Sep 27, 2016

የግማደ መስቀሉ ታሪክ 

የግሸን ማርያም ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት. ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ, በደላንታ, በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ የምትገኝ በሩአ አንድ የሆነ ዙሪያዋን በገደል የተከበበች በመስቀል ቅርጽ የተፈጠረች ልዩ ቦታ ናት. የአለም መድኃኒትን ክርስቶስን አይሁዶች ከስቀሉት በኋላ መስቀሉ ታምራትን በማድረጉ የተበሳጩት አይሁዳዊያን መስቀሉ ከተቀበረበት ቦታ ላይ ቆሻሻ አባራ በመጣል 300 አመታት ያህል ታላቅ ተራራ አድርገው ደበቁት. ንግስት እሌኒም በእግዚአብሔር ፈቃድ አስውጥታ ቤተመቅደስ አሰርታ አስቀምጣው ታላላቅ ታምራቶችን አደረገ. ከእስራኤላዊያንም እጅ የፋርስ ንጉስ ማርኮ በወሰደው ጊዜ እስራኤላዊያን የሮማን ንጉስ ሕርቅያልን እርዳታ በመጠየቅ አስመለሱት. ከዚህም በኋላ በኃያላን ነገስታት መካከል መስቀሉን እኔ እወስድ እኔ እወስድ ተጣሉ. የኃይማኖት መሪዎችም ተሰባስበው መስቀሉ በእጣ እንድክፋፈል አደረጉ. ቀኝ እጁ የተቸነከረበትና ያረፈበትም ግማድ መስቀል ለአፍሪቃ በደረሳት ጊዜ የግብጽ (የእስክንድርያ ፓትርያርክ) ተቀብሎ ግብጽ አስቀመጠው. በግብጽም ለብዙ ዘመናት ይህል ኖረ. በኢትዮጵያዊው አፄ ዳዊት ዘመነ መንግስት የግብጽ ክርስቲያኖች ከግብጻዊያን አህዛቦች ዘንድ ስቃይ ደረሰባቸው;... ለኢትዮጵያዊው ንጉስ ዳዊትም ስቃዩን ያስታግስላቸው ዘንድ ተማፀኑት ንጉሱም የክርስቶስ ልጆች መከራ ደረሰባቸው ብሎ 20,000 ሰራዊት አስከትሎ ወደ ግብጽ በታላቅ ቁጣ ገሰገሱ በዚህም ግዜ ግብጻዊያን አህዛቦች ፈሩ ተንቀጠቀጡ ንጉሱም ፈጥነው እርቅ እንድያደርጉ ካልሆነ ግን ግብጻዊያንን በታላቅ ቁጣ እንደሚያጠፋቸው መልእክት ላከ ግብጻውያንም ፈጥነው ታረቁ. በዚህም ጊዜ ግብጻዊያን ክርስቲያኖች በንጉሱ ዳዊትና በኢትዮጵያን ክርስቲያን ወገኖች ተደስተው ለንጉሱ 12,000 ወቄት ወርቅ ለንጉሱ የእጅ መንሻ ላኩላቸው. ንጉሱ ግን ይህንን ስጦታ መልሰው በመላክ ግማደ መስቀሉን እንድሰጧቸው በትህትና አመለከቱ. በዚህም ጊዜ የእስክንድርያ (የግብጽ) ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ተወያይተው መስቀሉን ስናር (ሱዳን) ድረስ በክብር መስከረም 21 ቀን አቀበሏቸው. ንጉሱ አፄ ዳዊትም ተመልሰው ኢትዮጵያ ሳይደርሱ በክብር አረፉ. የእሳቸውም ልጅ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደነገሰ ወደ ስናር ሂዶ ግማደ መስቀሉን አምጥቶ በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን መቅደስ አሰርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ ሌሊት በራዕይ "አንብር መስቀልየ በድበ መስቀል (መስቀሌን በመስቀልያ ቦታ አስቀምጥ) የሚል ትዕዛዝ ከጌታ ዘንድ መጣ .. ይህንም ቦታ ለሟግኘት ብዙ አድባራትን ዞሩ አላገኙምም ንጉሱ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እግዚእብሔርን ለመጠየቅ 7 ቀን ሱባኤ ያዙ;.. በዚህም ግዜ አምደ ብርሃን እየመራ እንደሚወስዳቸው ተነገራቸው አምደ ብርሃኑም አየመራ በመስቀልያ በተፈጠረች ልዩ ተራራ ግሸን አደረሳቸው መስከረም 21 ቀን ደረሱ በዚያም ታላቅ ቤተ መቅደስ አሳንጸው መስከረም 21 ቀን በዓሉን አከበሩ. ንጉሱ አፄ ዘርአ ያዕቆብም በዚህ ቀን በጽሁፍ ለምዕመናን አቀረቡ ከዚህም ግዜ ጀምሮ መስከረም 21 ቀን ይከበራል በቦታውም ልዩ ልዩ ታምራቶች ይደረጋሉ. የተራራው አቀማመጥ ከፎቶው እንደምታዩት መስቀልኛ ነው. ከእመቤታችን ክብረ በዓል በረከት ያሳትፈን አሜን.

ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !!!

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።