምሥጢር አራቅቃ ስትጓዝ
የምትኖር ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በደረሰው ድርሰት ተመርኩዛ ስለ ወልድ ሰው ለመሆን ወደዚህ
ዓለም
መምጣት በጾመ ነቢያት ጊዜ ፈጣሪዋን የምታመሰግንበት ሶስት ሳምንታትን ሰይማለች። እነዚህም ስብከት፣ ብርሃንና ኖላዊ በመባል ይታወቃሉ። ሶስቱም የሚጀምሩት ከእሁድ ሆኖ እያንዳንዳቸው ከጀመሩበት እሁድ እስከ ቀጣዩ እሁድ ቅዱስ ያሬድ በደረሰው የቃል ትምህርትም ይሁን በድጓው የተመደበላቸው ቀለም ሲባል ይሰነብታል። ሶስቱም በዓላት በሚባለው የቤተ ክርስቲያን ቀለም እንጅ የተለየ ሥርዓት የላቸውም።በሶስቱም እሁዶች ሥርዓተ ማኅሌት ይደርሳል። በስብከት እና በኖላዊ ትምህርተ ኅቡዓት የሚደረስ (በዜማ የሚባል) ሲሆን በብርሃን ግን መልክዓ ኢየሱስ ይደረሳል (በዜማ ይባላል)።
፩.ስብከት
ስብከት የሚል ስያሜ የተሰጠው “ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ” ዓለም ሳይፈጠር የነበረ አዳኝ የሆነ የአብ የባህርይ ልጁን እንሰብካለን ሲል ቅዱስ ያሪድ በድጓው
በደረሰው መዝሙር ካህናቱ ይጀምሩና ‘ነቢያት ሰበክዎ’
፤ ‘ኪያሁ ንሰብክ’ የሚሉ ቃላትንና
ሐረጎችን የሚያነሱ ቀለሞችን በዝማሬአቸው ስለሚያካትቱ ነው ።
ስብከት ከታህሣሥ ሰባት እስከ ታህሣሥ ዓሥራ ሶስት ሊወጣ ሊወርድ ይችላል። ከታህሣሥ ሰባት ወደታች አይወርድም ከታህሣሥ ዓሥራ ሶስትም ወደላይ አይወጣም። የስብከት እሁድ መጀመሪያ በታህሣሥ ወር መባቻ ወይም ኤልያስ (ታህሣሥ ፩) በሚውልበት የሳምንቱ ቀኖች ይወሰናል። ኤልያስ ሰኞ ቢውል ተከታዩ እሁድ ታህሣሥ ፯ ስለሚሆን ስብከት ታህሣሥ ፯ ይሆናል ማለት ነው። እስኪ በሠንጠረዥ መልክ እንየው።
ኤልያስ የሚውልበት የሳምንቱ ቀን
|
ስብከት የሚውልበት
|
ሰኞ
|
ታህሣሥ ፯
|
እሁድ
|
ታህሣሥ ፰
|
ቅዳሜ
|
ታህሣሥ ፱
|
ዓርብ
|
ታህሣሥ ፲
|
ሐሙስ
|
ታህሣሥ ፲፩
|
ረቡዕ
|
ታህሣሥ ፲፪
|
ማክሰኞ
|
ታህሣሥ ፲፫
|
፪.ብርሃን
ከስብከት ሳምንት በኋላ ተከታዩ እሁድ ብርሃን ይባላል።ብርሃን መባሉ “አቅዲሙ ነገረ በOሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ዘይዜንዋ ለጽዮን ቃለ ትፍሥሕት..... ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም”
ለጽዮን የምሥራች ቃልን የሚያበሥር ወልድ በምስጋና ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ አስቀድሞ በOሪት ተናገረ፤ እርሱም ወደ ዓለም የመጣ ብርሃን ነው እያለ ቅዱስ ያሬድ የደረሰውን ዜማ ካህናቱ ይዘምሩታል ። ለብርሃን በተመደበው እሁድ የቅዳሴ ምስባክም ከመዝሙረ ዳዊት “ፈኑ ብርሃነክ ወጽድቀከ፤ እማንቱ ይምርሃኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ፤ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ” ብርሃንህን እና እውነትህን ላክ፤እነርሱ ይምሩኝ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ፤ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ ( መዝ.42፡3-4) የሚለው ይሰበካል።ባጠቃላይ በሞት ጥላ ሥር ተውጦ በኃጢAት ተለውሶ በጨለማ ተጋርዶ የነበረ ዓለም በወልድ ሰው መሆን የድኅነት ብርሃን ፈነጠቀለት የሚል መልእክት ይተላለፍበታል።
፫.ኖላዊ
ኖላዊ ማለት ኖለወ ጠበቀ ከሚል ግሥ የወጣ ግብር ቅጽል ነው ። ስለዚህ ኖላዊ ማለት ጠባቂ እረኛ ማለት ነው።በኖላዊ እሁድና እስከ ዓርብ ባሉት ተከታዮቹ ቀናት ወልድ መድኅን ሊሆን ተበትኖ የነበረ የሰው ልጅን ሊሰብስብ ወደዚህ ዓለም መምጣቱን፤ የማያንቀላፋ ትጉህ እረኛነቱን የሚያነሱ ምንባባት ይነበባሉ፤ መዝሙራት ይዘመራሉ። ቅዱስ ያሬድ “ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃሉ ለእግዚአብሔር” የእግዚአብሔር አብ ልጁ ቃሉ እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣ ቸር ጠባቂ ነው ሲል በመዝሙሩ የደረሰውን ካህናቱ በቁም ዜማ፣በዝማሜ ፣በጸናጽል፣ በከበሮ ይዘምሩታል። ቀሳውስቱም በቅዳሴ ጊዜ ከመዝሙረ ዳዊት በሚሰበከው ምስባክ “ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አፅምእ፤ዘይርእዮሙ ከመ አባግዓ ዮሴፍ፤ ዘይነብር ላእለ ኪሩቤል አስተርአየ” ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ (መዝ.፸፱፡፩-፪) እያሉ ያዜማሉ፤ ለእለቱ የተመረጡ የእግዚአብሔርን ጠባቂነት/ኖላዊነት/ ከሚያንጸባርቁ ምንባባትም በተለይም መድኃኒታችን ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ ፲ ላይ ስለ በጎች እረኝነት ‘አንቀጸ አባግዕ’ ያስተማረው ትምህርት ለዚህ እለት ጎልቶ በትምህርትነት ይቀርባል።
ለነቢያት የሩቁን እንዲናገሩ ሀብተ ትንቢትን ያደለ፤ ምሳሌውን እና ምሥጢሩን የገለጠ፤ እስከ መጨረሻው በተስፋ እንዲጸኑ ጥንካሬን የለገሠ አምላክ ለእኛም ምሥጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን፤ሰላምን ፍቅርን በመካከላችን ያስፍን፤ በዚህ በያዝነው ጾም እንድንጠቀም በሰላም እንዳስጀመረን በሰላም ያስፈጽመን፤ ለብርሃነ ልደቱ ያድርሰን።
ለነቢያት የሩቁን እንዲናገሩ ሀብተ ትንቢትን ያደለ፤ ምሳሌውን እና ምሥጢሩን የገለጠ፤ እስከ መጨረሻው በተስፋ እንዲጸኑ ጥንካሬን የለገሠ አምላክ ለእኛም ምሥጢሩን ጥበቡን ይግለጽልን፤ሰላምን ፍቅርን በመካከላችን ያስፍን፤ በዚህ በያዝነው ጾም እንድንጠቀም በሰላም እንዳስጀመረን በሰላም ያስፈጽመን፤ ለብርሃነ ልደቱ ያድርሰን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።