Oct 4, 2017

እንኳን ለዘመነ ጽጌ አደረሳችሁ

ዘመነ ጽጌ
በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በወቅቶቶች ስርዓት ዑደት ውስጥ በዓመት አራት  ክፍሎች አሉ:: እነዚህም
  1. Related image
    ከመስከረም ፳፮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት መጸው ይባላል፡፡
  2. ከታኅሣሥ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት በጋ ይባላል፡፡
  3. ከመጋቢት ፳፮ እስከ ሰኔ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ፀደይ ይባላል፡፡
  4. ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክረምት ይባላል፡፡
ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚገኘው ዘመን መጸው ይባላል::መጸው› ማለት ‹ወርኀ ነፋስ› (የነፋስ ወቅት) ማለት ሲኾን ይኸውም ‹መጸወ ባጀ፤ መጽለወ ጠወለገ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ይህ ወቅትየሚገባው  በልምላሜ፣ በአበባ፣ በፍሬ ወቅት ነው፡፡ በውስጡም አምስት ንዑሳን ክፍሎችን የሚያካትት ሲኾን እነዚህም፡- ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ አስተምህሮ፣ ዘመነ ስብከት፣ ዘመነ ብርሃን እና ዘመነ ኖላዊ ናቸው (ያሬድና ዜማው፣ ገጽ ፵፰-፵፱)፡፡

ዘመነ  ጽጌ ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት ነው::
በማቴ 2:13-15 እንደተጻፈ:: ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ ጌታችንን ለማስገደል አሰበ፡፡ ጌታችንም በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታን ያገኘሁ መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ የሁለት ዓመት ከዚያ በታች የኾኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በሰይፍ አስጨርሷል፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን የጌታችን እና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኀ ግንቦት ነው፡፡ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባ፣ የፍሬ ወቅት በመኾኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ ከመስከረም እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በስፋት ተገልጧል፡፡ በተለይ በአባ ጽጌ ድንግል ድርሰት በማኅሌተ ጽጌ በጥልቀት ተመሥጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በዘመነ ጽጌ በማኅሌትና በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚሰጡ ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታት ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን በጥልቅ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡

የእመቤታችን ስደት እንደ ውኃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ ሳይሆን ትንቢት የተነገረለት እና ምሳሌ የተመሰለለት ነው፡፡ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ነብዩ እሳይያስ ‹‹እግዝአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይወርዳል፡፡›› በማለት ትንቢት ተነግሮ ነበር ኢሳ 19-1 ምሳሌውም ቀድሞ አባቶቹ እስራኤላውያን ወደ ግብጽ በተለያዩ ምክንያቶች ተሰደዋል፡፡ በተጨማሪም ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አኳያም ሲታይ ግብጽ ለኢየሩሳሌም ትቀርባለች፡፡ በዘመኑም ክህደት በነዚህ ጸንቶ ነበር፡፡ ግብፃውያን በአምሳለ ላህም ጣዖት ቀርፀው ያመልኩ ስለነበር ወደዚች ሀገር ገብቶ ጣዖታቱን በስልጣኑ ሰባብሯል ሀገሪቱም ሀገረ እግዚአብሔር እንድትሆን ባርኳታል፡፡መሰደዱም ሄሮድስን ፈርቶ ለመሸሽ ሳይሆን ከገነት ለተሰደደው አዳም እንደካሳ ለማጠየቅና በሃይማኖት ምክንያት ለሚሰደዱ ሰማዕታት ስደትን ለመባረክ ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራ በማስታወስ ዘመነ ጽጌን በፈቃዳቸው የሚጾሙ ካህናትና ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን የጽጌ ጾም የፈቃድ ጾም እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት ጋር የሚመደብ ስላልኾነ ጽጌን የማይጾሙ አባቶች ካህናትንና ምእመናንን ልንነቅፋቸው አይገባም፡፡ የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በሄሮድስ እጅ በግፍ የተሠዉ ሕፃናት በረከት አይለየን፡፡ አምላካችን በአበባ የሚመሰለው ሰውነታችን የጽድቅ ፍሬን ሳያፈራ እና ንስሐ ሳንገባ በሞት እንዳንወሰድ መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ምንጭ

  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • ማኅበረ ቅዱሳን ዌብ ሳይት

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።