Sep 28, 2016

መስቀሉ የት ነው ያለው? ክፍል ፪


ከዳንኤል ክብረት

መስቀሉ እንዴት ጠፋ?

የሀገራችን ሊቃውንት እና መዛግብት መስቀሉ እንዴት እንደ ጠፋ የሚተርኩት ታሪክ የጥንታውያኑን መዛግብት የተከተለ ነው፡፡ በመስከረም 16 እና 17 የሚነበበው ስንክሳራችን የጌታችን መስቀል በጎልጎታ በጌታችን መቃብር እንደነበረ ይተርክልናል፡፡ አይሁድ በመስቀሉ እና በመቃብሩ የሚደረገውን ተአምር አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውንም ያትታል፡፡ እስከ 64 ዓም አይሁድ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው ኃይል አልነበራቸውም፡፡ 64 ዓም አካባቢ ግን አይሁድ ራሳቸውን ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ዐመጽ ጀመሩ፡፡ ኢየሩሳሌምም በአይሁድ ቁጥጥር ሥር ዋለች፡፡
አይሁድ መስቀሉን፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን እና የጌታችንን መቃብር የተቆጣጠሩት እና ክርስቲያኖች እንዳይገቡ ያገዱት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ጎልጎታ የከተማዋ ጥራጊ እንዲደፋበት አዘዙ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም እና በአካባቢዋ አብያተ ክርስቲያናት አልነበሩም፡፡ ክርስቲያኖች ግን በጌታችን መቃብር አካባቢ ዋሻዎችን ፈልፍለው ይገለገሉባቸው ነበር፡፡
ዛሬ በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም ክልል የሚገኘው ጎልጎታ በዚያ ዘመን ከከተማዋ ውጭ ነበር፡፡ ጌታንም የሰቀሉት ከከተማ አውጥተው ነው፡፡ አይሁድ የከተማ ጥራጊ መድፊያ እንዲሆን የፈለጉትም ቦታው ከከተማ የወጣ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር ነው፡፡ ይህ ታሪክ በስንክሳራችን ከተጻፈው ታሪክ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

መስቀሉ የት ተቀበረ?

አንዳንድ አካላት የሚተርኩት ታሪክ በስንክሳራችንም ሆነ በጥንታውያን መዛግብት ከተገለጠው የተለየ ነው፡፡ በመስከረም 17 እና በመጋቢት 10 የሚነበበው ስንክሳራችን መስቀሉ የተቀበረው በዚያው በጎልጎታ እንደሆነ ይተርካል፡፡ «የጎልጎታን ኮረብታ ባስጠረገች ጊዜ የከበረ መስቀልን አገኘችው» ይላል፡፡ አንዳንድ አካላት ግን መስቀሉን አይሁድ በሌላ ቦታ ጉድጓድ ቆፍረው እንደቀበሩት ይገልጣሉ፡፡
በስንክሳራችን የተገለጠው እና መስቀሉ የተቀበረው በጎልጎታ ነው የሚለው ታሪክ በሦስተኛው እና 4ኛው መክዘ ከነበሩት የታሪክ ጸሐፊዎች ገለጻ ጋር አንድ ነው፡፡ 380 ዓም አካባቢ የተወለደው ታሪክ ጸሐፊው ሶዜማን መስቀሉ የተገኘው ከጎልጎታ መሆኑን መዝግቦ አቆይቶናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መስቀሉ በጎልጎታ ተቀብሮ ነበር የሚለው የስንክሳራችን ትረካ ከግብጽ፣ ከሶርያ እና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ስንክሳር ትረካ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃም እሌኒ ንግሥት መስቀሉን ቆፍራ ያወጣችበት እና በኋላም የመስቀሉን ቤተ ክርስቲያን የሠራችበት ቦታ የሚገኘው በዚያው በጎልጎታ፣ ያውም ከኢትዮጵያ የዴር ሡልጣን ገዳም ሥር ነው፡፡ በመሆኑም መስቀሉን አይሁድ በሌላ ቦታ ቀበሩት የሚለው ሃሳብ የሚያስኬድ አይመስልም፡፡

መስቀሉ እንዴት ተገኘ?

መስቀሉ እንዴት እንደ ተገኘ በቤተ ክርስቲያናችን የሚገለጠው ታሪክ ከሌሎች ጥንታውያን መዛግብት ታሪክ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ መስቀሉን ያወጣችው የቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ መሆንዋን ሁሉም ይስማሙበታል፡፡ እሌኒ ንግሥት ወደ ኢየሩሳሌም ስትገባ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ ለዚህም ሦስት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የመጀመርያው በኢየሩሳሌም 132 እስከ 135 በተደረገው እና ከተማዋ ፈጽማ በጠፋችበት ጦርነት ምክንያት ክርስቲያኖች ከከተማዋ ርቀው መኖራቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አይሁድ መስቀሉን በጎልጎታ ከቀበሩ በኋላ መጀመርያ ጥራጊ መድፋታቸው ሲሆን ሦስተኛው ንጉሥ ሐድርያን 135 ዓም የኢየሩሳሌምን ገጽታ የቀየረውን አዲስ ፕላን በማውጣት ከተማዋን እንደገና መሥራቱ፤ በጎልጎታም ላይ የቬነስን መቅደስ መገንባቱ ነው፡፡ የቬነስ መቅደስ መገንባት ክርስቲያኖች ወደ አካባቢው ፍጹም እንዳይቀርቡ አስከላከላቸው፡፡
ንግሥት እሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ገብታ ያደረገችውን ስንክሳራቸውን እንዲህ ይተርከዋል «እርሷ በመጣች ጊዜ የጌታችን የክርስቶስን መቃብር እስካሳዩዋት ድረስ አይሁድን ይዛ አሰቃየቻቸው፤ ያንን ኮረብታም እስከ ጠረጉ ድረስ አስገደደቻቸው፤ የከበረ መስቀሉም ከተቀበረበት ተገልጦ ወጣ» ይላል፡፡ በሌላም በኩል የመጋቢት 10 ቀኑ ስንክሳር ታሪኩን ያውቃል የተባለውን አንድን አይሁዳዊ አሥራ በማስጨነቅ ምሥጢሩን እንዳውጣጣችው ይገልጣል፡፡ ይህ አገላለጥ ከጥንታውያን መዛግብት አገላለጥ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ዞሴማን አልተቀበልኩትም ቢልም አንድ አይሁዳዊ ሽማግሌ ለንግሥት እሌኒ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ እንዳሳያት የሚተርከው ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን ኪርያኮስ የተባለ አረጋዊ ነገራት እየተባለ ከሚተረከው ጋር ተመሳይ ነው፡፡ በወቅቱ ይህ አይሁዳዊ ስለ ዕጣንም ሆነ ጸሎት ሊናገር የሚችል አይመስልም፡፡ ይህ ሃሳብ ምናልባት በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የአቡነ መቃርዮስ ይሆናል፡፡
እስካሁን እኔ በሌሎች መዛግብትም ሆነ በስንክሳራችን ላይ ያላገኘሁት «ደመራ ተደምሮ ጢሱ አመለከተ» የሚለውን ታሪክ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ጢሱ ለመስቀሉ መስገዱን ይገልጣል፡፡ እሌኒ ንግሥት ክርስቲያናዊት እናት እንደ መሆንዋ መጠን አይሁድ የሰጧትን መረጃ ብቻ ተቀብላ ቁፋሮ አታስጀምርም፡፡ በአይሁድ የተነገረው በጸሎት እንዲረጋገጥ አድርጋለች፡፡ ያን ጊዜ ጸሎት ተደርጎ ዕጣን ሲታጠን ጢሱ ወደ ጎልጎታ አመለከተ፡፡ ይህንን በተመለከተ መዛግብትን ማገላበጥ ይቀረናል፡፡

በዓለ መስቀል እንዴት ተወሰነ?

በኢትዮጵያም ሆነ በግብጽ ያሉ ስንክሳሮች ላይ መስቀሉ የተገኘው መስከረም 17 ቀን መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ ቁፋሮው መቼ እንደተጀመረ በትግጠኛነት የሚገልጥ መረጃ አላገኘሁም፡፡ የኛ ሊቃውንት ቁፋሮው መስከረም 17 ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን መጠናቀቁን ይገልጣሉ፡፡ በወቅቱ ከነበረው ቴክኖሎጂ አንፃር ሊወስድ ይችላል፡፡ መጋቢት 10 ቀን ግን ራሱን የቻለ ታሪክ አለው፡፡ መስቀሉ በፋርሶች ከተማረከበት በንጉሥ ሕርቃል ተመልሶ ወደ ጎልጎታ የገበባበት ቀን ነው፡፡
የቀድሞ አባቶች ታክን ከታሪክ ማገናኘት ልማዳቸው ነውና መስቀሉ መጋቢት 10 ቀን ወደ ጎልጎታ እንዲገባ ያደረጉት ቀድሞ ከተገኘባት ቀን ጋር ለማስተሣሠር ሊሆን ይችላል፡፡ በስንክሳራችን መስከረም 16 ቀን በኢየሩሳሌም እና በአካባቢው በንግሥት እሌኒ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት በመስቀሉ የተባረኩበት ቀን መሆኑን ይነግረናል፡፡ መስከረም 17 ቀን ደግሞ ቅድስት እሌኒ መስቀሉ በተገኘበት በጎልጎታ ያሠራችው የመስቀሉ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ነው፡፡ ነገር ግን በዐቢይ ጾም በዓል ስለማይከበር የመስቀሉ በዓል ቅዳሴ ቤቱ በተከበረበት ቀን በመስከረም 17 እንዲከበር ሊቃውንት ሥርዓት መሥራታቸውን ስንክሳሩ ይነግረናል፡፡

እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ገባ?

ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደገባ ሁለት ዓይነት ታሪኮች አሉ፡፡ አንዱ ከግብጽ ሁለተኛው ከኢየሩሳሌም፡፡ ለመስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት የሆነው በዐፄ ሠይፈ አርእድ ተፈጥሮ የነበረ ችግር ነው፡፡ በዚህ ዘመን የግብጽ ሡልጣኖች በግብር እያመካኙ የግብጽ ክርስቲያኖችን ባሰቃዩዋቸው ጊዜ ንጉሥ ሠይፈ አርእድ እስከ ደቡብ ግብጽ እየዘመተ ወግቷቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ የንግድ መሥመሩን ከለከለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ እና ከኑቢያ የሚሄደው ዕቃ ተቋረጠ፡፡
ሁኔታው ከሥጋት ላይ የጣላቸው የግብጽ ሡልጣኖች በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ የጣሉትን ቀንበር አላሉ፡፡ የግብጹ ጳጳስ እና ሡልጣኑ ተስማምተው ወደ ኢትዮጵያ መልክተኛ ላኩ፡፡ በጉዳዩም በኢየሩሳሌም የነበሩት ፓትርያርክ ዮሐንስ ገቡበት፡፡ አቡነ ዮሐንስ የመልክተኞቹ መሪ ሆነው መጡ፡፡ በጊዜው በዙፋኑ ላይ የነበረው ዐፄ ዳዊት ስለነበረ እርሱም ንግዱን ላይዘጋ ሡልጣናቱም ክርስቲያኖቹን ላያጉላሉ ተስማሙ፡፡ ለስምምነቱ ማሠርያ ይሆን ዘንድም ከጌታ ግማደ መስቀል እንዲመጣለት ንጉሥ ዳዊት ጠየቀ፡፡ ሡልጣኑም ተስማማ፡፡
1387 ዓም ግማደ መስቀሉን የሚያመጡ ሊቃውንት ወደ ካይሮ ተላኩ፡፡ መልክተኞቹ ለሡልጣኑ የሚሰጥ 20 ግመል የተጫነ ስጦታ ይዘው ነበር፡፡ ዐፄ ዳዊት አስቀድሞ ሃሳቡን ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ለአቡነ ዮሐንስ ነግሯቸው ስለነበር እርሳቸው ሉቃስ የሳላትን ሥዕል፣ ኩርአተ ርእሱ የተባለውን የጌታ ሥዕል እና ግማደ መስቀሉን ላኩለት፡፡ ግማደ መስቀሉ መስከረም 16 ቀን ተጉለት ገብቶ ንጉሡ ባሳነፁት ቤተ ክርስቲያን የቀመጠ፡፡ /ተክለ ጻድቅ መኩርያ፣ ከይኩኖ አምላክ እስከ ልብነ ድንግል፣ ገጽ 116-118/
በሌላ በኩል ደግሞ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ለመቀበል ዐፄ ዳዊት ወደ ስናር ወርደው ነበር፡፡ በዚያም ባዝራ ፈረስ ጥላ ስለረገጠቻቸው ሞቱ፡፡ ግማደ መስቀሉም በስናር ቆየ የሚል ታሪክም አለ፡፡ ይህንን ታሪክ ለመቀበል የሚከብደው በወቅቱ ሱዳን በዐረቦች መወረሯን፤ስናርም ለግዛታቸው ቅርብ የነበረ መሆኑን ስናስበው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ከዐፄ ዳዊት እስከ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ሠላሳ ዓመታት በዚያ ተቀመጣ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምናልባትም የተክለ ጻድቅ መኩርያ ትረካ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ በሌላም በኩል ግማደ መስቀሉ ከኢየሩሳሌም መጣ የሚለው ታሪክ በወቅቱ ኢየሩሳሌም ከነበረችበት ሁኔታ አንፃር ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም 1187 ዓም ሳላሕ ዲን ኢየሩሳሌምን ከያዛት በኋላ መስቀሉ ከአካባቢው ተሠውሯል፡፡ የሮም ነገሥታትም እርሱን ለማግኘት ተደራድረው አልተሳካላቸውም፡፡ የመስቀል ጦረኞችም ቢሆኑ ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ሌሎችን ንዋያት አመጡ እንጂ መስቀሉን አላገኙትም፡፡
እንደ እኔ ግምት ግማደ መስቀሉን ያገኘነው ከእስክንድርያ መሆን አለበት፡፡ ንግሥት እሌኒ የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናትን ሠርታ ስታጠናቅቅ የቁስጥንጥንያ፣ የአንፆኪያ እና የእስክንድርያ አባቶች ካህናትን ልከዋል፡፡ ግማደ መስቀሉ ወደ እስክንድርያ የገባው በዚያ ዘመን ሳይሆን አይቀርም፡፡ በኋላም ዐፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ሲጠይቅ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ላደረገው ውለታ ልከውለት ይሆናል፡፡ በሌላም መልኩ ሡልጣኑም ግፊት ማድረጉ አይቀርም፡፡ አያሌው ተሰማ የተባሉ ምሁር «ታሪክ ነው ገበያ፣ የሁሉ መዋያ» በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ዐፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ያገኘው ዓባይን ገድቦ ግብፆችን በማስጨነቅ ነው ይላሉ፡፡ ሁኔታው ያሰጋቸው የግብጽ ባለ ሥልጣናት ለላኳቸው መልክተኞች ግማደ መስቀሉን እንዲሰጧቸው በመጠየቃቸው ሡልጣናቱ ግብፃውያኑን አባቶች ተጭነው እንዳሰጧቸው ይተርካሉ፡፡

ደመራ

የደመራ በዓል መላዋን ኢትዮጵያ ከሚያስተሣሥሩት በዓላት አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት የደመራ በዓል መነሻ ንግሥት እሌኒ ናት ይላሉ፡፡ ነገር ግን ስለ ንግሥት እሌኒ በተጻፉት ጥንታውያን መዛግብት ሁሉ ይህንን የሚደግፍ ነገር አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናት ቅዳሴ ቤት ሲከበር አበው ሊቃነ ጳጳሳት መስቀሉን ይዘው ችቦ አብርተው እየዞሩ መባረካቸውን የሚገልጡ መዛግብት አሉ፡፡
ኢትዮጵያውያንም ይህንን በመያዝ የመስቀልን በዓል በደመራ በዓል ማክበር ጀምረዋል፡፡ ደመራ የአባቶቻችን የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ እንጂ ከውጭ አልመጣም፡፡ የጌታችንን ጥምቀት በዓል ታቦቱን በበዓለ ከተራ ይዞ በመውረድ እና በበዓሉ እንዲመለስ ሥርዓት እንደሠሩት ማለት ነው፡፡ የደመራ ሥርዓት ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ በተመሳሳይ ሰሞን እና ሥርዓት ይከበራል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ወርቃማው የክርስትና ዘመን የሚባለው ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን እስከ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ያለው ዘመን ነው፡፡ የመስቀል ደመራ ሥርዓት በደቡብ ውስጥ የሠረፀው እና መከበር የጀመረው በዚህ ዘመን ወይንም ቀደም ብሎ መሆን አለበት፡፡ አንድን ሥርዓት ባህል ለማድረግ ብዙ መቶ ዓመታት ያስፈልጋልና፡፡
በደቡብ ግራኝ ሊያጠፋቸው ካልቻሉ ክርስቲያናዊ ሥርዓቶች አንዱ መስቀል ነው፡፡ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጉራጌ፣ በከፋ ሸካ ከነ ክብሩ እና ሞገሡ አሁንም ይከበራል፡፡ አንዳንድ ሕዝቦች ትምህሩ ጠፍቶባቸው እንኳን ሥርዓቱን አልረሱትም፡፡ ይህ ነገር የደመራ በዓል ከግማደ መስቀሉ መምጣት በፊት በሀገራችን ሊኖር እንደሚችል ያመለክታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዜና መዋዕሎችን እና መዛግብትን ማገላበጥ ገና ይቀረናል፡፡
በሌላም በኩል የደብረ ታቦርን እና የአዲስ ዓመት መለወጫን በዓል በደመራ እና በችቦ የማክበሩ ባህላችን ደመራ ከመስቀል በዓል ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑን ፍንጭ ይሰጠናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይህንን ችቦ የማብራት ሥርዓት ከጥንት ሀገራዊ ባህል እና ከኢየሩሳሌም መብራት የማውጣት ሥርዓት የቀመሩት ይመስላል፡፡ በኢየሩሳሌም ከጌታ መቃብር በየዓመቱ ለበዓለ ትንሣኤ መብራት የማውጣት ሠርዓት ነበር፡፡ ይህ ሥርዓት ልዩ ልዩ የፈትል እና ዘይት መብራቶችን በአንድነት አስተሣሥሮ ይዞ መውጣት ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት በኢትዮጵያዊው ችቦ በመወከል በበዓል ቀን እንዲበራ ሥርዓት የሠሩልን አባቶች በረከታቸው ይደርብን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።