http://eotcmk.org/a/%E1%8C%BE%E1%88%98-%E1%8A%90%E1%89%A2%E1%8B%AB%E1%89%B5-3/
ጾመ ነቢያት
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ኅዳር ፲፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
እግዚአብሔር አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ መልበሱን፣ ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ ግብጽ ግብር መሰደዱን፣ በባሕረ ዮርዳኖስ መጠመቁን፣ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ማብራቱን፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ልዩ ልዩ ዓይነት መከራ መቀበሉን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ ማረጉንና ዳግም ለፍርድ የሚመጣ መኾኑን በአጠቃላይ የማዳን ሥራውን በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው አስቀደመው በትንቢት ተናግረዋል፡፡ ትንቢቱ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው ኾኖ ዓለምን የሚያድንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎትም በእግዚአብሔር ሰው መኾን ፍጻሜ አግኝቷል፡፡
ይህን ምሥጢር በማሰብ በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ዋይዜማ ድረስ እንድንጾም አባቶቻችን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ ይህ ጾም፣ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሲኾን፣ በስያሜም ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወቅቱ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ የተፈጸመበት ስለ ኾነም ‹‹ጾመአዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት በጾሙበት ማለት ከልደተ ክርስቶስ በፊት ባለው ወቅት ጾመዋልና፡፡
በሌላ አጠራር ይኸው ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያ እና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና ድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ተሰወረባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በዓት ዘግተው፣ ሱባዔ ገብው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ቢለምኑት ልመናቸውን ተቀብሎ ሱባዔ በያዙ በ፫ኛው ቀን የቅዱስ ፊልጶስን ሥጋ (በድን) መልሶላቸው በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት፣ ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡
ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ካበሠራት በኋላ ‹‹ሰማይና ምድርየማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›› በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ እመቤታችን ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹ጾመ ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ በጾመ ነቢያት፣ ነቢያትም ሐዋርያትም፣ ቀደምት አባቶቻችንም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጭ፡–
- ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፡፡
- ጾምና ምጽዋት (፳፻፩ ዓ.ም)፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ – ፶፡፡
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።