Jan 31, 2015

ጾመ ነነዌ


ምንጭ ፈለገ ስላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን
በየአመቱ በዕለተ ሰኑይ ብቻ (ሰኞ ቀን ብቻ) የሚጀምሩ ሦስት አጽዋማት አሉ፡፡ እነርሱም ዓቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነዚህ አጽዋማት ምን ጊዜም ቅበላቸው እሁድ ሲሆን የሚገቡት ደግሞ ሰኞ ቀን ነው፡፡ በየትኛውም አመት ይህን ዕለት አይለቁም፡፡
ስለዚህ 2007 ዓ.ም ጾመ ነነዌ ጥር 25 (Feb. 2/2015) የፊታችን ሰኞ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በየግላችንም ያጋጠሙንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ውጊያዎች በማሰብ ድል የምናደርግበትን ኃይል ፈጣሪያችን ይሰጠን ዘንድ ጾሙን ከወትሮው በበለጠ ጥንቃቄ ልንጾመው ይገባናል

የነነዌ ጾም ከሰባቱ የቤተክርስቲያን አጽዋማት አንዱና የዐቢይ ጾም ማዘጋጃ ደወል ነው፡፡ ይህ የነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ በቤተክርስቲያናችን በጣም ታላቅ ዋጋ ያለውና የራሱ መዝሙር የሚዘመርለት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት ታላቅ መታሰቢያ ያለው ታሪክ ነው፡፡ ራሱ ጌታችንም የነዌ ሰዎችን የንስሐ ታሪክ በመጥቀስ አይሁድን ገስጾበታል፤ በፍርድ ቀንም በዚያ ትውልድ ዘንድ እንደሚፈርዱበት ተናግሯል፡፡ ይህም የሆነበት የነነዌ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ የንስሐ ታሪክ ስላላቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን አስደሳች የንስሐ ታሪክ በጾመ ነነዌ ከሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት አንጻር ለመመርመር እንሞከራለን፡፡
ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆን ሁሉ ንስሐ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ በዚህ ከእግዚአብሔር ሊለዩ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች ባለቡት ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን ሁሉ የንስሐ ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም ጊዜ በተለየ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስባቸው የጾም ወቅቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ታላቁና ዋነኛው ዐቢይ ጾም ነው፡፡  ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በዐቢይ ጾም ከእያንዳንዱ ምእመን ልቦና የንስሐ ፍሬን ትፈልጋለች፤ ያለትንሣኤ ልቦና /ንስሐ/ የክርስቶስን ትንሣኤ በእውነትና በደስታ ማክበር አይቻልምና፡፡ ለመሆኑ ከንስሐ የሚያሰናክሉን ነገሮች ምን ምን ናቸው? የነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለዚህ ምን ያስተምረናል?
. ቅንጦትን መውደድ
ምንም እንኳን በደፈናው ገንዘብ የኃጢአት ምንጭ ነው ባንልም እንደ ወንጌል ትእዛዝ በክርስቲያናዊ መንገድ ካልተያዘ ግን እግዚአብሔርን ሊያስረሳና የኃጢአት ማስፈጸሚያና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜም ገንዘብና ባለጸግነት ከእግዚአብሔር በመለየታችን ያጣነውን ሰላምና ደስታ ለማግኘት ተስፋ የምንጥልበት ጣኦት ሆኖ ሊቀየር ይችላል፡፡ በሀብታችን በምናገኘው ጊዜያዊ ደስታና ሰላም ዘላለማዊውንና ፍጹምን የእግዚአብሔር ስጦታ መፈለግ፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስን መናፈቅ ልናቆም እንችላለን፡፡ በዚህ መልኩ ብልጽግና ከንስሐ የሚያሰናክል ወጥመድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር ሀብት እንኳ ቢሰጠን ለተቸገረ በመመጽወት፣ ልጆቻችን በክርስቲያናዊ መንገድ በማሳደግ፣ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት በማፋጠን የእውነተኛ ደስታና የጽድቅ መንገድ እንድናደርገው እንጂ እግዚአብሔርን የተጠማች ነፍሳችንን ጥሪዋን በማደናቀፍና ጩኸቷን በማፈን በሥጋ ድሎት ውስጥ የምንደበቅበት መሣሪያ እንድናደረገው አይደለም፡፡ «ታላቂቷ ከተማ» ነነዌም የጥፋት መንገድ የሆናት በብልጽገናዋና በታላቅነቷ እግዚአብሔርን ረስታ የኃጢአት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክ ውስጥ ገንዘብ ለዮናስ ከእግዚአብሔር የመከለያ መሣሪያ ሲሆን እናገኘዋልን፡፡ «. .. ከእግዚአብሔርም ፊት ኮብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ /ወደ መርከቧ/ ገባ» እንዲል /ዮና፤1-3/፡፡
በዚህ ሰዓት ለዮናስ ገንዘብ ባይኖረው ይሻል ነበር፡፡ እኛም ቢሆን ከንስሐ የሚመልስ፣ ለኃጢአት መሣሪያ የሚሆን ሀብት ከሚኖረን በድኅነት ብንኖር ይሻለናል፡፡ ምንም እንኳ በቤተክርስቲያናችን ትውፊት ዐቢይ ጾም አብዝተን የምንጸልይበት፣ በጾም በስግደትና በምጽዋት ልናሳልፈው የሚገባ ወቅት ቢሆንም አሁን አሁን ግን ገንዘብ ማግበስበሻ እየሆነ እንደሆነ እናያለን፡፡ በመሠረቱ በጾም ወቅት ከሆዳችን የምንቀንሰው ገንዘብ እንድናጠራቅመው ሳይሆን እንድንመጸወተው የሚገባ ነው፡፡ ለማጠራቀምማ የማያምኑ ሰዎችስ ምግብ ይቀንሱ የለ? ለዚህ ነው በነነዌ ጾም በመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት «አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ፡፡ ሀብታችሁ ተበላሽቷል፣ ልብሳችሁም በብል ተበልቷ፡፡ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጓል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል፡፡ ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል፡፡ እነሆ እርሻሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፣የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ጸባዖት ጆሮ ገብቷል፡፡ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፤ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል፡፡» በማለት አስፈሪ ተግሳጽ የሚያስተላልፈው፡፡ ስለዚህ በዐቢይ ጾም አብዝተን የምንመጸውትበት፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ስጦታ የምንፈልግበት፣ የንስሐ ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡
. ለኃጢአት ሌላ ተጠያቂ መፈለግ
ሌላው ከንስሐ ሲያርቀን የሚገኘው ምክንያት በሰዎች መፍረድ ነው፡፡ በሰዎች የሚፈርድ ሰው ራሱን የሚያጸድቅ ነው፡፡ ራሱን ያጸደቀ ደግሞ ንስሐ መግባትና ከኃጢአት መመለስ ዳገት ይሆንበታል፡፡ ከነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ ውስጥ ለንስሐ በጣም አስቸጋሪ የነበረው ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ መርከበኞቹና የነነዌ ሰዎች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ዮናስ ግን ከታሪኩ መጀመሪያ እስከ መጨረሻዋ ጊዜ ድረስ በእግዚአብሔር ያጉረመርም ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከእግዚአብሔር መኮብለሉና የነነዌ ሰዎችን ድኅነት መቃወሙን እንደ ስህተት እንጂ እንደራሱ ስህተት አለመቁ ጠሩ ነው፡፡ ለዚህ ነበር ከእግዚአብሔር ኮብልሎ ሲሔድ እንኳ ምንም ዓይነት ጭንቀት ሳይሰማው «በከባድ እንቅልፍ» ተኝቶ የነበረው /ዮና.1-5/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ኃጢአት እግዚአብሔርን ተጠያቂ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በራሳቸው ከመፍረድ ይልቅ በሰዎች መፍረድ ይጀምራሉ፤ ወይም የኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔርን አድርገው ይገኛሉ፡፡ ነቢዩ ዮናስ የራሱን ክብር ፈላጊነት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት የኃጢአቱ ምክንያት ማድረጉ የሚያስገርም ነው፡፡ ይህም ለብዙ ጊዜ ከንስሐ እንዳዘገየው ከታሪኩ እንማራለን፡፡ በተቃራኒው ለንስሐ ቅርብ የሆኑት መርከበኞች በዮናስ ላይ ለመፍረድ ምን ያህል እንደተጨነቁ ስናይ ቀድሞውኑ በዮናስ አለመታዘዝ ምክንያም ቢሆን እግዚአብሔር ወደ ንስሐ ሊመልሳቸው የፈለገ ይህን አይቶ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
በጾመ ነነዌ የመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ጳዉሎስ መልእክትም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡- «ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፣ የምታመካኘው የለህም በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኮንናለህና፡፡ አንተም ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና፡፡ እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለንና፡፡ . . . ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ስታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን ቁጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ»/ሮሜ.2-1-5/፡፡ በተቃራኒው ግን በሰው ላይ ከመፍረድ በራሳቸው ላይ መፍረድን የሚመርጡ ሰዎች ለንስሐ ቅርብ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ቀን ማክሰኞ የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትም የሚያብራራው ይህንኑ ነው/1ቆሮ.4-1/
. የእግዚአብሔርን ተግሳጽ አለመቀበል
በነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ሰዎችን ሲገስጽ እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ዮናስን በማዕበል፣ ወደባሕር እንዲወረወር በማድረግ፣ አሳ አንበሪ እንዲውጠው በማድረግእግዚአብሔር ወደ ትክክለኛ መንገዱ ሊመልሰው ቢጥርም በዚህ ሁሉ ሊመለስ አልቻለም፤ ከአሳ አንበሪ አፍ ወጥቶ ሔዶ ቢሰብክም እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው ግን በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ጀምሯልና፡፡ ድሮም ቢሆን በፍርሃት እንጂ ስህተቱን ተቀብሎ አልነበረም ወደ ነነዌ ሔዶ የሰበከው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ነፋስ፣ አሳ አንበሪ፣ ትል፣ ፀሐይ/ እንዴት እንደሚታዘዙለት እርሱ ግን ታላቅ ነቢይ ሲሆን አልታዘዝም ማለቱን በማሳየትም ገስጾታል፡፡ በመጨረሻም ለንስሐ በቅቷል፡፡ መርከበኞቹም በመርከባቸው ላይ የተነሣው ማዕበል ተግሳጽ ሆኗቸው ወደ ንስሐ ተልሰዋል፡፡ ከዘላለም ሕይወት እንዳንለይ አጥብቆ የሚፈልገው እግዚአብሔር ልዩ ልዩ መከራዎችንም በማምጣት ወደ ንስሐ እንድንመለስ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ተግሳጽ ግን በትክክለኛ ወይም በተሳሳተ መንገድ መልስ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ ካወቅንባቸውና ከተጠቀምንባቸው ችግሮችና መከራዎች ወደንስሐ የሚመሩ መንገዶች ናቸው፡፡ የነነዌ ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ በነነዌ ጾም በቅዳሴ የሚነበቡት የሚከተሉት ምንባባትም በአጽንኦት የሚገልጹት ይህንኑ ነው፡፡
ምስባክ:- «ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ፡፡ እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዛል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል የእኔ ስዕለት ለሕይወቴ አምላክ ነው፡፡» /መዝ.41-7-8/
መልእክት:- «. . . ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል. . .» /ሐዋ.14-22/፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አሳዛኙ ነገር ሰው ካለፈ ሕይወቱ አለመማሩ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክም የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተሳፈረበትን መርከብ ካናወጠ፣ ዮናስ በአሳ አንበሪ እንዲዋጥ ካደረገ በኋላ እንኳ እግዚአብሔር በነነዌ ሰዎች ላይ ያሳየው ምሕረት ዮናስ ሞትን እስኪመኝ ድረስ እንዲያዝንና በእግዚአብሔር ላይ እንዲያጉረመርም አድርጎታልና፡፡ በእኛም ሕይወት ተመሳሳይ ተግሳጻት ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢመጣም ከኃጢአት ባለመመለስ ከዮናስ ያልተለየ መልስ ነው የምንሰጠው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ራሳችንን የምናይበት፣ በሕይወታችን ያደረጋቸውን የእግዚአብሔር ሥራዎች የምንመረምርበት፣ በውስጣችን ያደፈጡትን አውሬዎች የምናድንበት የተረጋጋና ሰፋ ያለ ጊዜ ስለሌለን ነው፡፡ ይህን አጥብቃ የተረዳችው ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በልዩ ልዩ መንገድ የሚጠራንን የእግዚአብሔር ድምፅ የምናዳምጥበት፣ በመልካም ምክንያቶች የተሸፈኑ ነገር ግን መልካም ያልሆኑና መልካም ልንሠራበት የምንችለውን የሕይወት ጊዜዎችን የሚያቃጥሉ ከንቱ ምኞቶቻችን፣ የማይጨበጡና የማይደረስባቸው «ክፉ ተስፋዎቻችን» ሁሉ የምንመረምርበት፣ መልካሟንና እውነተኛዋን ነገር ግን አስቸጋሪዋንና ጠባቧን የሕይወት መንገዳችን አጉልተን «የምናስምርበት» ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥታናለች፤ ይህም ዐቢይ ጾም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በአግባቡ ከተጠቀምንበትም የዚህን አስቸጋሪና አወናባጅ ዓለም በድል የተወጡ ሰዎች የሚያዩትን የዘለዓለማዊን ሕይወት «ቀብድ» የትንሣኤውን ብርሃን እናያለን፡፡ ዐቢይ ጾምን እንደሚገባ ያላሳለፈ ክርስቲያን ግን የትንሣኤን ድግስ በልቶ ሆዱን ይሞላ እንደሆነ እንጂ የትንሣኤን ታላቅ ደስታ መቅመስ አይችልም፡፡ ስለዚህም ዐቢይ ጾም ለክርስቲያን ታላቅ ስጦታ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ስለጾም በጻፉት መጽሐፋቸው «በዐቢይ ጾም ሕይወቱን ያልቀየረ ክርስቲያን በሌሎች አጽዋማት ይቀይራል ማለት ይከብዳል» በማለት የጻፉት፡፡
. ክፉ እኔነት
በዮናስ ታሪክ ውስጥ ከብዙ የዮናስ ስህተቶች ጀርባ የነበረውና ንስሐውን ያዘገየበት ታላቁ መሰናከል ክፉ እኔነት ነው፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የነነዌ ሰዎችን ድኀነት ሳይሆን የራሱን ክብር እንዲመለከት ያደረገው በዮናስ ሕይወት ውስጥ በጥልቅ የተተከለ ክፉ እኔነቱ ነው፡፡ በዚያ ሁሉ ታሪክ ውስጥ በርግጥም ዮናስ ስለራሱ እንጂ ስለሰዎች ሲያስብ አልታየም፡፡ ነቢዩ ዮናስ «እኔ ሐሰተኛ ነቢይ ከምባል የነነዌ ሰዎች መጥፋት ይሻላል»«የዮናስ አምላክ ቃሉን ይቀይራል ከምባል የነነዌ ሰዎች ይጥፉ» ብሎ ያስብ እንጂ እግዚአብሔር ግን አላለም፡፡ አመድና ትቢያ የሆነው የሰው ልጅ ስለክብሩ ሲጨነቅ ክብር የባሕሪዩ የሆነ ሩህሩህ አምላክ ግን ማንም እንዲጠፋ አልፈቀደም፡፡ በርግጥ የነነዌ ሰዎች በመዳናቸው የዮናስም የእግዚአብሔርም ቃለ አልታበለም፡፡ ዮናስ «ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች» ብሎ ሰበከ፡፡ አመጸኛዋ ነነዌ ግን በቁጣ እሳት ከመጥፋቷ በፊት በንስሐ ራሷን አዋረደች፡፡ በዚያን ጊዜ ነነዌ በንስሐ አዲስ ፍጥረት የሆነች፣ እግዚአብሔር የሚያጠፋት ሳትሆን የሚወዳት ሌላ ነነዌ ሆነች፡፡ ዮናስ ሆይ በንስሐ የታደሰችው ነነዌ የእግዚአብሔርቅን ፍርድ እንደማያጠፋስ ለምን አላሰብክም? ታላቁ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆይ ንስሐ የገባችዋን ነነዌን ማጥፋት አምላክህን አያስነቅፈውምን? በነቢዩ በዮናስ ውስጥ ያለው እኔነቱ በርግጥምእግዚአብሔርንም፣ የነነዌ ሰዎችንም እንዳያስብ መጋረጃ ሆኖበት ነበር፡፡
በነቢዩ በዮናስ ሕይወት ወስጥ ክፉ እኔነቱ በዚህ መልክ ቢገለጥም፣ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ግን በተለያየ መንገድ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አንዳንዶቻችን «እኔ ቅዱስ ነኝ» የማለት ክፉ እኔነት ተጠናውቶናል፡፡ ኃጢአታችን ለንስሐ አባታችንና ለጓደኞቻችን ስንናገር እንኳ «ኃጢአትን የመናገር ቅድስና» እንጂ ኃጢአተኝነታችን አይሰማንም፡፡ «እኔ ርኩስ ነኝ» ስንልም ራስን በፈቃድ ኃጢአተኛ የማድረግ «ቅድስና» እንጂ ልባዊ የሆነ ንስሐ አይሰማንም፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ «እኔ አዋቂ ነኝ» የማለት ክፉ እኔነት ይዞናል፡፡ «እኔ እኮ ምንም አላውቅም» ብለን ስንናገር እንኳን በልባችን ራስን ዝቅ ማድረግን «እያስተማርን» ነው በፍቅር ከተሰባሰቡ መንፈሳውያን ወንድሞችና እኅቶች መካከል እንኳን «ወርቃማ መንፈሳዊ ምክሮችን» ለመለገስ እንጂ መች ፍቅርን 'ከታናናሾቻችን' ለመማር እንቀመጣለንና፡፡ በዚህም በባዶነታችን እንኖራለን፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን «ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች መድኃኒት አያስፈልጋቸውም» ብሏል፡፡ ሕመምተኞች መሆናችን አውቀን በንስሐ ብንቀርብ መድኃንኒት ይሆነናል፤ ራሳችንን አጽድቀንና «ቅዱስ ነኝ» ብለን በውሸት የጤንነት ስሜት መድኃኒት መፈለግ ከተውን ግን ከነኃጢአታችን እንሞታለን፡፡ ጌታችን ለእውራን ብርሃን፣ ዕውቀት ለሌላቸው ሰማያዊ ጥበብን የሚሰጥ ራሱ የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ራሳችን በአዋቂዎች ተራ ከመደብን መምህር አልፎን ይሔዳል፡፡ ጌታ አለማወቃቸውን ያወቁትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ጥበብን የሚፈልጉትን ሲያስተምር እንጂ «ምሁራንን» ሊያስተምር አልመጣምና፡፡ በኃጢአት መኖር እንደ ሀሞት መሮት፣ እንደጨለማ ከብዶት ከልቡ የሚጮኽን ተነሣሒ ለመቀደስ፣ እግዚአብሔር የዕውቀት ምንጭ የሕሊና ብርሃን መሆኑን አውቀው ከጥልቅ ከልቦናቸው ዕውቀትን የሚፈልጉትን ለማስተማር መጥቷልና እንደዚሁ ካልሆንን ከዚህ ጸጋ ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡
ይህን ሁሉ የሕይወታችን ውጥንቅጥ እንመረምርበት ዘንድ ታላቁ የቤተክርስቲያን ስጦታ ዐቢይ ጾም እነሆ፡፡
የእውነተኛ ንስሐ ውጤቶች በነነዌ ሰዎች ታሪክ
. የዘላለም ሕይወት ተስፋ
ነነዌ የጥፋት ፍርድ ከተፈረደባት በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጣት ከተማ ናት፡፡ በሌላ አነጋገር ነነዌ ሞታ የተነሣች ከተማ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ነቢዩ ዮናስም ወደ ባሕር ከተጣለ፣ በአሳ አንበሪ ሆድ ውስጥ ካደረ በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጠው ሰው ነው፡፡ መርከበኞችም መርከባቸው በማዕበል ከተመታች በኋላ፣ ማዕበሉ ካሸነፋቸው በኋላ በእግዚአብሔር ምሕረት ሌላ የመኖር ተስፋ የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የነነዌ ታሪክ የተስፋ ታሪክ ነው፡፡
ንስሐም በኃጢአት ከሞቱ በኋላ እንደገና የመኖር ተስፋ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የዘለዓለም ሕይወትን ተስፋ ማድረግ ይከብዳቸዋል፤ ለዚህም ምክንያቱ በንስሐ አለመኖራቸው ነው፡፡ ሰው ያላየውን ነገር እንዴት ይናፍቃል? የማያውቀውን ነገርስ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? በንስሐ የሚኖር ሰው ግን የዘለዓለም ሕይወት ቀብድ የሆነ ትንሣኤ ልቦናን ይነሣልና የዘለዓለም ሕይወትን በተስፋ ይናፈቃሉ፡፡ ዐቢይ ጾምንም በንስሐና ራስን በመመርመር ያሳለፈ ሰው በትንሣኤው ትንሣኤን ይቀምሳልና ዘለዓለማዊውን ትንሣኤ በተሰፋ ይናፍቃል፡፡
በነነዌ ጾም የሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባትም ይህን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡-
«. . . ትዕግሥትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም፡፡» /ሮሜ.5-4-5/፡፡

«እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ፡፡» /ይሁዳ.1-20/፡፡
. በእግዚአብሔር ዘንድ መከበር
በንስሐ የተመለሰችው ነነዌ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ከብራለች፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በማይገቡ ዘንድ በትውልዱ ሁሉ ምስክር ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዷል፡፡ «የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፣ እነሆም «ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ» እንዲል /ሉቃ.11-32/፡፡ የነቢዩ የዮናስ ታሪክም እንደዚሁ ነው፡፡ የንስሐ ሰባኪ የሆነው ራሱም ከብዙ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኋላ በንስሐ የተመለሰው ዮናስ የክርስቶስ ምልክት እንዲሆን እግዚአብሔር መፍቀዱ እግዚአብሔር ለተነሳሕያን የሚሰውን ክብር ያሳያል፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ምድር ያለን ሰዎች የተነሣሕያንን ክብር ባናውቅም በሰማይ ያሉ መላእክት ግን በአንድ ኃጢአተኛ ንስሐ መግባት ታላቅ ደስታ ማድረጋቸው የንስሐን ክብር ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው ለንስሐ የተዘጋጀ ልብን በማየት እግዚአብሔር አስቀድሞ ነነዌን «ታላቂቷ ከተማ» ብሎ የጠራት /ዮናስ.1-2/፡፡ ተነሣሕያን የእግዚአብሔር ይቅርታና ፍቅር የሚገለጥባቸው ሰዎች ናቸውና በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ዘንድ የከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡
. የእግዚአብሔርን ኃይል ማየት
በነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔር ኃያልነት በግልጥ ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ኃያልነትም በትዕግሥቱ፣ በፍቅሩ፣ ፍጥረትን በመግዛቱ፣ ለሰው ልጆች በሰጠው ድንቅ ነፃነት ወዘተ ተገልጧል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንዲትም ነፍስ ሳትጠፋ ሁሉም ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር ያሳየው የትዕግሥቱ ኃያልነት እንዴት ድንቅ ነው! የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተምር ዘንድ ነቢይ የሆነው ዮናስ እንኳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቶ ሲኮበልል በሔደበት ሁሉ እየተከተለ በተለያየ መንገድ ወደ መንገዱ እንዲመለስ ይሠራ ነበር፡፡ ምናልባትም ሰው ዮናስን ይህን ያህል አይታገሰውም፡፡ ሰዎችእግዚአብሔርን 'የመምከር' ዕድል ቢሰጠን «ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ማድረግ ትችላለህ፤ ከነዚህ ድንጋዮት እንኳ ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት ትችላለህ፡፡ ለምን ዮናስን ትለምነዋለህ? ተወው ሌላ ነቢይ ወደ ነነዌ ላክ፡፡ ዮናስን ርግፍ አድርገህ ተወው ከነነዌ ሰዎች የራሱን ክብር አስቀድሟልና፡፡» እንል ይሆናል፡፡ በባሕሪዩ ታጋሽ የሆነው እግዚአብሔር ግን ዮናስ በንስሐ ይመለስ ዘንድ ጠብቆታል፤ በመጨረሻም ለክርስቶስ ምሳሌ የሚሆን ታላቅ ነቢይ አድርጎታል፡፡
በነነዌ ታሪክ የእግዚአብሔር የፍቅሩ ታላቅነትም ተገልጧል፡፡ የእስራኤል አምላክ ይባል እንጂ ከአሕዛብ መካከል ለንስሐ የተዘጋጀ ሕዝብ ሲያይ ነቢዩን ልኮ ሕዝቡ አድርጓቸዋል፡፡ ቀና ልብ ያላቸው፣ ዮናስ ሲተኛ እንኳ ለማያውቁት አምላክ ሲጸልዩ የነበሩትን መርከበኞችንም በዮናስ ምክንያት እንዲያውቁት አድርጓል፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር ወደርሱ የምታይን ነፍስ፣ እርሱን የተጠማችን ልቦና አይተዋትም፡፡ በነነዌ ሰዎች ታሪክ የታየው ሌላው የእግዚአብሔር ኃይል በፍጥረቱ ላይ ያለው ሥልጣን ነው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ፀሐይ፣ ማዕበል፣ ትል፣ ዛፍ፣ አሳ አንበሪ. . . / የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያለምንም ተቃውሞ ሲፈጽሙ እናያለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን ታላቅ ስጦታ 'ነፃነትን' እናደንቃለን፡፡ ፍጥረታት የሚታዘዙለት ኃይል እግዚአብሔር በነፃነት የፈጠረው የሰው ልጅ ፈቃዱን ሲጥስ ይመለስ ዘንድ በሚታዘዙት ፍጥረታት፣ በነቢያት. . . ይናገራል እንጂ ልቦናን በኃይሉ ቀይሮ እንደፈቃዱ እንዲኖር አያደርግም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መቀየር የፈለገን ልብ መቀየር የሚችል የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ፍጥረታቱን በማዘዝ አሳይቷል፡፡
ከዚህ ታሪክ ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው በንስሐ የምንኖር ከሆነ ወደዚህ ሕይወት እንደርስ ዘንድ እግዚአብሔር የታገሰባቸውን ያለፉትን የኃጢአት ዘመናት አስተውለን የእግዚአብሔርን የትዕግሥቱን ብርታት በሕይወታችን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ ስለ እግዚአብሔር ታጋሽነት ሰዎች ሊነግሩን አያስፈልግም፤ በሕይወታችን አይተነዋልና፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ የሠራውን የፍቅሩን ብርታትም እናውቃለን፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ምድር ላይ ከቢሊዮኖች መካከል አንድ ብንሆንም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በንስሐ መመለሳችን ሁሌ በእግዚአብሔር ሕሊና ውስጥ ሲታሰብ የኖረ፣ በሰማያት ካሉ ቅዱሳን ይልቅ የአንድ ኃጢአተኛ መመለስ ለሰማያትና ለእግዚአብሔር ደስታ የሚሰጥ መሆኑን ስናውቅ በርግጥም እግዚአብሔር እንዴት ሰውን ወዳጅ ነው? ነፍሳችንስ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል የምትወደድ ናት? እንላለን፡፡
ከዚህ ሌላ ፍጥረታት የእግዚአብሔር ሁሉን የማድረግ ሥልጣን በመታዘዝ እንዳሳዩ ሁሉ በንስሐ የተመለሰ ኃጢአተኛም የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት የሚታይበት ይሆናል፡፡ በኃጢአት የኖረን፣ አያሌ ዘመናትን በዲያብሎስ ምክር በጠማማ መንገድ የኖረን ልቦና መቀየር ከኃያሉ ከእግዚአብሔር በቀር ለማን ይቻለዋል? ኃጢአተኛን 'ቅዱስ' ማድረግ የእግዚአብሔር የብቻው የኃያልነቱ ውጤት ነውና፡፡ ለዚህ ነው 'ተነሳሕያን' ሰማዕታት ናቸው የሚባለው፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በሕይወታቸው ይመሰክራሉና፡፡ ጥንታውያን ክርስቲያኖች በደማቸው የእግዚአብሔርን ክብር መስክረው ከሆነ ለዚህ ትውልድ ደግሞ «የንስሐ» ሰማዕትነት ቀርቶለታል፡፡
በአጠቃላይ ከነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለንስሐ ብዙ እንማራለን፡፡ ለዚህም ነው ከብዙ የንስሐ ታሪኮች መርጣ ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ክብር የምታስበው፡፡ ለዚህም ነው ለታላቁ የንስሐ ወቅት ለዐቢይ ጾም ማዘጋጃ መግቢያ ያደረገችው፡፡ እኛም ከዚህ ታሪክ ተምረን፣ የተማረነውንም በንስሐ ወቅታችን /በአሁኑ ጾም/ በተግባር ልናውለው ይገባል፡፡ ለዚህም የተነሳሕያን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን፡፡

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።