Sep 19, 2017

ባሕረ ሐሳብ

ባሕረ ሐሳብ
መስከረም 2010 ዓም
ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው::''ይህ ዓለም በሚዛን ተመዝኗልና ባሕርንም በላዳን ሰፍታልና የተሰጠው ዘመኑ እስኪፈጸም ደረስ ዝም ይላል አያልፍምም” ሱቱ. ዕዝራ 2:37 ዘመንን ባሕር ብሎ እንደተናገረ ቅዱስ ዳዊት እንዲሁ ቁጥርን ሐሳብ ይለዋል::መዝ. 31:1 ''ኃጢአታቸው በንስሐ የተሰረየላቸው በደላቸው በንስሐ ያልተቆጠረባቸው ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው''::ባሕረ ሐሳብ መርሐ ዕውራን፣ አቡሻህርና ሐሳበ ፈለክ ተብሎ  ተብሎ ይጠራል::አላዋቂወችን መርቶ ወደ እውቀት ደረጃ የሚያደርስ ስለሆነ መርሐ ዕውራን፣መጽሐፉን የጻፈው አቡሻህር የሚባል ሊቅ ስለሆነ  በስሙ ተጠርቷል እንድሁም የብርሃናትን የጸሐይን ጨረቃን ከዋክብትን እና ሐሳብ ነፋሳትን ስለሚያስረዳ ሐሳበ ፈለክ በመባል ይጠራል::


ባሕረ ሐሳብን የቀመረው ሊቅ ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው:: ድሜጥሮስ በእስክንድርያ ጌታችን ባረገ 180 ዘመን ሊቀ ጳጳስነት የተሻሞና በተሾመ በ27 ዘመኑ መንፈስ ቅዱስ ባህረ ሓሳብን የገለጸለት ሰው ነው::ቅድመ ታሪኩ እንደምነው ቢሉ በሀገራቸው በወቅቱ አህዛብ የበዛበት ስለነበር አህዛብን አግብቶ ንጹህ ነፍስ ከምትፈርስ ንጹህ ሥጋ ይፍረስ ብለው የዘመዱን ልጅ አጋብተውት ነበር:: እግዚያብሔር ሰውን ለአገልግሎት ይመርጣል ይጠብቃልና የድሜጥሮስ ሚስት የሙሽሮችን ስርዓት ሊፈጽሙ በመጋረጃ ሳሉ እንድህ አለች “ይህን ነገር ስለምን እንፈጸመዋለን?ዝምድናውን እቀህ ነው ወይስ እኔን እቀህ?” ብላ ድሜጥሮስን ጠየቀችው?እርሱም “የአባትና የእናቴን ትዕዛዝ ለመፈጽም እንጅ ይህንንስ አስቤ አይደለም ፈቃድሽ ከሆነ በአንድ ላይ በንጽህና እንኑር ተባብለው ሁለቱም ተግባብተው በአንድ ቤት በሥጋ ሳይተዋወቁ እግዚያብሔር በመላኩ አስጠብቋቸው በንጽህና ኖረዋል ::
የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የማርቆስ ዐሥራ አንደኛ የነበረው ዩልያኖስ የእርጅናው ሰዓት ሲደርስ ህዝቡ ተተኪ እንድሾምላቸው በጠየቁት መሠራት ከህዝቡ ጋር ሱባኤ ይዞ ድሜጥሮስን እንድሾምላቸው በመላአክ ተገልጦላት ሾሞታል::ድሜጥሮስ ከሚስት ጋር  ለ48 ዘመን ሲኖሩ ያላቸውን የኑሮ ሁኔታ ስለማያውቁና በዚህም እየተሰናከሉበት እያሙት ስለነበር ስርዓተ ቅዳሴ ከፈጸመ በኋላ ደመራ አሰርቶ ካደመራው የተቃጣለውን ፍም በእጁ እየታፈነ ለሚስቱ በነጣላዋ አስታቅፎ ምንም እሳቱ ሳይነካቸው በማሣያት ንጽህናቸውን ገልጾላቸውል:፡የኑዛዜንም ስርዓት የጀመረው ያን ጊዜ ነው:፡(ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ይበላችሁ ከኅጢአታችሁ የተፈታችሁ ሁኑ::)


ቅዱስ ድሜጥሮስ የጌታ ፈቃድ ቢሆን ጾመ ነነዌ፣ዐቢይ ጾም ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ ፣ደብረ ዘይት፣ሆሣዕና ፣ትንሳኤ፣ጰራቅሊጦስ ከእሁድ ረክበ ካህናት፣ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፣ ዕርገት ከኀሙስ ፣ስቅለት ከዓርብ ባይወጣ እያለ ይመኝ ስለነበር በመላአኩ ሱባኤ ገብቶ እንድሚገለጽለት ተነግሮት ከቀኑ 7 ከሌሊቱ 23 ሱባኤ ገብቶ የበአላትና የአጿማት ቀመር ተገልጾለታል::

የአጽዋማትና የበዓላት ሥርዓት


ዘመን ሳድሲትን በኃምሲት ኃምሲትን በራብዒት ፣ራብዒትን በሣልሲት፣ሣልሲትን በካልዒት፣ካልዒትን በኬክሮስ፣ኬክሮስን በሰዓታት፣ሰዓታትን በዕላታት፣ዕለታትን በሳምንታት ሳምንታትን በወራት፣ወራትን በዓመታት የሚሰፈር ነው :፡ከነዚህ ሰባቱ መሥፈርታት የሚባሉትም፡- ሳድሲት፣ ኃምሲት፣ ራብዒት፣ ሣልሲት፣ ካልዒት፣ ኬክሮስ እና ዕለት ሲኾኑ ሰባቱ አዕዋዳት ደግሞ፡- ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ ፀሐይ፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ማኅተም እና ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡


ዓመተ ዓለም

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ልደተ ክርስቶስ ያለው ዘመን ዓመተ ፍዳ ፣ዓመተ ኩነኔ ፣ዘመነ ብሉይ ይባላል:፡ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ያለው ደግሞ ዓመተ ምሕረት፣ዓመተ ሥጋዌ፣ዘመነ ሐዲስ ይባላል:: ሁለቱ በአንድ ላይ ማለትም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስካሁን ያለው ዓመተ ዓለም፣መዋዕለ ዓለም ይባላል:፡ ምሳሌ ፡- ዓመተ ዓለም በ2010ዓም በጸሐይ =5500(ዓመተ ፍዳ)+2010 ዓመተ ምሕረት=7510 ይሆናል ማለት ነው:፡

ዓመተ ዓለምን ለመቁጠር መስፈሪያ የሚሆኑ ሰባት አዕዋዳት ሲሆኑ ዐውደ ጳጉሜን ሲጨምሩ ስምንት ይሆናሉ::
  1. ዐውደ ዕለት :- የሰባት ዕለታት ዑደት ነው::ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባቱ ዕለታት ሲኾኑ፤ አውራኅን (ወራትን) ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡ጥንተ ዕለት(የመጀመሪያ) ዕለት እሑድ ነው::
  2. ዐውደ ወርኅ:- በፀሐይ 30 ዕለታት፣ በጨረቃ 29 ወይም 30 ዕለታት ናቸው፤ ዓመታትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
  3. ዐውደ ጳጉሜን:- 4 ዓመት ነው::እያንዳንዱ ዓመት በአራቱ ወንጌላዊ በማቴዎስ፣ማርቆስ ፣ሉቃስና ዮሐንስ እንደ ቅደም ተከተላቸው ተሰይሟል:: በዐውደ ጳጉሜን ውስጥ ዓመተ ወንጌላውያን ይገኝበታል::ዓመተ ወንጌላውያን ማለት ዓመተ ዓለም ለአራት ተካፍሎ ትርፍ ሆኖ የሚገኘው ዓመት ነው:: ይከውም ዓመተ ዓለም ለአራት ሲካፈል ትርፉ:-                                                                             
  • ዜሮ (ትርፍ ባይኖር)=ወንጌላዊው ዮሐንስ ጳጉሜን 6 ይሆናል:
  • 1 ቢሆን ወንጌላዊው ማቴዎስ ጳጉሜን 5 ነው
  • 2 ቢሆን ወንጌላዊው ማርቆስ ጳጉሜን 5 ነው::
  • 3  ቢሆን ወንጌላዊው ሉቃስ ጳጉሜን 5 ነው::
በዚህ መሠረት የ2010 ዓ.ም ወንጌላዊ =5500+2010 ሲካፈል ለአራት ነው ማለት ነው። 7510/4=1877 ቀሪ ሁለት(2) ይሆናል ወንጌላዊውም ማርቆስ ነው ማለት ነው::
  1. ዐውደ ዓመት:- በፀሐይ ቀን አቈጣጠር 365 ቀን ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ፤ በጨረቃ አቈጣጠር 354 ቀን ከ22 ኬክሮስ ከ1 ካልዒት ከ37 ሣልሲት ከ52 ራብዒት ከ48 ኃምሲት ነው፡፡  ከኬክሮስ በኋላ ያለችውን ስድስቷ ካልዒት ተደምራ ጳጉሜን 7 የምትሆንበት ዘመን አለ::
  2. ዐውደ ፀሐይ :- 28 ዓመት ነው፤ በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
  3. ዐውደ አበቅቴ:-19 ዓመት ነው፤ በዚህ ፀሐይና ጨረቃ ይገናኙበታል፡፡
  4. ዐውደ ማኅተም:-76 ዓመት ነው፤ በዚህ አበቅቴና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
  5. ዐውደ ቀመር :- 532 ዓመት ነው፤ በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ፣ አበቅቴም ይገናኙበታል፡፡

...........ይቀጥላል


              



0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።