ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን ሰሜን አሜሪካ ማዕከል ድረ ገጽ
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሰን
«ጥምቀት» የሚለው ቃል ተጠምቀ ተጠመቀ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ቃል በቃል ሲተረጐምም መጠመቅ፣ ውሃ ውስጥ ገብቶ መነከር፣ መዘፈቅ ይሆናል፡፡ ሳምንቱ ዘመነ አስተርእዮ ይባላል፡፡ ስያሜውም ለወሩና ለሳምንቱ የተሠጠበት ምክንያት፡-
2ኛ. ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በ3ዐ ዓመቱ በተጠመቀ ጊዜ የሥላሴ ሦስትነት በዮርዳኖስ በግልጥ ታይቶአል፡፡ ማቴ. 3፤16፡፡ ስለዚህም ዘመኑ ዘመነ አስተርእዮ ተባለ፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ የፈጸማቸው ሥራዎች፡-
ሀ/ የዕዳ ደብዳቤያችንን ደመሠሠልን
በአዳምና በሄዋን መተላለፍ ምክንያት አዳምና ሄዋን የ እግዚአብሔር ን ልጅነት ርስታቸው ገነትን አጥተው በሞት ጥላ ሥር ወደቁ፡፡ የ እግዚአብሔር ልጆች የነበሩ የሳጥናኤል ባሪያዎች ሆኑ፤ ዲያብሎስ በተንኰሉ የሰው ልጆችን ለዘለዓለሙ ለመኰነን «አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሄዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ» «አዳም የዲያብሎስ ባሪያው ነው፤ ሄዋን የዲያብሎስ ገረድ ነች» የሚል የሰው ልጆች መቅጫ የሚሆን ጽሑፍ በዮርዳኖስ እና በሲኦል አስቀምጦ ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ በዮርዳኖስ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን ደምስሶ አጠፋልን፡፡ ስለዚህ ነው ቅዱስ ዮሐንስ «የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የ እግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ»ሕ1ኛዮሐ.3፡9ሕ በማለት የመሠከረው ቅዱስ ጳውሎስም ለገላትያ ምዕመናን በጻፈላቸው መልእክቱ «በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን» ሕገላ.5፡1ሕ በማለት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕዳ ደብዳቤያችን ደምስሶ ከሞት የባርነት አገዛዝ ነጻ እንዳወጣን አስረድቶአል፡፡ ስለሆነም ይህ በዓል እኛ ክርስቲያኖች የ እግዚአብሔር ን ልጅነት ያገኘንበት ስለሆነ በድምቀት እናከብረዋለን፡፡
ለ/ በጥምቀቱ ወለደን
አዳምና ሄዋን ከተፈጠሩባት ኤልዳ ከምትባል ቦታ አዳም በ4ዐ ቀን ሄዋን በ8ዐ ቀን በይባቤ መላእክት ወደ ገነት ገብተው ነበር፡፡ ኩፍሌ 4፡9-13፡፡ ሕጉን በተላለፉ ጊዜ ከገነት ወጥተው፣ ልጅነታቸውን አጥተው በጉስቁልና ወድቀው ሲኖሩ እግዚአብሔር ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ ሰውን ለመፈለግ አምላክ ሰው ሆነ የአዳምን ልጅነት ለመመለስ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ «ኀዲጎ ተሥዐ ወተሰዐተ ነገደ ቆመ ማዕከለ ባህር» ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ ሰውን ለመፈለግ አምላክ ከባህር ውስጥ ቆመ በማለት ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንደገለጸው አምላክ በውሃ ተጠምቆ ጠፍተን የነበርነውን ፈለገን፤ ፈልጐም አዳነን፤ የመጀመሪያ የልጅነት ጸጋችንን መለሰልን፤ ወራሾቹም አደረገን፡፡ «ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ ወዳጆቼ ናችሁ» ዮሐ.15፡14፡፡ እግዚአብሔር ወልድ በጥምቀቱ ወለደን «ወለደነ ዳግመ እመንፈስ ቅዱስ ወማይ»፤ «ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ወለደን» እንዲል በጥምቀቱ ሀብተ ልደት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ሠጠን፤ ጥምቀትን መዳኛ የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር አደረገው፤ ያለጥምቀት ሰው መዳን አይችልምና፡፡ «ሰው ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ የ እግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም» ዮሐ.3፡5 በማለት በጥምቀት ልጅነት በልጅነት ድህነት እንደሚገኝ አስረድቶአል፡፡ ማር. 16፡ 10፡፡
- ሰው የሥላሴ ልጅ ሊሆን የሚችለው በጥምቀት ነው፡፡ ዮሐ. 3፡ 6
- ጥምቀት ከጌታችን ከአምላካችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ያደርጋል፡፡ ገላ. 3-26
- በጥምቀት የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እንሆናለን፡፡ ልጅ የአባቱን ርስት እንደሚወርስ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ የሚችለው በጥምቀት በተቀበለው ልጅነት ነውና «ልጆቹ ከሆን ወራሾቹ ነን» ገላ. 4-7
ሐ/ በጥምቀቱ ሕዝብና አህዛብን አንድ አደረገ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በዮርዳኖስ ወንዝ ነው፡፡ የዮርዳኖስ ምንጭ ከላይ አንድ ሲሆን ለሁለት ይከፈልና ዝቅ ብሎ አንድ ይሆናል፡፡ ጌታችን ከመገናኛው ተጠምቆአል ይህም ሕዝብና አህዛብ በጥምቀቱ አንድ እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ በጌታ ጥምቀት ሕዝብና አህዛብ አንድ እንደሆኑ «ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና አይሁዳዊ፣ ግሪካዊ፣ ባሪያ፣ ጨዋ፣ ወንድ፣ ሴት የለም ሁላችሁም በክርስቶስ አንድ ሰው ናችሁ» በማለት የሰው ዘር ልዩነት በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ ተወግዶ ሰው እኩል መሆኑን እና በጥምቀት አንድ ሰው መሆኑን አስረድቶአል፡፡ ገላ. 3፡27፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ከዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ያደረገውን አምላካዊ ጉዞ ለማሰብ ታቦታቱ በካህናትና በምእመናን ታጅበው ወደ ባህረ ጥምቀት ተጉዘው አምሳለ ዮርዳኖስ በሆነውና በተዘጋጀላቸው ስፍራ ያርፋሉ፡፡ ሌሊቱን በሙሉ በማኅሌትና በቅዳሴ በዓሉ እየተከበረ ያድርል፡፡ ጧት የበረከት ጥምቀት ከተፈጸመ በኋላ በደማቅና በልዩ ልዩ ሥነ ሥርዐት በስብሐተ እግዚአብሔር በዓሉ ይከበራል፡፡ ታቦታቱም በማኅሌትና በእልልታ ታጅበው ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ፡፡
ይህ ዕለት ነጻ የወጣንበት የዕዳ ደብዳቤያችንን የተደመሰሰበት ከ እግዚአብሔር ጋር አንድ የሆንበት ዕለት ስለሆነ ልዩ በሆነ ደስታ እናከብረዋለን፡፡ ይህንን ታላቅ በዓል በምናከብርበት ጊዜ በክርስቶስ የተደመሰሰው ኃጢአትን አስወግደን እንደ ልብሳችን ልባችንን በንስሐ አጥበን ንጹሐን ሆነን ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን አስገዝተን እግዚአብሔር ን ከሚያሳዝን ከኃጢአት፣ ከተንኰል፣ ከዘረሕነት፣ወዘተ ሁሉ ርቀን ለነፍሳችን በሚጠቅም በፍፁም መንፈሳዊ ሥርዓት በዓሉን ልናከብር ይገባናል፡፡ ለዚህም አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
kale hiwot yasemalin
ReplyDelete